Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሜታ ቢራ ከስድስት ሺሕ በላይ ገበሬዎችን ተጠቃሚ ያደረገበት አሠራር ለሽልማት እንዳበቃው አስታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ8000 ቶን በላይ ምርት ለፋብሪካው እንዳቀረቡ ገልጿል

የእንግሊዙ ዲያጆ ኩባንያ የጠቀለለው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ፣ ‹‹አብሮ ለማደግ ከአገር ውስጥ አምራቾች ግብዓቶችን መግዛት›› በሚል መርኅ፣ ላለፉት አራት ዓመታት ለምርት ጥሬ የሚያውላቸውን ምርቶች ከገበሬዎች ሲገዛ መቆየቱና በዚህም መሠረት ላበረከተው አስተዋፅኦ፣ በአሜሪካ በተሰናዳው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ለመሸለም እንዳበቃው አስታወቀ፡፡

ኩባንያው ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ መስከረም 8 ቀን 2010 ዓ.ም. በአሜሪካ፣ ኒው ዮርክ በተካሔደ ሥነ ሥርዓት ወቅት ሜታ ቢራን ለሽልማት ያበቃው 6400 አነስተኛ ገበሬዎችን በማሳተፍ ከ8000 ቶን በላይ እህል እንዲያመርቱ ያስቻለ ፕሮግራም (ሶርሲንግ ፎር ግሮውዝ -S4G) መተግበሩ ነው፡፡ ፕሮግራሙ ከአራት ዓመታት በፊት ሲጀመር ተሳታፊ የነበሩ አነስተኛ ገበሬዎች ቁጥር 800 እንደነበርና በአሁኑ ወቅት ከ6400 በላይ እንደደረሰ ሜታ ቢራ አስታውቆ፣ በወቅቱ ያመርቱት የነበረው የምርት መጠንም 150 ቶን እንደነበርና ይኼም በአሁኑ ወቅት ወደ 8000 ቶን ማደጉን ጠቅሷል፡፡

ይኼንን ፕሮግራም የዓለም ባንክና የካናዳው ዓለም አቀፍ የልማት ምርምር ማዕከል በአጋርነት በሚያስተባብሩት ‹‹አዲስ ራዕይ ለልማት›› (ኒው ቪዥን ፎር ደቨሎፕመንት) ተብሎ ለተሰየመው የውድድር መርሐ ግብር በማስገባት ተሳትፏል፡፡ በውድድሩም ከተመረጡት መካከል በመሆን ለመሸለም መብቃቱን አስታውቋል፡፡ የፕሮግራሙ ዓላማ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ግብዓቶችን በመጠቀም ከውጭ የሚገባውን ምርት ማስቀረት፣ ብሎም የአነስተኛ ገበሬዎች አምራችነት በማሳደግ የገቢ አቅማቸውን ማሻሻልና ኑሯቸውን መደገፍን ያማካለ ነው፡፡ ይኼ ሲሆን የምርት መጨመር ከመፈጠሩም ባሻገር የዲያጆ ኢትዮጵያን የምርት አቅርቦት እንደሚያሳድገው ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም እስካሁን ሲያካሒድ በቆየው ፕሮግራም በአብዛኛው ለቢራ ጠመቃ የሚውል የገብስ ምርት ሲያስመርት ከመቆየቱም በተጨማሪ ማሽላንም አካቷል፡፡ 

ባለፈው ዓመት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የማሽላ ምርትን በሰፊው ለማስመረት እንቅስቃሴ በማድረግ በሰሜኑ ክፍል ለሚኖረው ሕዝብ ፍጆታ እየዋለ የሚገኝ አዲስ የቢራ ምርት ማስተዋወቁን የገለጸው ሜታ ቢራ፣ ይኼንኑ አሠራር በማስፋፋት ገበሬዎችን ተጠቃሚ በማድረግ ራሱንም የምርት አቅርቦት ተጠቃሚ የማድረግ አሠራሩን እንሚያጠናክር አስታውቋል፡፡ ‹‹ሶርሲንግ ፎር ግሮውዝ›› የተሰኘው ፕሮግራም በኢትዮጵያ በተለየ መንገድ በመተግበር ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ ሜታ ቢራ ከኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ፣ ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ፣ ከቴክሰርቭ ኩባንያ፣ ከሲንጄንታ፣ ከባስፍ፣ ከኒያላ ኢንሹራንስና ከሌሎችም አጋሮቹ ጋር በትብብር ሲሠራ መቆየቱን አስታውቋል፡፡

ከተመሠረተ 50 ዓመታትን ያስቆጠረው ሜታ አቦ ቢራ ፋብሪካ በመንግሥት ባለቤትነት ሲተዳደር ቆይቶ፣ ከአምስት ዓመታት በፊት ለእንግሊዙ ዲያጆ ኩባንያ በ225 ሚሊዮን ዶላር መሸጡ ይታወሳል፡፡ ዲያጆ ሜታ አቦን ከገዛ በኋላ ለማስፋፊያ ተጨማሪ የ119 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ማካሄዱም አይዘነጋም፡፡ ዲያጆ ከ180 በላይ አገሮችን የሚያዳርሱ ልዩ ልዩ የመጠጥ ምርቶችን በማምረት ይታወቃል፡፡ ጆኒ ዎከርን ጨምሮ፣ ክራውን ሮያል፣ ጄብ፣ ቡካናን፣ ዊንድሮስ ዊስኪ፣ ስሚርኖፍ፣ ካፒቴን ሞርጋን፣ ኪትል ዋን ቮድካስ የሚባሉትን ጨምሮ ሜታ ቢራና ጊነስን በምርቱ ዝርዝር ውስጥ በማካተት ዓለም አቀፍ ድርሻውን በአፍሪካም እያስፋፋ መጥቷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች