Monday, September 25, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከዓለም ባንክ በተገኘ የ50 ሚሊዮን ዶላር ብድር የጥራት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት ሊተገበር ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጥራት መሠረተ ልማት ተቋማትን አቅም ለማጠናከር ያስቻላል ያለውን የ50 ሚሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ይፋ አደገ፡፡ የፕሮጀክቱን ማስፈፀሚያ የገንዘብ ብድር ያገኘው ከዓለም ባንክ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ፣ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን ጽሕፈት ቤት፣ የኢትዮጵያ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩትና የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅቶች የፕሮጀክቱ ተቀዳሚ ተጠቃሚዎች እንደሆኑ ታውቋል፡፡ በተቋማቱ ፍተሻ ከሚደረግባቸው ምርትና አገልግሎቶች መካከል የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ተደርገው የተለዩ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ላይ የሚታዩ የጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ ያለመ ፕሮጀክት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም አግሮ ፕሮሰሲንግ በፕሮጀክቱ ተለይተው የወጡና ትኩረት የተደረገባቸው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ናቸው፡፡

ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ማድረግ ቀዳሚ ዓላማው እንደሆነ በተጠሰው ፕሮጀክት ውስጥ እንዲካተቱ የተመረጡት የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች የሚገለገሉባቸውን የቴክኖሎጂ ግብአቶችን ማስፋፋትና ለባለሙያዎችም የዕውቀትና የክህሎት አቅም ግንባታ ሥራዎች ይከናወኑበታል፡፡

‹‹በተለያዩ አገሮች የጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና ቆዳ ምርቶች እንዲሁም የአግሮ ፕሮሰሲንግ ውጤቶችን በተመለከተ የተዘጋጁ መስፈርቶች አሉ፡፡ ምርቶቹ የተቀመጡትን መስፈርቶች ማሟላት አለማሟላታቸውን የሚፈትሹበት በቂ ቴክኖሎጂ አላቸው፡፡ ይሁንና በአገሪቱ በቂ የሚባል፣ የተሟላ ላቦራቶሪ የለም፡፡ ቶክኖሎጂዎቹ በጣም ውድ ናቸው፡፡ ስለዚህም በተገኘው ብድር ቴክኖሎጂዎችን የማሟላት ሥራ ይሠራል፤›› ያሉት የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ የግሉንም ዘርፍ ወደ ጥራት መሠረተ ልማት አገልግሎቶች በመግባት ተጠቃሚ እንዲሆን የማድረግ ሥራም ይሠራል፡፡ በሌላው ዓለም የግሉ ዘርፍ በእነዚህ አገልግሎቶች በስፋት የሚሳተፍና የሚጠቀም ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን በመንግሥት ከተቋቋሙ ድርጅቶች ውጪ በጥራት መሠረተ ልማት የተሰማሩ የግል ድርጅቶች እምብዛም ናቸው ማለት ያስችላል፡፡

‹‹እንደ አገር እየገነባን ያለነው ሰፊና ግዙፍ ኢኮኖሚ ለሚጠይቀው መጠነ ሰፊ የአገልግሎት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የግሉ ዘርፍ ካልታከለበት፣ መንግሥት በሚያቋቋማቸው ተቋማት ብቻ መዝለቅ አይችልም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ፕሮጀክቱ የግሉ ዘርፍ ምርቶችንና አገልግሎቶችን የመፈተሽ አቅም እንዲኖረው አስፈላጊውን የፋይናንስና የሎጂስቲክስ ድጋፎች እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡

‹‹ጥራት የሌላቸው ምርቶች ወደ ውጭ ተልከው የሚመለሱበት ሁኔታ እያጋጠመን ነው፡፡ ይህም የሚልኩበት አገር የሚጠይቀውን መስፈርት ማሟላት አለማሟላቱን ፈትሾ መላክ ያለውን ጥቅም ባለመረዳት የሚከሰት ነው፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ለላኪዎች ጭምር የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለመሥራት ዕቅድ መያዙን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኰንን፣ ፕሮጀክቱ ተቋማቱን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ያግዛል ብለዋል፡፡ ለአምስት ዓመታት ለሚቆየው ይህ ፕሮጀክት፣ በየዓመቱ አሥር ሚሊዮን ዶላር ፈሰስ እንደሚደረግለት፣ የመንግሥት የትኩረት አቅጣጫ በሆኑ በአራቱ የማኑፋክቸሪንግ መስኮች ላይ ያተኮረ በመሆኑም በአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ ተገቢውን ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ዕውን የማድረግ እንቅስቃሴ የተጀመረው ከዘጠኝ ወራት በፊት ሲሆን፣ ከዓለም ባንክ የብድር ጥያቄ ይሁንታን ያገኘው ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ነው፡፡ በመሆኑም 38.2 ሚሊዮን ዶላር የተቋማቱን አቅም ለማጠናከር የተመደበ ነው፡፡ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን ኢንዱስትሪ የሚፈለገውን አቅም መገንባት፣ እንዲሁም አገልግሎትና ምርት ከፍላጎት ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ላይ ያተኮረው ፕሮጀክቱ አገሪቱ ከውጭ ንግድ የምታገኘው ገቢ እንዲጨምር ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል፡፡  

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች