Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልእየጠፉ ያሉትን ባህላዊ ቅርሶች የሚታደጋቸው ማን ነው?

እየጠፉ ያሉትን ባህላዊ ቅርሶች የሚታደጋቸው ማን ነው?

ቀን:

ለኢትዮጵያዊ ጥንታዊነት ምስክርነት የሚቆሙ በተለያዩ ሥፍራዎች በርካታ ባህላዊ ቅርሶች ይገኛሉ፡፡ ለዘመናት ‹‹የሦስት ሺሕ ዓመት›› ታሪክ የሚለውን ብሒል የሚቀይሩ፣ ከአራት ሺሕ ዓመታት በላይ የሚያስቆጥሩ ግኝቶች፣ በሥነ ቁፋሮ ባለሙያዎች መገኘታቸው ከአሠርት ወዲህ ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡ ለዚህም በምሥራቅ ትግራይ በቀድሞው አጋመ አውራጃ፣ ከዓዲግራት ዛላምበሳ መስመር፣ ፆና ዓዲ በሚባለውና በመነበይቲ መንደር በቁፋሮ የተገኘው ግኝት የሚያሳየው መንበይቲ ከአክሱም ሥልጣኔ በፊትና በዘመነ አክሱም መካከል የነበረ መሆኑን ነው፡፡

እየጠፉ ያሉትን ባህላዊ ቅርሶች የሚታደጋቸው ማን ነው?

 

የአሁኑ ምሥራቃዊ ዞን ዓጋመ፣ ክልተ አውላሎና ኢሮብን የሚያካልል ሲሆን፣ በርካታ ባህላዊ ቅርሶች የሚገኙበት ነው፡፡ በርካታ ሐውልቶች፣ የዋሻ ሥዕሎች፣ የቤተ መንግሥት ፍራሾች፣ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት፣ እንዲሁም የድንጋይ ላይ ጽሑፎችንም አቅፎ ይዟል፡፡ የአውሮፓውያን ተመራማሪዎች ትኩረት የሳበው አካባቢው ያሉትን ሀብቶች ከመጠበቅና ከመንከባከብ አንፃር ክፍተት እንዳለበት ይልቁንም በተለያዩ ምክንያቶች በቅርሶቹ ላይ ጥፋት እየደረሰ መሆኑ ይነገራል፡፡

ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የመስቀል በዓል አጋጣሚ ባዘጋጀው አራተኛው የአርኪዮሎጂ ኢንተርናሽናል ዐውደ ጥናት ላይ ይኼው ተንፀባርቋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአርኪዮሎጂ ረዳት ፕሮፌሰር ተክሌ ሐጎስ፣ በምሥራቃዊ ዞን ከዋሻ ዘመን ጀምሮ እስከ 19ኛው ምዕት ባሉት ዘመናት የታዩ ባህላዊ ቅርሶች፣ የሚገኙበትንና እየደረሰባቸው ያለውን አሉታዊ ተፅዕኖ በተመለከተ (Condition Assessments of the Tangible Cultural Heritage Resources of Eastern Tigray) ዳሰሳ አቅርበዋል፡፡

እየጠፉ ያሉትን ባህላዊ ቅርሶች የሚታደጋቸው ማን ነው?

 

እንደ አቶ ተክሌ አገላለጽ፣ በርካታ ቅርሶች ላይ በተፈጥሮና በሰው ሠራሽ አማካይነት ጉዳት ደርሷል፡፡ ጥናቱ የሚያሳየው 99 በመቶ የሚሆነው ጉዳት የደረሰው በሰው ሠራሽ ምክንያት ነው፡፡ ሰው ሠራሽ ማለት አንዱ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በመንገድ፣ በቤት ሥራ የሚመጣ ጥፋት ሲሆን፣ ሁለተኛው ካላዋቂ የሚደረግ የቅርስ ላይ ጥገና ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ ብለው አጥኚው ያቀረቡት በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የተፈጸመውን ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው አንዛ ላይ የሦስተኛው ምዕት የሆነው (ከ1750 ዓመታት በላይ ያስቆጠረ) የድንጋይ ጽሑፍ ሐውልት የቆርቆሮ መጠለያ ሠርቶበታል፡፡

አቶ ተክሌ እንዳሉት፣ የሐውልቱ ጽሑፍ ግልባጩና ኦርጅናል ቅርሱም አንድ አይደሉም፡፡ ሁለተኛ ቆርቆሮና ሐውልት አብሮ አይሄድም ጭራሽ በቆርቆሮ በመዘጋቱ ሰውም አያየውም፡፡ በቅርስ ጥገና ላይ ቆርቆሮ ባዕድ ነገር መሆኑን ያንን መጠገን ካስፈለገ ድንጋይ በሚመስል ነገር መሸፈን ያስፈልግ እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው ጥፋት ከዓዲግራት ከተማ በስተደቡብ በሚገኝ ደብረ ገነት ማርያም (ዲቢላ ስዓት) ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን የተፈጸመ ነው፡፡ የፍልፍል ቤተ ክርስቲያኑ የተወሰነው ክፍል ያላግባብ በሲሚንቶ ሲደፈን፣ የውስጥ ክፍሉም በኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት አሸብርቋል፡፡ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያንነቱን አጥፍቶበታል፡፡ ሌላው ጥፋት የጥንቱን አንዛ ማርያም ቤተ ክርስቲያን አፍርሶ አዲስ ቤተ ክርስቲያን መታነፁ፣ የአክሱም ዘመኑ ማርያም ጠቖት ላይም እንደዚሁ አዲስ ቤተ ክርስቲያን መሠራቱ የቅርሱን ገጽታ ለውጦታል፡፡

አቶ ተክሌ ተጨማሪ ጥፋት ያሉት ከመቐለ ወደ ዓዲግራት የሚወስደው መንገድ ሲሠራ በአካባቢው የቅድመ ጥንቃቄ ጥናት ባለመደረጉ በርካታ የአክሱም ዘመን ሕንፃዎችና ቅርሶች የኢንዱስትሪ ቦታዎች መጥፋታቸው፡፡ በአፅቢ የሚገኙ ሐውልቶችም ሆን ተብሎ ተሰብረዋል፡፡ በእርሻ የተነሳም ሐውልቶች ከየቦታቸው እየተነሱ ያላግባብ ውለዋል፡፡

የዋሻ ሥዕሎች

‹‹ኢትዮጵያ የዋሻ ሥዕሎች ሙዚየም ብትባል ማጋነን አይሆንም፤›› የሚሉት አቶ ተክሌ የዋሻ ሥዕሎች ከሱዳን ጠረፍ ከሰሜን ምዕራብ ትግራይ ጀምሮ በተምቤን በኩል አድርጎ፣ በምሥራቅ ትግራይ ወደ አፋር፣ ወደ ምሥራቅና ደቡብ በተዘረጋ ሰንሰለት ውስጥ በርካታ የዋሻ ሥዕሎች አሉ፡፡ ከስድስትና ሰባት ሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ የተሣሉ ናቸው፡፡ አሁን ያሉበት ሁኔታ ከተፈጥሮ ሠራሽ ችግር አኳያ በጣም አሳሳቢና ሁሉም ባለቤት የሌላቸው ናቸው ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ዋሻዎቹ በገጠር ሰው በሌለበት ነው የሚኖሩት፡፡ የቤተ ክርስቲያን ቅርሶች እንኳን ቄሶች ባለቤት መሆናቸው ይጠብቁዋቸዋል፡፡

በአቶ ተክሌ አነጋገር፣ በምሥራቅ ትግራይ የሚገኙት ሥዕሎች ከዕድሜ ብዛት ከመደብዘዛቸውም በተጨማሪ እረኞችም እየሄዱ በቀለም ይነካኩዋቸዋል፡፡ ቱሪስቶች ኬሚካል እየረጩ ፎቶ ያነሳሉ፡፡ ስለዚህ በጣም በአሥጊ ሁኔታ ላይ ስለሚገኙ ትኩረት ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡ እነዚህን በቅጽበት መመዝገብ ያስፈልጋል፡፡

መፍትሔው ምንድን ነው?

አቶ ተክሌ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ጥናቱ የሚያሳየው አብዛኛው ጥፋት የደረሰው በሰው አማካይነት ነው፡፡ ከከፍተኛ የመንግሥት አመራር እስከ ታች ያለው በቅርስ ላይ ያለው ዕውቀት ውስን ነው፤ ግንዛቤም የለውም፡፡ ሌላው ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ባለው የባህል መዋቅር ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ብቃት  ያለው ባለሙያ አይመደብም፡፡ በሌላ በኩል የትግራይ ክልል ለመተግበር አዳጋች የሆነው ዕቅድ አቅዷል፡፡ ግን ስንት ቀላል የሆኑ ነገሮች አሉ የሚሉት አቶ ተክሌ፣ ምሳሌም አቅርበዋል፡፡ አሁን ከመንገድ ላይ ወጣ ተብሎ ለምሳሌ ‹‹ነኳል እምኒ›› የሚባለው ከዕዳጋ ሐሙስ ወጣ ብሎ የሚገኘው ሥፍራ ከአስፋልቱ 20 ሜትር ይርቃል፡፡ እርሱን የሚያመለክት ታፔላ አድርጎና አፅድቶ ቱሪስት ማስጎብኘት ይቻላል፡፡

አቶ ተክሌ የመፍትሔ ሐሳብ ሲሉ የጠቀሱት፣ አጠቃላይ የቅርሶች ምዝገባ በክልሉ ውስጥ መካሄድ እንዳለበት ነው፡፡ ቅርሱ ከተመዘገበ የዳታ ማዕከል ይኖራል፡፡ ቅርስ የሚመዘገበው አንዱ ከጥፋት ለመከላከል፣ ከሕገወጥ ንግድ ለመታደግ፣ ለቱሪስት ልማት ለማዋል፣ ከመሠረተ ልማት ከሚመጣ ጥፋት ለመከላከል ነው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ የሆነ የቅርስ ምዝገባ ሲካሄድ ዳታው (የመረጃ ማዕከል) በፌዴራልም በመቐለም ይኖራል፡፡ ስለዚህ አንድ ባለሀብት ሲመጣ እዚህ አካባቢ ልሠራ ነው ካለ ያለበት ገጽታ ስለሚታወቅ ቅድመ ጥንቃቄ ለመውሰድ ያስችላል፡፡ ምርጥ የተባለ ባለሙያ የሚፈልገው ትልቁ ሥራ ቅርስ ምዝገባ በመሆኑ የተለያየ መድበለ ዕውቀት (መልታይ ዲሲፕሊነሪ) አርኪዮሎጂስት ያስፈልጋል፡፡

በትግራይ ለቱሪዝም የሚሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ያህል ለባህል እንዳልተሰጠ እንዳመለከቱት አቶ ተክሌ አነጋገር፣ የባህልና ቱሪዝም መዋቅር ከላይ እስከ ታች ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ባህልና ቱሪዝም እየተባለ የዘርፉን የሰው ኃይል አይቀበልም፡፡ በክልሎችም በአዲስ አበባም የሠለጠነ የሰው ኃይል የለም እየተባለ 20 ዓመት ተወራ፡፡ አሁን ግን ብዙ የሰው ኃይል አለ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከአክሱም፣ ከመቐለና ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በአርኪዮሎጂና በቅርስ አስተዳደር፣ በቱሪዝም እየተመረቁ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በየቢሮዎቹ ያለው መዋቅር እነዚህን የሰው ኃይል አይቀበልም፡፡ የሠለጠኑትን ሰዎች የሚቀበል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ብቻ ነው፡፡ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም አይቀበልም፡፡ እውነታው ግን ከሙያው ጋር ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች የማይመለከታቸው በየቦታው ተቀምጠው ይታያሉ፡፡  

አቶ ተክሌ በምሳሌነት አንድ አሥር አለቃ ቅርስ መዝጋቢ ሆኖ የተመደበበት ክልል መኖሩን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ስለዚህ ወጣት ተማሪዎችን ወደ ቦታው ማስገባትና የሥራ ላይ የተግባር ሥልጠና መስጠት አስፈላጊነቱን ያሰምሩበታል፡፡ ‹‹ማብቃት የሚባለው ነገር ከሙያው ጋር ለተያያዘ የሚውል ነው፤ በአርኪዮሎጂ የጨረሰ ሰው መርጦ ማሠልጠን ይቀላል፡፡ ምንም ዕውቀት የሌለው ስለ ቅርስ መዝግብ ብለህ ብታሠለጥነው አይገባውም፡፡ ስለዚህ የትግራይ ክልል በየባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤቱ ያሉ ሰዎችን ማብቃት፣ አዲስና ወጣት የሚመለከታቸውን ማስገባትና ሥልጠና መስጠት፣ ተከታታይ የሆነ ሥልጠናም ለአመራሩ መሰጠት አለበት፡፡››

በተጨማሪም አቶ ተክሌ በዐውደ ጥናቱ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩበት ጉዳይ፣ በሰኔ 1992 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 209/1992 የወጣው ስለቅርስ ጥናትና አጠባበቅ የወጣውና በሥራ ላይ ያለው አዋጅ፣ የአርኪዮሎጂያዊ ተጽዕኖ ግምገማ እንዲደረግ በሚያስችል መልኩ እንዲሻሻል ምክረ ሐሳብ ማቅረባቸው ነው፡፡

በዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ መስከረም 17 ቀን 2010 ዓ.ም. በተከናወነው ኢንተርናሽናል ዐውደ ጥናት የካናዳ ሴሞን ፍራሰር ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ካተሪን አንድሪያ (ዶ/ር) ከቅድመ አክሱም ወደ ዘመነ አክሱም የተደረገውን ሽግግር ዖና ኣዲን በማሳያነት (The Pre Axumite to Axumite Transition in Eastern Tigrai Lessons from Ona Adi) አቅርበዋል፡፡ ከተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ ብሮክ ዊዴሪክ የምሥራቃዊ ትግራይ የአርኪዮሎጂ ፕሮጀክት ቅኝት፣ (Summary of the Eastern Tigray Archaeological Project Survey) እንዲሁም ከመቐለ ዩኒቨርሲቲ ገብረክርስቶስ ወልደገብርኤል የትግራይ የቅርስ ትርጓሜና አቅርቦት የውቕሮ ቱሪዝም ክላስተርን በማሳያነት (Heritage Interpretation and Presentation Practices In Tigray, Northern Ethiopia; A case of Wukro Tourism Cluster) በሚል ጥናቶቻቸውን አቅርበዋል፡፡ 

በውይይትና ጥያቄ መድረክ ከተነሱት መካከል አንዱ የኢሮብ ብሔረሰብ የተመለከተ ነው፡፡ በኢሮብ አካባቢ ብዙ ታሪክና ቅርስ በአይጋ፣ በአሊተና፣ በጉንዳጉንዶ አካባቢ እያለ ትኩረት አልተሰጠውም፣ ይጠናልን የሚል ተነስቷል፡፡ የመንግሥት አካላትም ወደፊት እናሻሽላለን ብለዋል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...