Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፕሪሚየም ስዊች ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የክፍያ ልውውጦችን እንዳከናወነ አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በኤቲኤም አማካይነት ወደ ቁጠባ ሒሳብ ገንዘብ ማስገባት ይጀመራል ተብሏል

ከሰባት ዓመታት በፊት በሦስት ባንኮች ጥምረት የተቋቋመውና ከጊዜ በኋላ ሌሎች ሦስት የግል ባንኮችን በማካተት ወደ ሥራ የገባው ፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽንስ አክሲዮን ማኅበር፣ ሥራ ከጀመረ ወዲህ በአምስት ዓመታት ውስጥ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማስተላለፍ መቻሉን አስታወቀ፡፡ ኩባንያው ሥራ የጀመረበትን አምስተኛ ዓመት እንዲሁም የ2009 ዓ.ም. ክንውኑን በማስመልከት ቅዳሜ፣ መስከረም 20 ቀን 2010 ዓ.ም. እንዳስታወቀው ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ውጤት ያሳየበት ክንውን አስመዝግቧል፡፡

የፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽንስ አክሲዮን ማኅበር የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ፀሐይ ሽፈራው (የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት ናቸው) እንደገለጹት፣ ኩባንያው ያስተናገዳቸው ልዩ ልዩ ክፍያዎች በጠቅላላው ከ10.7 ሚሊዮን በላይ ሲሆኑ፣ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ማንቀሳቀስ ችሏል፡፡

ሕብረት፣ አዋሽ፣ ንብ፣ ብርሃን፣ አዲስ ኢንተርናሽናል እንዲሁም የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮችን በአክሲዮን አባልነት ያካተተው ፕሪሚየር ስዊች (ፒኤስኤስ)፣ የ2009 ዓ.ም. የተናጠል አፈጻጸሙ ከቀደሙት ዓመታት የላቀ እንደነበር የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ከኩባንያው ሲስተም ጋር በተገናኙ 560 የኤቲኤም ማሽኖችና በ880 የሽያጭ መዳረሻ ተርሚናሎች አማካይነት ያንቀሳቀሰው ገንዘብ 4.8 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በዚህ ሒደት 5.4 ሚሊዮን የኤቲኤም ማሽኖች ያንቀሳቀሱት የክፍያ መጠን ሲሆን፣ ከ26 ሺሕ በላይ የሚሆነውን የገንዘብ ማስተላለፍ እንቅስቃሴ የሽያጭ መዳረሻ ጣቢያ ማሽኖች እንዳከናወኑ ተገልጿል፡፡ በመሆኑም ባለፉት ዓመታት በኩባንያው በኩል ከተንቀሳቀሰው የገንዘብ መጠን ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡ ይኼም ከ2007 ዓ.ም. ጋር ሲነፃፀር የ45 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየ ተመልክቷል፡፡

በተገባደደው ዓመት ቪዛ፣ ማስተር ካርድ እንዲሁም ዩኒየን የተባሉ የውጭ የክፍያ ካርዶችን በመጠቀም የገንዘብ መጠናቸው ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ የሚጠጋ 94,456 ክፍያዎችና የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ፒኤስኤስ በሚያንቀሳቅሳቸው የኤቲኤምና የሽያጭ መዳረሻ ጣቢያ ማሽኖች (ፖስ) አማካይነት ተከናውኗል፡፡ በዚህም በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ እንዲገኝ አስተዋፅኦ ማድረጉም ተጠቅሷል፡፡

ፒኤስኤስ በአገሪቱ በሚገኙ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶች መካከል ትስስር እንዲፈጠር ታስቦ በተቋቋመው የብሔራዊ የክፍያ ሥርዓት (EthSwitch) አተገባበር ላይ ጉልህ አስተዋፅኦ አበርክቷል ተብሏል፡፡ ብሔራዊ የክፍያ ሥርዓቱ ተግባራዊ በሆነበት የመጀመርያው ዓመት፣ የፒኤስኤስ የክፍያ ማሽኖች ከ945,000 ያህል የሌሎች ባንኮች ደንበኞችን የገንዘብ ክፍያ ጥያቄዎችን እንዳስተናገዱ ኩባንያው ገልጿል፡፡ ከሌሎች ባንኮች የቀረቡ የገንዘብ ክፍያ ጥያቄዎችን መሠረት በማድረግ የተስናገደው የገንዘብ መጠንም ከ597 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ኩባንያው ይፋ አድርጓል፡፡

በዓመቱ ውስጥ 59 ሚሊዮን ብር ክፍያ የተፈጸመባቸው 19,016 የግብይት ጥያቄዎች በፒኤስኤስ የክፍያ ማሽኖች አማካይነት መስተናገዳቸውን፣ ይህም ካለፉት ዓመታት አፈጻጸም አኳያ ላቅ እንደሚል አቶ ፀሐይ ጠቅሰዋል፡፡

ባንኮች የዘረጉትን የሞባይል ክፍያ ሥርዓት ከፒኤስኤስ ጋር በማስተሳሰር በአገራችን ለመጀመርያ ጊዜ ደምበኞች በሞባይል ክፍያ አማካነት የባንክ ደብተራቸውንም ሆነ የኤቲኤም ካርዳቸውን ሳይጠቀሙ ከኤቲኤም ገንዘብ ማውጣት እንዲችሉ መደረጉን የኩባንያው ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ ይህም በተለያዩ የክፍያ መንገዶች መካከል ጥምረት በመፍጠር ለደምበኞች የተቀላጠፈና ምቹ አገልግሎት እንዲዳረስ ማስቻሉ ተጠቅሷል፡፡

‹‹ኤቲኤም ከሞባይል ባንኪንግ ሥርዓት ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ ለምሳሌ ገንዘብ ማውጣት ቢያስፈልግ፣ ከሞባይል ስልክ ወደ ኤቲኤም ትዕዛዙን በማስላለፍ ከኤቲኤም ገንዘብ ማውጣት ይቻላል፤›› ያሉት አቶ ፀሐይ፣ ዲጂታል ባንኪንግ ማለት የሞባይል ኢንተርኔትን ከኤቲኤም ጋር በማስተሳሰር አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ሥርዓት እንደሆነ በማብራራት አዲሱ የክፍያ ዘዴ እንዴት ሥራ ላይ እየዋለ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የፒኤስኤስ አባል ባንኮች ገንዘብ ከማስገባትና ከማስወጣት ባሻገር በኤቲኤም አማካይነት ገንዘብ መላክ እንደሚችሉም አብራርተዋል፡፡

አንድ የአዋሽ ባንክ ደንበኛ ለምሳሌ እንዴት ወደ ማንኛውም አካባቢ በኤቲኤም በኩል ገንዘብ መላክ እንደሚችል ሲገልጹም፣ ‹‹ለምሳሌ መቐለ ዩኒቨርሲቲ የሚማር ወንድም ቢኖርህ፣ ገንዘብ አስገብተህለት ኮዱን ስትነግረው ወደ ማንኛውም ኤቲኤም በመሄድ ኮዱን አስገብቶ ገንዘብ ማውጣት ይችላል፤›› በማለት በኤቲኤም ገንዘብ መሰጠት ስለጀመሩ ተናግረዋል፡፡

 በኤቲኤም አማካይነት ደንበኞች ወደ ቁጠባ ሒሳባቸው ገንዘብ ማስገባት የሚችሉበት አሠራርም ይተገበራል ብለዋል፡፡ ይህም ገንዘብ በፖስታ ውስጥ በማድረግ ወደ ኤቲኤሙ በማስገባት ማሽኑ ገንዘቡን ቆጥሮ በሒሳብ መዝገባቸው እንዲመዘግብላቸው የሚያደርግ አሠራርም እየተጀመረ እንደሚገኝ አቶ ፀሐይ ተናግረዋል፡፡   

እንደኩባንያው መረጃ በ2009 ዓ.ም. ብቻ በአባል ባንኮች በኩል ዝግጁ የሆኑ 258 ኤቲኤሞችና 264 ፓይንት ኦፍ ሴል ተርሚናሎች ከፒኤስኤስ መረብ ጋር በማገናኘት ሥራ እንዲጀምሩ አድርጓል፡፡ ይህም እስካሁን ከፒኤስኤስ መረብ ጋር የተያያዙትን ኤቲኤሞች ቁጥር 566 እንዳደረሰውና ፖይንት ኦፍ ሴል ተርሚናሎቹንም ወደ 887 ከፍ እንዳደረው ተጠቅሷል፡፡

በተጠናቀቀው 2009 ዓ.ም. ፒኤስኤስ ያስመዘገበው አጠቃላይ ገቢ 43 ሚሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህ መጠን ቀድሞ ከነበረው አኳያ ሲነጻጸር የ26 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በ2009 ዓ.ም. ኩባንያው ወደ አትራፊነት የተሸጋገረበት ጊዜ መሆኑን  የሚያመለክተው መረጃ፣ በዓመቱ ከግብር በፊት 10.4 ሚሊዮን ብር ትርፍ እንዳስመዘገበ አመላክቷል፡፡  ይህ የትርፍ መጠን በ2008 ዓ.ም. ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከ20 እጥፍ በላይ አድጓል፡፡

በፒኤስኤስ የባንኮችን የውድድር ሥርዓት ሳያዛባ፣ በትብብርና በጋራ የክፍያ ሥርዓት ልማት ላይ እንዲሳተፉ ያስቻለ መሆኑንና እንዲህ ያለው ትብብርም የአንዱ ባንክ ደንበኛ የሌላውን የክፍያ ወይም የሽያጭ መዳረሻ ክፍያ ማሽን ተጠቅሞ አገልግሎት እንዲያገኝ በማድረግ እንዳገዘ ተነግሮለታል፡፡ እያንዳንዱ ባንክ በተናጠል የየራሱን ሥርዓት ዘርግቶ ቢሠራ ሊያወጣ ይችል ከነበረው ወጪ እንደታደገውም ተጠቅሷል፡፡

በተጠናቀቀው ዓመት 300,000 የሚጠጉ ካርዶችን አትሞ ለአባል ባንኮች በማቅረብ ኩባንያው እስካሁን ለአገልግሎት ያቀረባቸውን የካርዶች ቁጥር ወደ 700,000 ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም ዓምና ከተመዘገበው አኳያ የ70 በመቶ ብልጫ ሲኖረው፣ ድርጅቱ ሥራ ከጀመረ አንስቶ ካተማቸው ኮርዶች ውስጥ አኳያም የ43 በመቶ ድርሻ እንደያዘ አቶ ፀሐይ ገልጸዋል፡፡ ከዓመት ዓመት እየታየ ያለው ዕድገት በኢንዱስትሪው ውስጥ ካለው ዓመታዊ አማካይ የካርድ አቅርቦት ዕድገት ጋር ሲተያይም ከፍ ያለ ቁጥር የተመዘገበበት ሲሆን፣ በአገሪቱ የፋይናንስ አገልግሎት በኩል ያለው ድርሻም እያደገ እንደመጣ አመላካች ሆኗል፡፡

የካርድ ባንኪንግ አገልግሎት በኢትዮጵያ ብዙ እንደሚቀረው እነ አቶ ፀሐይ ይናገራሉ፡፡ አገልግሎቱ ከተጀመረ አራት ዓመት ያህል ማስቆጠሩን አቶ ፀሐይ አስታውሰው፣ ወደፊት አገልግሎቱ ይበልጥ እያደገ እንደሚመጣ ያምናሉ፡፡ ዋናው ጉዳይ መሠረተ ልማት እንደሆነና በአሁኑ ወቅትም ይኸው መሠረተ ልማት በመዘርጋቱ  አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በኤቲኤም፣ በሞባይል ስልኮችና በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የሚታገዝ የፋይናንስ አገልግሎት በመፍጠር በየዓመቱ አዳዲስ ነገር እናመጣለን ብለዋል፡፡

ኩባንያው ባካሔደው ፕሮግራም ወቅት፣ ኩባንያውን አሁን ለደረሰበት ደረጃ በማድረስ ከምሥረታው ጀምሮ በተለያዩ ኃላፊነቶች ሲሠሩና አስተዋፅኦ ሲያደርጉ ለነበሩ የቀድሞ የፒኤስኤስ ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ጌታነህ፣ አቶ አመርጋ ካሳ፣ አቶ ለይኩን ብርሃኑ እንዲሁም አቶ እሸቱ ፋንታዬ የኩባንያውን እውቅና በመስጠት፣ ለባረኩት አስተዋፅኦ ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች