Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበማባበልና በልመና የተሰባሰቡት ዋሊያዎቹ ማክሰኞ ሞሮኮን ይገጥማሉ

በማባበልና በልመና የተሰባሰቡት ዋሊያዎቹ ማክሰኞ ሞሮኮን ይገጥማሉ

ቀን:

ለበርካቶች የክብርና የታላቅ አስተዋፅኦ መገለጫ ነው፡፡ ለብሔራዊ ቡድናቸው ተሠልፈው ተጋድሎ በመፈጸም የአገራቸውን ስምና ባንዲራ ማጥለቅ ለበርካታ ስፖርተኞች የሁልጊዜም ሕልምና ምኞት ነው፡፡ በተለይ በእግር ኳስና በአትሌቲክስ ዘርፍ ትልቅ ሽፋን የሚሰጠው ይኼው ገድለኝነት ነው፡፡

ከስምንት አሠርታት በላይ ባስቆጠረው የአገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ ብሔራዊ ቡድኖቹ ለስኬት የበቁበት አጋጣሚ እምብዛም ነው፡፡ ከሦስቱ አሠርታት ቆይታ በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ የተገኘው ብሔራዊ ቡድኑ (ዋሊያዎቹ) የጀመረውን የስኬት መንገድ መቀጠል እንኳን አልቻለም፡፡ እየተካሄዱ ባሉት አህጉራዊና ያለም ዋንጫ ማጣሪያዎች በተደጋጋሚ ለሽንፈት መዳረጉ ብዙ እያስተቸው ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም. ለሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በምድብ ማጣሪያ ውስጥ እየተወዳደረ የሚገኘው ብሔራዊ ቡድኑ፣ የመጀመሪያውን የምድብ ጨዋታ ከጋና ጋር አድርጎ 5ለ0 ተሸንፎ መመለሱ ይታወቃል፡፡ ሁለተኛው የምድብ ጨዋታውን በመጋቢት ወር ያካሂዳል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

በፊፋ መርሐ ግብር መሠረት ሰሞኑ የተለያዩ አገሮች የወዳጅነት ጨዋታዎች እያደረጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም የዚሁ አጋጣሚ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችላትን ዕድል ከሞሮኮ አግኝታለች፡፡ የሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኢትዮጵያን 30 ልዑካን ቡድን ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ነው ለወዳጅነት ጨዋታ ጥሪውን ያደረገለት፡፡ የሞሮኮ ቡድን ለ2017 የቻን የአፍሪካ ዋንጫ ከፊት ለፊቱ ለሚጠብቀው ማጣሪያ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ያቀደው መሆኑም ታውቋል፡፡  የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቅዳሜ መስከረም 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ካዛብላንካ ያመራ ሲሆን፣ ማክሰኞ ጥቅምት 1 ቀን ጨዋታውን ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይሁን እንጂ የዋሊያዎቹ ተጨዋቾች በአልባሳትና መሰል ቁሳቁሶች ጋር የተያያዙ ምክንያቶችን በመደርደር፣ ሞሮኮን ሊያስተናግድ የሚችል ‹‹ጥሩ አቋም ላይ አይደለንም›› በሚል ወደ ስፍራው ላለማምራት ሲያቅማሙ እንደነበር ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንደ ምንጮቹ ከሆነ፣ ቡድኑ ቀደም ሲል ለአፍሪካ አገሮች ዋንጫ (ቻን) ማጣሪያና ከሳምንት በፊት ለተመሳሳይ የወዳጅነት ጨዋታ ወደ ቦትስዋና አምርቶ በ2ለ0 ሽንፈት መመለሱ፣ ከዚያም በፊት ባጋጠመው ተደጋጋሚ ሽንፈት በተለይ በተጨዋቾቹና በአሠልጣኝ አሸናፊ በቀለ መካከል የተፈጠረው መሻከር በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ አሠልጣኝ አሸናፊ የሞሮኮውን የወዳጅነት ጨዋታ እንደ ተጨዋቾቹ ፊት ለፊት መናገር ባይፈልጉም፣ ከአንዳንድ ተጨዋቾች ጋር በነበራቸው ግንኙነት ወደ ሞሮኮ አምርተው የመጫወት ፍላጎት እንዳልነበራቸው ተነግሯል፡፡

ቡድኑ ወደ ሞሮኮ ለማምራት የሁለት ቀን ጊዜ እስኪቀረው ድረስ በካፒታል ሆቴል የነበሩት ተጨዋቾች አሥራ አንድ ብቻ እንደነበሩ፣ ከነዚያ ውስጥ ደግሞ ሦስቱ በረኞች መሆናቸው ጭምር ተወስቷል፡፡ የወዳጅነት ጨዋታው እንዲሳካ ከፍተኛውን ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ፣ ቡድኑ ወደ ካዛብላንካ ለማምራት የሰዓታት ጊዜ እስኪቀረው ድረስ ከዋና አሠልጣኙ ጋር በመሆኑ በየክፍላቸው የነበሩ ተጨዋቾችን በማባበልና በመለመን ቡድኑ እንዲሟላ ማድረጋቸውም ተነግሯል፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የዋልያዎቹ የቡድን መሪ አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ ወደ ሞሮኮ መሄድ አንፈልግም ብለው አቋም የያዙ ተጨዋቾችን፣ ምንድነው ችግራችሁ? እነሱም የያዙት እግር እናንተም የያዛችሁ እግር፣ ምን አስፈራችሁ?፤›› ማለታቸው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ተጨዋቾች ተናግረዋል፡፡ እነዚሁ ተጨዋቾች በቡድኑ ውስጥ ለተፈጠረው አለመግባባት መንስኤውን ሲገልፁ፣ ‹‹ፌዴሬሽንም ሆነ የቡድኑ አሠልጣኞች ይኼ ነው የሚባል ዕቅድ የላቸውም፡፡ በፈለጉ ጊዜና ሰዓት ተነስተው ነው የወዳጅነት ጨዋታ እንዳለ የሚናገሩት፤ በማለት አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡድን ከዘንድሮው የቻን ዋንጫ ውጭ በመሆኑና ለቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ቡድኑ ከወራት በኋላ ለሚጠበቀው ወሳኝ ጨዋታ ጊዜ ስላለው፣ አሠልጣኙም ሆነ ፌዴሬሽኑ እነዚህን የመሰሉ የወዳጅነት ጨዋታዎች ሲገኙ ዕድል መስጠት የሚገባቸው ለወጣትና ተተኪ ተጨዋቾች መሆን እንደነበረበት ተጫዋቾቹ ተናግረዋል፡፡

አንዳንድ የፌዴሬሽን አመራሮች ይኼንኑ የተጨዋቾችን አስተያየት የሚጋሩ አሉ፡፡ እንደነሱ አገላለጽ፣ ቡድኑ በምድብ ድልድሉ የመጀመሪያ ጨዋታ ያሳየው ብቃት በምድቡ ካሉት ቡደኖች አኳያ የማለፍ ተስፋው የጠበበ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህን በመሰሉ የወዳጅነት ጨዋታዎች ሙሉ ለሙሉ እንኳ ባይሆን ለተወሰኑ ተተኪ ተጨዋቾች ዕድል መስጠት ተገቢና ትክክለኛውም አካሄድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ አሠልጣኙ እዚህ ላይ ምንም ዓይነት ፍላጎት እንደሌላቸውም አክለዋል፡፡

የዋሊያዎቹ ዋና አሠልጣኝ አቶ አሸናፊ በቀለ ኃላፊነቱን በተረከቡ ማግስት ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ ግባቸው ለ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ብቻ ሳይሆን በሻምፒዮናው እስከ ሩብ ፍጻሜ መዝለቅ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...