የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ሁሌም ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ ጀምሮ ከእረፍት መልስ ሥራውን ይጀምራል፡፡ በዚህም መሠረት ሰኞ መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ጀምሮ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ ይደረጋል፡፡ ይህ ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን የሚጀምረው አምስተኛው ምክር ቤት፣ በ2007 ዓ.ም. ምርጫ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና አጋሮቹ ሙሉ በሙሉ መቀመጫዎችን ያገኙበት ነው፡፡ የአሁኑ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንደኛ ዓመት ሥራውን ከጀመረ በኋላ ወዲያው፣ በአገሪቱ ባለፉት 26 ዓመታት ታይተው የማይታወቁ ሁከቶችና ደም አፋሻስ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡ ዘርፈ ብዙ በሆኑ ጉዳዮች ላይም በርካታ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን የሚገዳደሩና የአገሪቱን ህልውናም ጥያቄ ውስጥ የከተቱ ችግሮች አሁንም እያንዣበቡ ነውና በጥሞና መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ይህ ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ይወድቃል፡፡ ምክንያቱም ከፍተኛው የሥልጣን አካል ነውና፡፡
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ መንግሥት ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ነው፡፡ ፌዴራላዊነቱ የመንግሥት ሥልጣን በማዕከልና በክልል መንግሥት ማከፋፈሉ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊነቱ በሕገ መንገግሥቱ አንቀጽ ስምንት መሠረት የሕዝብ ልዕልና ይገለጽበታል መባሉ ነው፡፡ ሪፐብሊክነቱ ሕዝብ ተወካዮቹን፣ ተወካዮቹ ደግሞ አስፈጻሚውን መግራትና መቆጣጠር ይችላሉ መባሉ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 መሠረት የምክር ቤት አባላት የመላው አገሪቱ የሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተገዥነታቸውም ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝብና ለህሊናቸው እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ተደንግጓል፡፡ ማንኛውም የምክር ቤት አባል በምክር ቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ድምፅ ወይም አስተያየት ምክንያት እንደማይከሰስ፣ ዕርምጃ እንደማይወሰድበትና የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ሲያጣበት በሕጉ መሠረት ከምክር ቤት አባልነት እንደሚወገድ በግልጽ ሰፍሯል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ባለቤት የሚሆነው ሕዝብ በውክልና የሰጠውን የሕግ አውጪነት ሥልጣን ተግባራዊ ሲያደርግ፣ አባላቱ ደግሞ የሕዝብን ውክልና መሠረት በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሲወጡ ነው፡፡ ይህ ማለት አስፈጻሚውን መንግሥት አሠራሩን ግልጽና ተጠያቂ ከማድረግም በላይ፣ ለሕዝብ ጥያቄዎች በበቂ ሁኔታ ምላሽ መስጠት መቻል ነው፡፡ የአስፈጻሚው ሥልጣን ልጓም ይበጅለት ማለት ነው፡፡
ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ ለአባላቱ የሚቀርብ መሠረታዊ ጥያቄ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ ዘመን ዴሞክራሲ የሚያስገኘው የሕዝብ ልዕልና ሕይወት አግኝቷል ወይ? በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ በክልል ምክር ቤቶች፣ በዞን፣ በወረዳ፣ በከተማ ማዘጋጃ ቤቶች፣ በቀበሌ ምክር ቤቶችና አባላት፣ ከላይ እስከ ታች ባሉ የአስተዳደር ዕርከኖች የሕዝብ ልዕልና ተዘርግቷል ወይ? በምክር ቤቶች አባላት ምርጫ በሁሉን አቀፍ፣ በእኩልና በነፃ ምርጫ በተመረጠ የሥልጣን አካል ሕዝብ ተወክሏል ወይ? የአገሪቱን ሕዝብ ብሶትና የፖለቲካ ጥያቄ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገዶች መፍታትና ውጤቱን መቀበል ተችሏል ወይ? የአስፈጻሚው አካል ጡንቻ እየፈረጠመ የምክር ቤቶች አቅም ሲፍረከረክ ኧረ አይሆንም ተብሏል ወይ? የመሳሰሉ ጥቄዎች ሲነሱ በጣም ብዙ ርቀት ወደ ኋላ ተቀርቷል፡፡ ለሕዝብ ቅሬታና ብሶት በወቅቱ ምላሽ በመጥፋቱ ቁጣዎች ገደባቸውን እየጣሱ ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለእስራትና ለአገር ሀብት ውድመት ሲያጋልጡ በግልጽ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ይህ ፈተና እንደ አዙሪት እየተደጋገመ ሲመጣና ምላሹም እዚህ ግባ ሲሆን፣ የሕዝብ ውክልና ያላቸው ምክር ቤቶችና ተወካዮች አስፈጻሚውን የመንግሥት አካል መስመር ማስያዝ ነበረባቸው፡፡ ይህንን በሕግ የተሰጠ ኃላፊነት መወጣት ባለመቻሉ ግን ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
አሁን ካለው ወቅታዊ አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ዙሪያ ገባውን ያሉ ችግሮችን የሚመረምር ማንኛውም ቅን ኢትዮጵያዊ አዕምሮ ውስጥ የሚንገዋለሉ ሐሳቦች አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው በተለይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መነሳት ያለባቸው በርካታ የሕዝብ ጥያቄዎችን የሚመለከት ነው፡፡ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገሪቱን ያተራመሷትና ሕዝቡን ደግሞ ከፍተኛ ችግር ውስጥ የከተቱት ቀውሶች፣ በአንድም ሆነ በሌላ ገጽታቸው እየቀያየሩ እየተከሰቱ ነው፡፡ በቅርቡ ለበርካታ ወገኖች ሕልፈትና ለብዙ ሺሕ ወገኖች መፈናቀል ምክንያት የሆነው በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተከሰተው ግጭት አንዱ ምሳሌ ነው፡፡ ይህ አደገኛ ድርጊት የአገር አንድነትን የሚያናጋ፣ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ሕዝብ ትስስርና ቁርኝት የሚያፋልስ፣ ቁርጠኛ የሕግና የፖለቲካ መፍትሔ ካላገኘ ለበለጠ አደጋ የሚዳርግ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን የአገር ፈተና እንዳላዩ ሆኖ ማለፍ፣ ችላ ማለት፣ ለማይረባ የፖለቲካ ፍጆታ መጠቀም፣ ወይም እንደተለመደው ማድበስበስ በታሪክ ያስጠይቃል፡፡ ይልቁንም የችግሮችን ሥረ መሠረት በሚገባ አብጠርጥሮ በመፈተሽ ሁሉንም ወገን የሚያግባባ የጋራ መፍትሔ መፈለግ የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ የማያወላዳ ምላሽ ያገኝ ዘንድ ደግሞ ፓርላማውና አባላቱ ከምንጊዜውም በላይ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ከፖለቲካ ውግንናና ከሌሎች አላስፈላጊ ትስስሮች የፀዳ ኃላፊነት፡፡ የተሸከሙት የመላ ሕዝቡን አደራ ነውና፡፡
የምክር ቤት አባላት በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠላቸው የመላው ሕዝብ ተወካዮች ናቸው፡፡ እንደተባለው ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለህሊናቸው ተገዥ መሆናቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡ ተወካዮቹ በህሊናቸው ዳኝነት የሚመሩ፣ በህሊናቸው የሚሞገቱና ህሊናቸውን የሚሞግቱ ናቸው ወይ? ተብሎ በስፋት የሚቀርብባቸውን ጥያቄ መመለስ መቻል አለባቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ኃላፊነትን የማክበር ጨዋነት ፖለቲካዊ ዝንባሌያቸውን በልጦ ይገዛቸዋል? ገለልተኝነታቸውና ለሕዝብ አደራ የመታመን ጥንካሬያቸውስ? ይህንንም በድፍረት የመመለስ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ እናገለግለዋለን ያሉትን ሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄዎቹን አንጥረው አውቀው ለመፍትሔ ከሚበጁ ሐሳቦች ጋር መቅረብ ካልቻሉ ፈተናውን ይወድቃሉ፡፡ በየደረጃው ከሕዝብ የዕለት ተዕለት ሕይወት ጋር የሚገናኘው የመንግሥት አስፈጻሚ አካልን መገሰፅና ልክ የማስገባት ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነትን አለመወጣት ያስጠይቃል፡፡ የአገር ህልውና ከመቼውም ጊዜ በላይ ሥጋት ላይ በወደቀበት በዚህ ወቅት እንደተለመደው ተሰብስቦ መተያየት አያዋጣም፡፡ ሕግ የሚከበረው በቁርጠኝነት መሥራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የአሁኑ ጊዜ አንደኛ አስቸጋሪ ፈተና ደግሞ ይኼ ነው፡፡ አስፈጻሚው ከሕግ አውጪው በላይ ሲሆን ለአገር ጠንቅ ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በክረምት ወደ መጡባቸው ሥፍራዎች በተመለሱ ጊዜ ከሕዝብ በርካታ ግብዓቶችን እንዳገኙና ራሳቸውም በአካል ተገኝተው እንደተገነዘቡ ግልጽ ነው፡፡ ሕዝብ ውስጥ ሲገባ ለማመን የሚከብዱ መረጃዎች አሉ፡፡ ማስረጃ የሚቀርብባቸው በርካታ ጉዳዮችም እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡ የተለያዩ ለአገር የሚበጁ ሐሳቦች ከመፍትሔዎቻቸው ጋርም ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ቆይታም ከበቂ በላይ ለአጀንዳ የሚሆኑ ጉዳዮች መገኘታቸው አያጠራጥርም፡፡ ከብልሹ አስተዳደር እስከ አገር ሀብት ዘረፋ፣ ከፍትሕ መጥፋት እስከ ሰብዓዊ መብቶች ረገጣ፣ ወዘተ ድረስ አርብቶና አርሶ አደሮች፣ የከተማ ነዋሪዎች፣ መምህራን፣ ነጋዴዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የመንግሥትና የግል ሠራተኞችና ከመሳሰሉት የኅብረተሰብ ክፍሎች ብዙ ብዙ የአገር መነጋገሪያ ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ጥያቄዎችን ብቻ ሳይሆን የመፍትሔ አመላካች ሐሳቦችን የቋጠሩ ናቸው፡፡ ሕዝብን ማዳመጥ የሚቻለውም በዚህ መንገድ ነው፡፡ አስፈጻሚው አካል በሚፈጥሯቸው ችግሮች ምክንያት ብቻ አገር ላይ አደጋ የሚጋርጡ ብልሹ አሠራሮች የሚወገዱትም በዚህ መሠረት ነው፡፡ የሕግ የበላይነት መሠረት ይዞ የሕዝብ ልዕልና የሚረጋገጠው እንዲህ ሰፋ አድርጎ ማሰብና ለተግባራዊነቱ በቁርጠኝነት መነሳት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ይህ ኃላፊነት ደግሞ ለፓርላማውና ለአባላቱ በሕግ የተረጋገጠ ነው፡፡ ለዚህም ነው ፓርላማው አስፈጻሚውን አካል መግራትና መቆጣጠር መቻሉን በተግባር ያረጋግጥ የሚባለው!