ኢትዮጵያ ከመስከረም ወር ጀምሮ በፀጥታው ምክር ቤት የነበራትን የአንድ ወር የፕሬዚዳንትነት ጊዜ ለፈረንሣይ አስረከበች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የአንድ ወር ጊዜው መጠናቀቁን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ አገሪቱ በመስከረም ወር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሆና በቆየችበት ጊዜ ስድስት የውሳኔ ሐሳቦችና አንድ ፕሬዚዳንታዊ መግለጫ በምክር ቤቱ ተላልፈዋል፡፡
የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በነበረችበት መስከረም ወር በማሊ፣ በሰሜን ኮሪያ፣ በሊቢያ፣ በኮሎምቢያ፣ በሰላም ማስከበር ተልዕኮና በአይኤስ ተጠያቂነት ላይ የውሳኔ ሐሳቦች መተላለፋቸውን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ትኩረት እንዲያገኙ በለየቻቸው ጉዳዮች ላይ ሁለት ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውንም አስታውሰዋል፡፡ እነዚህም ከጳጉሜን 2 እስከ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. 15 የፀጥታው ምክር ቤት አባላት አዲስ አበባ በመምጣት ከአፍሪካ ኅብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት ጋር ያደረጉት ስብሰባ፣ እንዲሁም አገሪቱ የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዚዳንት በሆነችበት በመስከረም ወር የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮን ለማጠናከር የተካሄደው ስብሰባ እንደሆኑ ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡
ስብሰባው በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሰብሳቢነት የተካሄደ እንደነበር አስታውሰው፣ የምክር ቤቱ 15 አባላትን ጨምሮ ሌሎች በሰላም ማስከበር ተልዕኮ የሚሳተፉ አገሮች በመሪዎች ደረጃ የተገኙበትና የተመድን የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ለማጠናከር ውሳኔ የተላለፈበት እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በዚህም ኢትየጵያ የራሷን ብሔራዊ ጥቅምና የአፍሪካ ኅብረትን ፍላጎት እንዳስከበረች አስረድተዋል፡፡
አቶ መለስ አያይዘው እንደገለጹት፣ የህንድ ፕሬዚዳንት ራም ናት ኮቪንድ ረቡዕ መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሦስት ቀናት ጉብኝት አዲስ አበባ መግባታቸውን ጠቁመው፣ ጉብኝቱን ልዩ የሚያደርገው የህንድ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ሲጎበኝ ከ45 ዓመታት በኃላ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ አገሮች የጋራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ ከሰባት ዓመታት በኋላ በኅዳር ወር እንደሚካሄድ ጠቅሰው፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከህንድ ጋር ላላት ታሪካዊ ግንኙነት ብቻ ሳይሆን፣ ለወቅታዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ግንኙነትም ልዩ ቦታ ትሰጣለች፤›› ብለዋል፡፡