Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመገናኛ አካባቢ የተቆለለ ቆሻሻ ከፍተኛ የጤና ችግር እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ

መገናኛ አካባቢ የተቆለለ ቆሻሻ ከፍተኛ የጤና ችግር እያደረሰ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

‹‹ችግሩን ለመቅረፍ አስተዳደሩን ቦታ ጠይቀን እየተጠባበቅን ነው›› የየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምሪት አመራር

በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት መገናኛ የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ባለሥልጣን አጠገብ በመንግሥት፣ በግል ተቋማትና፣ በመኖሪያ ቤቶች መሀል ላይ የተቆለለ ቆሻሻ፣ በሠራተኞችና ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የጤና ችግር እያደረሰ መሆኑን ሠራተኞችና ነዋሪዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ የሚናገሩት እውነት መሆኑን በማረጋገጥ፣ ችግሩን ለመፍታት ተግቶ እየሠራና ለቆሻሻ መድፊያ የሚሆን ቦታ መርጦ የአስተዳደሩን ይሁንታ እየተጠባበቀ መሆኑን የወረዳ ስምንት አመራር ገልጿል፡፡

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገለጹት፣ እየደረሰባቸው ያለው የጤና ጉዳት ከፍተኛና ለሕይወታቸውም አሥጊ መሆኑን ከወረዳው አልፈው ለክፍለ ከተማው ፅዳት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አስታውቀዋል፡፡ ከቆሻሻው በሚወጣው ሽታና ብናኝ አልጋ ላይ የዋሉ ነዋሪዎች መኖራቸውን እንዲመለከቱና መፍትሔ እንዲሰጧቸው አመራሮቹን ቢጠይቋቸውም፣ ምንም ምላሽ እንዳልሰጧቸው አስረድተዋል፡፡

አቶ ገረሱ ዓለሙ የሚባሉ የአካባቢው ነዋሪ ለሪፖርተር እንደገለጹት ቆሻሻው የተከመረበት ቦታ ልጆች የሚጫወቱበት፣ አካባቢው በርካታ ቢሮዎች ያሉበት፣ በርካታ ሕዝብ የሚመላለስበት ነበር፡፡ በርካታ መሥሪያ ቤቶች በቆሻሻው ምክንያት ቢሮአቸውን ዘግተው ወደ ሌላ ሥፍራ ለውጠዋል፡፡ ነዋሪዎች ግን የሚሄዱበት ስለሌላቸውና አቤት የሚሉበት በማጣታቸው፣ ለተለያዩ ሕመሞች ተጋልጠው በአልጋ ላይ እየዋሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ታመው በሞት አፋፍ ላይ የደረሱ አዛውንቶችና በአስም የተጠቁ ወጣትና ሕፃናት በየቀኑ ቁጥራቸው እየጨመረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ቆሻሻው በተከመረበት አጠገብ በላስቲክ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ነገር ግን ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ አዛውንት ብርድና ፀሐይ የሚፈራረቅባቸው አንሶ በቆሻሻ ተከበው ለተላላፊና ተስቦ በሽታ እንዲጋለጡ ማድረግ፣ ከአንድ ኃላፊነት ከሚሰማው ሥራ አስፈጻሚ የሚጠበቅ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት፣ ቆሻሻ በየበራፉና አካባቢው ተከምሮ ተሽከርካሪዎች በየሁለትና ሦስት ቀናት ያነሱት እንደነበር አስታውሰው፣ ‹‹ለገጽታ ግንባታ ጥሩ ስለማሆን ለዓይን ዘወር ብሎ ይከማችና ይነሳል፤›› በማለት በመሥሪያ ቤትና በመኖሪያ ቤት ደጃፍ ላይ እንዲጣል መደረጉ ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ የወረዳው ኃላፊዎች ‹‹ምንም ችግር የለም በቅርብ ቀን እናነሳላችኋለን፤›› ከማለት ባለፈ ምንም መፍትሔ እንዳልሰጧቸው ጠቁመው፣ ይባስ ብለው ገንዘብ እንዲሰጧቸውና እንዲያነሱላቸው እየተደራደሯቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም የሚመለከተው የመንግሥት አካል በተለይም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ የፅዳት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ለማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ነዋሪዎቹ የሚናገሩት ሁሉ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን ወረዳውም ቢሆን ዝም ብሎ እየተመለከተ አይደለም፡፡ አንድ ሰፊ የቆሻሻ መጣያ ቦታ አግኝተው የከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ እንዲሰጣቸው እየጠበቁ መሆኑንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ቆሻሻውን እንደሚያነሱ ተናግረዋል፡፡ የቦታ ችግር እንጂ በነዋሪዎች አካባቢ ቆሻሻ ለመጣል ተፈልጎ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡ እሳቸው ወደ ቦታው ከመጡ ትንሽ ጊዜ ከመሆኑ አንፃር ብዙ ነገሮችን እያስተካከሉ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ነዋሪዎቹን በገንዘብ የሚደራደር አካል ካለ እንዳይታለሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ቆሻሻውን ማንሳት የሚቻለው እሳቸው ሲፈቅዱ ብቻ መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹እናነሳላችኋለን›› በማለት ሊያጭበረብሩ የሚመጡትን በማጋለጥ ወይም በመከልከል ራሳቸውን እንዲጠብቁ አቶ ዳዊት አሳስበዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...