Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናህንድ ለኢትዮጵያ የ195 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ልታደርግ ነው

ህንድ ለኢትዮጵያ የ195 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ልታደርግ ነው

ቀን:

የህንድ ፕሬዚዳንት ራም ናት ኮቪንድ በኢትዮጵያ ባደረጉት ቆይታ፣ ከፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው ተወያይዋል፡፡ በውይይታቸው ወቅት ፕሬዚዳንቱ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ በኃይልና በትምህርት ዘርፎች ያሏትን ዕቅዶች ለማሳካት ያግዛት ዘንድ የ195 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ታደርጋለች፡፡

ፕሬዚዳንት ኮቪንድ ህንድና ኢትዮጵያ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ያላቸው አገሮች እንደሆኑ ጠቅሰው፣ ይህ ግንኙነት በአዲሱ ትውልድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁለቱም አገሮች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሙላቱ በታላቁ ቤተ መንግሥት ለህንዱ አቻቸው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፣ ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በዝግ ውይይት አድርገዋል፡፡ መሪዎቹ በዝግ ያደረጉትን ውይይት ካጠናቀቁ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሁለቱ አገሮች በሁለት ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ሁለቱ አገሮች ከዚህ በፊት የነበረውን የንግድ ሥርዓት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አዲስ የንግድ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ በኢንፎርሜሽን፣ በኮሙዩኒኬሽንና በሚዲያ በጋራ ለመሥራትም ተፈራርመዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኮቪንድ ህንዳውያን በኢትዮጵያ የአሥር ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት እንዳደረጉ ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህን ያሉት ሐሙስ መስከረም 25 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሰዓት በኃላ በሸራተን በተካሄደው የኢትዮጵያና የህንድ ቢዝነስ ፎረም ላይ ነበር፡፡

ኮቪንድ በፎረሙ ላይ እንደገለጹት 574 የህንድ ኩባያዎች በኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በጨርቃ ጨርቅ፣ በጥጥ ምርት፣ በግብርና፣ በአበባ፣ በፕላስቲክ ማምረቻ፣ በውኃ ልማት፣ በአይሲቲና ማማከር፣ በትምህርት፣ በመድኃኒትና ጤና ዘርፎች የተሠማሩ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያና ህንድ ቆየት ያለ የንግድ ግንኙነት እንዳላቸው የገለጹት ፕሬዚዳንት ኮቪንድ፣ ኢትዮጵያ ከህንድ ብረታ ብረት፣ መድኃኒቶች፣ የማሽነሪ ዕቃዎችና ሌሎች ዕቃዎችን እንደምታስገባ፣ ህንድ በበኩሏ ከኢትዮጵያ የከበሩ ድንጋዮች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ቆዳና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦችን እንደምትወስድ አስረድተዋል፡፡

ህንድ ከዚህ በፊት አንድ ቢሊዮን ዶላር በመለገስ የስኳርና የገጠር ኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፊያ ፕሮጀክቶች ተጠናቀው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረጓንም አስታውሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 460 ሚሊዮን ዶላር በመመደብም የፊንጫ፣ የወንጂ ሸዋ፣ የተንዳሆ ክፍል ሁለት ግንባታዎች ተጠናቀው ወደ ሥራ እንዲገቡ ማስቻሏን ጠቁመዋል፡፡ ለኃይል ማስተላለፊያ የሚሆን የ300 ሚሊዮን ዶላር ብድር መደረጉንና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲመጣ ማስቻሉን ፕሬዚዳንት ኮቪንድ ተናግረዋል፡፡

በፀረ ሽብር ዘመቻና በአየር ንብረት ለውጥ ህንድና ኢትዮጵያ አብረው ይሠራሉ ያሉት ኮቪንድ፣ ሁለቱ አገሮች ግንኙነት የጀመሩት በአክሱም ዘመነ መንግሥት ጊዜ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በሸራተን አዲስ በነበረው የቢዝነስ ፎረም ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ሙላቱ እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያና ህንድ ይፋዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1945 ነው፡፡ ይህ ግንኙነት ከፍ ወዳለ ደረጃ የተሸጋገረው ግን እ.ኤ.አ ከ1948 ወዲህ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች በአሁኑ ወቅት በዓመት ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የንግድ ልውውጥ እንደሚያደርጉ የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ ከፕሬዚዳንት ኮቪንድ በፊት የህንድ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን የጎበኘው ከ45 ዓመታት በፊት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ ይህ ጉብኝት በሁሉም ዘርፎች ከዚህ የተሻለ ለመሥራት እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኮቪንድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም ጋር ተገናኝተው ውይይት አድርገዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን ‹‹የህንድ ወዳጅ ናቸው፤›› ብለው፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በየጊዜው እንዲሻሻል የሚያደርጉትን ጥረት አመስግነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ኮቪንድ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን አመስግነው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ከዚህ በተሻለ  እንዲጠናከር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሠሩ ገልጸውላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መሪዎች እ.ኤ.አ. በ1956 በአፄ ኃይለ ሥላሴ፣ በ1983 እና በ1985 በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም፣ በ2007፣ በ2008 እና በ2009 በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ እንዲሁም በ2015 በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አማካይነት ህንድን ጎብኝተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሦስተኛው የህንድ አፍሪካ ጉባዔ ለመካፈል ነበር እ.ኤ.አ. በ2015 ወደ ህንድ የሄዱት፡፡

በህንድ በኩል ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1965 የህንድ ፕሬዚዳንት ራድሃ ክሪሽናን፣ በ1967 ምክትል ፕሬዚዳንት ዛኪር ሁሴንስ፣ በ1972 ፕሬዚዳንት ቪቪ ጂሪና፣ በ2011 ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንምሃን ሲን በሁለተኛው የህንድ አፍሪካ ፎረም ለመካፈል በአዲስ አበባ ተገኝተው እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...