Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ችግር ፈጣሪ መፍትሔ የለውም!

እነሆ መንገድ። ከወሎ ሠፈር ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ‹‹አቦ ደመና ነው መነጽሩን አውልቀህ ምናለበት ሰውን ብታየው?›› ይላል በትምባሆ ጭስ ከሰል የመሰለ ከንፈሩን ደጋግሞ የሚያረጥበው ሾፌራችን። ‹‹ፀሐይ ሳለ ሲዘንብ ዓይተህ የማታውቅ ይመስል ደመና ነው ብለህ መነጽሬን ትተቻለህ? ይቅር ይበልህ፤›› ይላል ወያላው። እኩያማቾች ይመስላሉ። ቆየት ብሎ ደግሞ ‹‹ለነገሩ ልክ ነህ የዘንድሮ ሰው እንኳን በመነጽር በዓይንም አልመለስ ብሏል፤›› ብሎ መነጽሩን አወለቀ። ‹‹እንዴት? እንዴት? ደግሞ ከእናንተም ብሶ ሰው ታማላችሁ?›› አለችው ከሾፌሩ ጀርባ ወያላው ክንዱን የሚያስመረኩዝባት መቀመጫ ላይ ዘና ብላ የተቀመጠች ወይዘሮ። ‹‹እኛ ሰው አይደለንም እንዴ? ምነው ትችትና ግምገማ በመደብ መከፋፈል ተጀመረ ደግሞ?›› ብሎ ወያላው አሽሟጠጠ።

‹‹አሁን መደብ ስትል በመደብ ጊዜ የተወለድክ አትመስልም? አንተ ቀርቶብህ ስለመደብ እኛ እናውራ። አየህ ከመደብም መደብ አለ። በአጭሩ ሁለት ዓይነት በለው። በየጊዜው የሚለቀለቅ፣ አጎዛ የሚለብስ፣ ለሰው ታስቦ ለሰው የሚበጅ መደብ ማለት ነው። ያዝክ ይኼን? አዎ። ሌላኛው ደግሞ ንቃቃት የመታው፣ የተፈረፈረ፣ ሰው የማይደርስበት የማይበጅ፣ የማይበጅ (አጥብቃና አላልታ) መደብ አለ። ከፈለግክ ይኼን በዘመኑ መዝገበ ቃል ስትፈታው የመንግሥትና የግል ሌባ እንዳይሆን እንዳይሆን ያደረገው ዓይነት ዘርፍ ልትለው ትችላለህ። ልቀጥል?›› ስትለው ፈገግ ብላ ወያላው ማክረሩን ትቶ፣ ‹‹ለዛሬ ፔሬዱ አልቋል። በሚቀጥለው ጊዜ ከክለሳ እንጀምራለን፤›› አላት። ተጠቃቅሰው ተሳሳቁ። ይኼኔ ሁለተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ ጎልማሳ፣ ‹‹ትምህርት በሬዲዮ ተመልሶ ቢመጣ አንቺን ነበር ርዕሰ መምህር አድርጎ መሾም፤›› አላት። ገርመም አድርጋው፣ ‹‹ራሳቸውን በራሳቸው የሚሾሙ በበዙበት ጊዜ ማን ፈቅዶልህ ነው የምትሾመኝ?›› ስትለው፣ ‹‹ውይ ረስቼው ለካ ለመሾምም ፈቃድ ሰጪ ያስፈልጋል። የሕዝብ ድምፅ በቂ እየመሰለኝ ይኼውልሽ ስሰስት እውላለሁ . . .›› አላትና ከእሱም ጋር የጥቅሻ ቺርስ ተጋጩ። ከአፍ ወለምታና ከግጭት መቼም የዓይን ቺርስ ማለፊያ ነው።  

‹‹ሞልቷል ሳበው!›› አለ ወያላው  ዘሎ  እየገባ። ‹‹ምን ይሞላል ብለህ ነው የዚህ ዓለም ነገር?›› ሶስተኛው ረድፍ ላይ የተቀመጡ አዛውንት ናቸው። ‹‹አይዞን! አንድ ቀን ዓለምም ብትሆን እንደዚች ታክሲ መሙላቷ አይቀርም፡፡ ዓለም ባትሞላ ደግሞ ሲኦልና ገነት ቀድመው ሞልተው ይገላግሉናል፤›› አላቸው። ‹‹ምን? ምን? ሆሆ! ስቴዲየም መሰሉህ እንዴ እንዲህ እንደምታስበው ጢም የሚሉት? መጀመሪያ እስኪ ዓለም ትሙላ። ይቀልዳል እንዴ ይኼ?! እንኳን ዓለም መቼ ሞባይላችንስ ሞላ? እንፍቃለን የለም። ኪሳችን ባዶ። ሆዳችን ባዶ። ኔትወርክ ባዶ። እኮ ዓለም ናት የምትሞላው?›› አሉት አንዴ በመስኮቱ አሻግረው ወደ ውጭ እየተመለከቱ፣ አንዴ ደግሞ ወደ ወያላው ዞረው ዓይን ዓይኑን እያዩ። ‹‹ታዲያ ምን ተሻለ ይላሉ?›› አላቸው ሾፌራችን። የወያላውን ተግባቢነት ለመንጠቅ ይመስላል። ‹‹የዘመኑ ሰው በውድድር ስም የማይነጣጠቀው ነገር የለም፤›› ይላል ከጎኔ። ‹‹ምን ይሻላል? ጊዜን ከዚህ የበለጠ ለመታዘብ ዕድሜ መለመን! አበቃ ሌላውማ። ምንም የሚሻል ነገር የለም። ደግሞ በዚህ ጊዜ ምኑን ትቼ ምኑን እተወዋለሁ ልጄ? እንዲያው በአጠቃላይ የፖለቲካንም የኢኮኖሚንም ወሬ ማመን አያስፈልግም። እኛም እኮ አልሰማ ብለን እንጂ ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም ተብለናል፤›› አሉት። ሾፌራችን ሳቀ።

‹‹መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲያችን መሥራት እንዲጀምር ቢያንስ መፍትሔ የለዎትም?›› ቢላቸው አጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት ተራቸውን ሳቃቸውን ለቀቁት። ‹‹አንተ? ተወኝ ስል አትሰማም እንዴ? አንተስ ብትሆን አርፈህ  ውለህ በሰላም ወደ ቤትህ ብትገባ አይሻልም?  . . . . እ? ምነው አንተን ባደረገኝ! ያልተነካ አቤት ግልግል ሲችልበት እኮ?›› እያሉ አሽሟጠጡት። ወጣቱ ግራ ተጋብቶ አፍሮ ዝም አለ። ወያላው ነገሩን እንደገና አንስቶ፣ ‹‹ ‘ፋዘር’ ታዲያ ነገራችን ሁሉ መቆራረጥ በበዛበት ዘመንና ምድር ላይ ለመኖር ምን ዕድሜ አስለመንዎ?” አላቸው። ‹‹የለም! ርስት ልለምን ኖሯል? ያውም በሊዝ የገባ መሬት? ኧረ ባካችሁ ተውኝ ብያለሁ ዛሬ። ነው ምክክር አላችሁ ሰው የማናገር?›› ብለው ቁጣ ቁጣ አላቸው። ‹‹ይቅርታ ‘ፋዘር’ አስቆጣሁዎት መሰለኝ?” ብሎ ሳይጨርስ፣ ‹‹ወግድ ቀጣፊ! ወትሮም ተደራጅተሽ ስታበቂ ሰውን ክፉ ለማናገር እሳት መጫር ሙያ መስሎሻል አዳሜ፡፡ ቆይ ግድ የለም!›› ብለው አፈጠጡበት። ወያላው ቀልቡ ተገፎ አመዱ ሲቦን ትዕይንቱ ዘና ያደረጋቸው ተሳፋሪዎች ይሳሳቃሉ። ወይ መንገድና ድዱ!

ጉዟችን ቀጥሏል። ከወደ ራዲዮኑ ስለአንጎላ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ወሬ እየሰማን ነው። ‹‹ጆሮዬ ነው ወይስ እውነት ነው?›› ትላለች መካከለኛው ረድፍ ከጎልማሳው አጠገብ የተሰየመች ወጣት። ‹‹ምኑ?›› ስትባል፣ ‹‹አንጎላ የምትባለው አገር ያለችው አፍሪካ ነው አውሮፓ?›› ብላ ሌላ ግራ አጋቢ ጥያቄ አመጣች። ‹‹ጉድ እኮ ነው እናንተ? ካርታም ሳታጠኑ ነው የምትመረቁት? ለነገሩ የዘንድሮ ልጆች ከኮንከርና ከሴካ ውጪ የአገርና የአኅጉር ካርታ ምን ጠቅሟችሁ? ድንቄም እውቀት ተስፋፍቶ ልባችን ወልቋል . . .›› ብለው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየሙ አዛውንት ሲጨሱ ‹‹ኧረ እንደሱ አይደለም አባት። እሷ ለማለት የፈለገችው እንዴት ሆኖ ነው በአፍሪካ ምድር በምርጫ 38 ዓመት ሥልጣን ላይ የቆየ መሪ ተሸንፌያለሁ ብሎ ሥልጣን የሚለቀው ለማለት ፈልጋ ነው። ያለመደብንን ነው በአጭሩ . . .›› ብሎ ጎልማሳው አረጋጋቸው።

‹‹ታዲያ እንደሱ አትልም ቀድሞውን?›› ብለው አዛውንቱ አሁንም በቁጣቸው እፍ እፍ ሲሉ ሌላ ዜና መጣ። ካታሎናውያን ካልተገነጠልን ብለው እሪ ማለታቸውን ስንሰማ ቆየን። አዛውንቱ በተራቸው፣ ‹‹ካታሎን ደግሞ የትኛዋ የአፍሪካ ክልል ላይ ትሆን?›› ብለው ተራቸውን አወናበዱን። መጨረሻ ወንበር የተሰየሙ ወጣቶች፣ ‹‹እኮ የእኛው ባርሴሎና ከላሊጋ ሊወጣ? እኮ ኤልክላሲኮ የሚባል ነገር ላናይ?›› እያሉ እንደ ኳስ ያብዳሉ። አዛውንቱ ግራ ተጋብተዋል። ጎልማሳው ይኼኔ፣ ‹‹ካታሎን የስፔን ግዛት ናት። አፍሪካ ውስጥ አይደለችም፤›› አላቸው። ይኼኔ አዛውንቱ አንጎላን አውሮፓ ወስዳ ልትከልላት ወደ ሞከረችው ወጣት ቀና ብለው፣ ‹‹የእኔ ልጅ ይቅር በይኝ። ፊተኞች ወደኋላ፣ ኋለኞች ወደፊት ቦታ እየተቀያየሩ እኮ ዓለምና ካርታዋ ተዘበራረቁብን፤›› ብለው ተሳፋሪውን አዝናኑት።

መንገዱ ከተጋመሰ ቆይቷል። ወያላችን ሒሳቡን ሰብስቦ መልስ በመመለስ ተጠምዷል። አንዳንዱ አፍንጫውን ይዞ መልስ ሲቀበለው ለአንዳንዱ የመልስ ሳንቲሙን ለመስጠት ወያላው ራሱ ይለምናል። ‹‹ኧረ ተቀበለኝ ወንድሜ!›› ይላል ወያላው መጨረሻ ወንበር በጥግ በኩል በሁለቱም ጆሮዎቹ ‘ኢርፎን’ ሰክቶ ‘ስማርት’ ስልኩን እየጎረጎረ አጠገቡ ያሉትን የረሳውን ታዳጊ አስግጎ። በስንት ጉትጎታ አጠገቡ ባሉት ተሳፋሪዎች ጉሰማ ልጁ ጆሮውን የደፈነበትን ገመድ ነቅሎ መልሱን ተቀበለ። ‹‹ይኼ ትውልድ እኮ በዚህ ዓይነት እንኳን ለአዲስ አሠራርና ዓላማ ጥያቄ ሊጠይቅ፣ ለአሮጌው ጥያቄ መልሱ ሲመጣም ግድ የለውም ማለት ነው?›› አሉ  አዛውንቱ። እዚያው አካባቢ ጠየም አጠር ያለች የደስደስ ያላት ልጅ፣ ‹‹ምን ይደረግ! የደጉ ዘመን ሰው፣ ሰው ከፍቶ ሲያስከፋው ፈረሱን ወይም በቅሎውን ኮርቻ ይጭናል። የአሁኑ በተራው እያየ ላለማየት፣ እየሰማ ላለመስማት ሲመኝ ‘በዳውንሎድ’ ጥበብ ስልኩን በመጫን ይጠመዳል፤›› አለች።

አዛውንቱ እኛ የገባን የገባቸው አይመስሉም። የሕይወት ዘይይ ገጽታዋን ስትቀያይር በቋንቋም ታደንቋቁረን ይዛለች። ታዳጊው በተራው ነገሩን በዝምታ ሊያልፈው አልወድ ብሎ ‹‹ታዲያ የሰው ልጅ በማሰብ ችሎታዬ በሥልጣኔ እዚህ አደረስኳት የሚላት ዓለም እያደር የጦርነት፣ የሽብርና የክፋት አውድማ ከሆነች ምን ማድረግ አለብን?›› ብሎ በአካባቢው ያሉትን ተሳፋሪዎች ገላመጣቸው። ‹‹እውነት ነው! ‘ቫይበር’ እና ‘ፌስቡክ’ ባይኖሩን ኖሮ ዛሬ ዛሬ ምን እነሆን ነበር? ዓለም እንደሆነች ይኼን ያህል ሺህ ዘመን ፍትሕ የማታውቅ፣ በፖለቲካ ቁማር የሕዝቦች ሰላማዊ ኑሮን ማመስ ያልሰለቻት ሆነች። ደግሞስ እንኳን ፍትሕን የዓለም ዋንጫን አራት ዓመት እየጠበቅን መሳተፍ ህልም የሆነብን ከዚህ በላይ ብንዘጋጋ ይገርማል?›› አለች ጠይሟ ወጣት። እንደኖሩት ኖረው እንደሚሰነብቱት እየሰነበቱ ያሉት አዛውንት በበኩላቸው ዝምታን መርጠዋል። እንዲህ እንዲህ ያለው ሰዓት ላይ ዝምታው ብዙ ይላል!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወጣቶቹ እየተቀባበሉ ስለ ላስቬጋስ የጅምላ ፍጅት ያወራሉ። ‹‹ቆይ ግን ኃላፊነቱን ማን ወሰደ?›› ይጠይቃል አንደኛው። ‹‹ነፍስ እየነጠቁ ኃላፊነት መውሰድ ማለት ምን ማለት ነው?›› እያለ ጎልማሳው ያጉተመትማል። ‹‹ገዳዩ ነጭ ነው ጥቁር?›› ትጠይቃለች መስኮት ጥግ የተሰየመችው። ‹‹ነጭ ነው!›› ይላታል አንደኛው ወጣት። ‹‹ተመስገን!›› ብላ ተነፈሰች። ተሳፋሪዎች በሙሉ ደንግጠው አፍረው ወደእሷ ዞሩ። አመዷ ቡን አለ። በዚህ ጉድ ስንል ደግሞ አንዱ ምን ይላል ‹‹ሙስሊም ነው ክርስቲያን?›› ከማለቱ፣ ‹‹ኧረ በፈጠራችሁ እናንተ ሰዎች? እንዴት ነው ይህን ያህል አዕምሮ የነሳችሁ? የሴረኛን ደባ እንደ ማምከን መልሳችሁ በእሱ ልሳን ስትስቱ አታፍሩም? ሰውዬው ነጭም ጥቁርም አይደለም። ነጭና ጥቁር ብሎ ነገር የሚሠራው ቀለም ፋብሪካ ብቻ ነው። ሰይጣን በሰው ሲያድር ብርቅ ነው እስኪ አሁን? ሀ ብሎ ሲጀምር በቃየል ልብ ክፉ ሐሳብ አድሮ ወንድሙን አቤልን ገደለው አይልም መጽሐፉ? ምነው አንዳንዴ እንኳን የቢቢሲንና የሲኤንን ያህል ጊዜ ባትሰጡት እንኳ መጽሐፉን ብትገልጡት?” ብለው አዛውንቱ ተቆጡ።

‹‹የለም አባት ይረጋጉ። አሁን ዘመኑ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሐሳብ የሚገዛው ነው። ጀርባ የምናጠናው ርዕዮተ ዓለሙን ለማውገዝ እንጂ ሰውን በቀለም፣ በሃይማኖትና በዘር ለመፈረጅ አይደለም፤›› ሲላቸው ከወጣቶቹ አንደኛው፣ ‹‹ወግድ እናንተም እንደ ዘመኑ ሬዲዮ ናቸሁሳ። የዘመኑ ሬዲዮ አንቴና፣ ጣቢያ ማስተካካያና ወንፊት የለው። ከየት እንደሚስብ አይታወቅ ብቻ ዝም ብሎ እየሳበ መትፋት ብቻ። ይብላኝላችሁ . . .›› እያሉ ሲንገሸገሹ ወያላው ‹‹መጨረሻ›› ብሎ በሩን ከፈተው። ከራስ ጥቅምና ከራስ ገድል አንፃር ወሬ በሚተረጎምበት ጎዳና፣ አንድ በአንድ ወርደን ስናበቃ ከሚተመው ጋር መትመም ጀመርን። ወንፊትና አንቴና ያለው ስንቱ ይሆን ነው ጥያቄው? ወይስ አልበርት አንስታይን እንዳለው ችግር ፈጣሪ መፈትሔ አያመጣም ብለን እንለፈው? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት