Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርመልካም የግንባታ ሥርዓት እንዲሰፍን መፍትሔ እንካችሁ

መልካም የግንባታ ሥርዓት እንዲሰፍን መፍትሔ እንካችሁ

ቀን:

ሰሞኑን በጋዜጣ የወጡ ሁለት ማስታወቂያዎች የአርክቴክቸርን ሙያና የአርክቴክቶች ማኅበርን የማግለል አዝማሚያ እንዳላቸው በማንሳት ከሙያ ጓደኞቼ ጋር የሐሳብ ልውውጥ አድርገን ነበር፡፡ ጉዳዩ ውሎ ሲያድር ከጠባብ የሙያ ጥቅም አልፎ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ አሉታዊ ውጤት ሊያሳድር እንደሚችል ተግባብተናል፡፡

በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የተሠማሩ ባለሙያዎች በሰፊው የተካፈሉባቸው ሁለት ትልልቅ ጉባዔዎች በቅርቡ ተካሂደዋል፡፡ ጉባዔዎቹ ያተኮሩባቸው ጉዳዮችና ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ከእነዚህ ሁለት ማስታወቂያዎች ይዘት አንፃር ሲታዩ፣ ዘርፉ ያሉበትን ችግሮች ለማሻሻል ከሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይልቅ ልቅ አሠራርን መገደብ ለነገ የማይባል ዕርምጃን እንደሚሻ ያመለክታሉ፡፡ ከዚሁ ጎን ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚሊኒየም አዳራሽ በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አማካይነት የተካሄደው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማትና የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፖሊሲ ብሔራዊ ኮንፈረንስ፤ ከታኅሣሥ 13 እስከ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. በተባበሩት መንግሥታት የስብሰባ አዳራሽ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር አማካይት የተካሄደው ጉባዔና የተገባው ቃል በያዝነው 2010 ዓ.ም. ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሁም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዘርፉን ለማሻሻል በርካታ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥም ብዛት ያላቸው ሕንፃዎችና መንገዶች እንደተሠሩና እየተሠሩ እንደሚገኙ ግልጽ ነው፡፡ እንዲህ ለማንም የሚታይ ውጤት እያስገኘ ያለው ዘርፍ፣ ችግሮች ይታዩበታል ሲባል ግራ የሚያጋባ ይመስላል፡፡ በዘርፉ ውስጥ ይታያሉ የተባሉት ችግሮች በጥቅል የሚገለጹ ከመሆናቸው በቀር፣ ለችግሮቹ ማሳያ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮች ተነቅሰው ስላልቀረቡበት ጉዳዩን ሾላ በድፍኑ አሰኝቶታል፡፡

በቅርቡ በጋዜጣ ታትመው የወጡት ሁለት ማስታወቂያዎች፣ ለዘርፉ ችግሮች ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ የመጀመርያው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴምፔምበር 10 ቀን 2017 በኢትዮጵያን ሔራልድ ጋዜጣ ያወጣው ጨረታ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የፐብሊክ ሰርቪስ ሠራተኞች ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ያወጣው የፍላጎት መግለጫ ጥሪ ናቸው፡፡

የሕንፃ ግንባታ ሥራ ፕሮጀክቶች የሚከናወኑበት ሥርዓት፣ በተለይ ለመንግሥት ፕሮጀክቶች፣ ረዥም ታሪክ ያለውና በየጊዜው ማሻሻያ እየተደረገበት እስካሁን የዘለቀ ነው፡፡ ይኸውም ‘የተለምዶ’ በሚባለው ‘ዲዛይን ማድረግ፣ ጨረታ ማከናወን፣ ግንባታ ማካሄድ’ ሥርዓትን የተከተለ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት የተለያዩ አማራጭ የፕሮጀክት ማከናወኛ ሥርዓቶች በተለያዩ ያደጉ አገሮች ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን አማራጮች በአገራችን ተግባራዊ ለማድረግ ሥርዓት አልተበጀላቸውም፡፡ ስለዚህም ለ‘ተለምዶው’ አሠራር የተዘጋጁ ሰነዶችን ወይም ለሕንፃ ሥራ ያልተዘጋጁ የውጭ አገር ሰነዶችን ያለቦታቸው፣ ያለ ተገቢው ጥንቃቄ የመጠቀም አካሄድ እያቆጠቆጠ ይገኛል፡፡ ይኼ አዝማሚያ ካልተገታ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ መገመት ያስቸግራል፡፡

መደበኛ የጨረታ ሰነድ የሌለውን የፕሮጀክት ማከናወኛ ዘዴ መምረጥ ከመነሻው ስህተት ሆኖ እያለ በፍፁም አግባብነት የሌላቸውን የውል ሁኔታዎች ሰነድ አብሮ መጠቀም ከፍተኛ የሙያ ሥነ ምግባር ጉድለት ከመሆን አያልፍም፡፡ “የጨረታ መክፈቻ ዕለት ማንም ተጫራች እንዳይገኝ” የሚል አንቀጽ በየጨረታው ሰነድ ውስጥ እየሰፈረ ይገኛል፡፡ እያንዳንዱ ኃላፊ እንዳሻው በዘህ መልኩ አሠራሮችን የመጀረጅ ሚና ውስጥ ሲገባ ተደጋግሞ ይሰማል፡፡ በዚህም ሳይገታ በሥሩ የሚገኝን ‘ባለሙያ’ እኔ የምፈልገው በዚህ መንገድ እንዲሠራ ስለሆነ አስፈላጊውን ሰነድ አዘጋጅልኝ እያለ ያዛል፡፡ ‘ባለሙያው’ ደግሞ ዘርፉን የሚመሩት አካላት የተለሙትን እንደማያውቅ፣ በጉባዔዎች ላይ እንዳልተገኘ ይባስ ብሎም መሠረታዊ ዕውቀት የሌለው በሚመስል አኳኋን አድርግ የተባለውን ብቻ ይፈጽማል፡፡ በራሱ አነሳሽነትም የተሳሳተ ምክር ሲሰጥም ታይቷል፡፡

ስለችግሩ ባለሙያዎች በግለሰብ ደረጃ ምንም ያህል ቢጮሁ፣ የሙያ ማኅበራትም ምንም ያህል ቢመክሩ፣ ጠብ የሚል ነገር አልተገኘም፡፡ ችግሩን እያነሱ ዘወትር በግል ውይይት ወቅት፣ በማኅበራዊ መገናኛዎችና በማኅበራት ስብሰባዎች ላይ መሳለቅም ፋይዳ አላመጣም፡፡ በአጭሩ ስለችግሩ መናገር ብቻ ሳይሆን፣ መፍትሔውንም መጠቆም ያስፈልጋል፡፡

በእኔ አስተያየት መፍትሔው ያለው በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እጅ ነው፡፡ የመፍትሔው አካል ናቸው ብዬ የምገምታቸው ዕርምጃዎችም የሚከተሉት ናቸው፡፡

1ኛ. በጋዜጣም ሆነ በሌላ ዘዴ የሚሠራጩ የጨረታ ሰነዶችን፣ የውድድር ግብዣዎችንና የፍላጎት መግለጫዎችን እየተከታተለና ሰነዶቹን እየሰበሰበ ካሉት ፖሊሲዎችና የአሠራር መመሪያዎች አንፃር ስለይዘታቸው አጭርና ወቅታዊ ሪፖርት የሚያቀርብ ቡድን ማቋቋም፤

2ኛ. ስለ አማራጭ የፕሮጀክት ማከናወኛ ዘዴዎች ያለውን አቋም ማሳወቅ፤

3ኛ. ስለ ጨረታ ሰነዶች፣ የውድድር ግብዣዎችና የፍላጎት መግለጫዎች መሠረታዊ መረጃ የሚሰጥ ዴስክ መመሥረት፤

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሚመኝልንን ምርጥ ዓለም አቀፍ አሠራርን መተግበር ባይቻለን እንኳ በአገራችን ሁኔታ ላይ የተመሠረተ መልካም አሠራር እንዲሰፍን ካደረገልን ትልቅ ስኬት ነው፡፡

(ውሂብ ከበደ (አርክቴክት)፤ ከኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር)

***

በሙሰኞች ላይ የተጀመረው ዘመቻ ይቀጥል!

የኢትዮጵያ መንግሥት በሙሰኞች ላይ የከፈተው ዘመቻ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ብዙኃኑ የአገሪቱ ሕዝብ ያምናል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎች ከመንግሥትና ከሕዝብ የተሰጣቸውን ሥልጣን መከታ በማድረግ በአቋራጭ ያላግባብ ለመበልጸግ ሲሉ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጥፋት በማድረሳቸው ነው፡፡

ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በፈሰሰባቸው የመሠረተ ልማት አውታሮች ዝርጋት ላይ አስፈጻሚ የሆኑ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ ልማቶች በአግባቡ እንዳይገነቡ አድርገዋል፡፡ መንግሥት ማግኘት የነበረበትን ቀረጥና ግብር አሳጥተዋል፡፡ ለአንድ መሥሪያ ቤት የሚገዛውን የዕቃ ዋጋ እያጋነኑ ከነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር ማቅረብ፣ ለአንድ መሥሪያ ቤት የተገዛን አላቂ ንብረት ለውጭ አሳልፎ መሸጥና ለድርጅቱ ጥቅም እንደዋለ አስመስሎ ማቅረብ፣ በረቀቀ መንገድ የመንግሥትና የሕዝብን ሀብት ለግል ጥቅም ማዋልን የመሳሰሉ የዘርፊያ ተግባራትን ሲፈጽሙ መገኘታቸው በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ መሆን የለበትም፡፡

 በአጠቃላይ ሲታይ ጥቂት የማይባሉ ባለሥልጣናት በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ ላይ ተቀምጠው መንግሥት ያቀደውን የዕድገትና የልማት ግስጋሴ የሚገታ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ አሁንም ቢሆን አርፈው ይቀመጣሉ፣ የተጣለባቸውን ኃላፊነት ብቻ ይወጣሉ ብሎ መገመት አይቻልም፡፡ የባለሥልጣናቱ ኃላፊነት የጎደለውና ከልክ ያለፈ ራስ ወዳድነት አገርንና ሕዝብን ለውድቀት የሚዳያርግ ትግባር ነው፡፡ ተግባራቸውም  ለወጣቱ ትውልድ የመልካም ዓርአያነት የሌለው ነውረኛነት ነው፡፡

እንዲህ የሙስና ወንጀሎች ሲስፋፉ የኢሕአዴግ መንግሥት  ተገቢውን ዕርምጃ ፈጥኖ ሳይወስድ ቀርቷል፡፡ በመሆኑም ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ እስከመሆን ደርሰው ስለነበር በአሁኑ ጊዜ ሰፊ የማጽዳት ሥራ መጀመሩ የሚበረታታ ነው፡፡ አጥፊዎቹ ለፍርድ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት የማያገኙ ከሆነ ግን እንደገና ማቆጥቆጣቸው አይቀሬ ነው፡፡ በእርግጥ ዘመቻው ተጀመረ እንጂ ገና ወደፊት አልተራመደም፡፡ እስካሁን ያልተያዙት ሙሰኞችም አንገታቸውን ቀብረው ያመለጡና የሸወዱ ስለሚመስላቸው፣ አመቺ ጊዜ ሲያገኙ አጸያፊ ተግባራቸውን ከመፈጸም ወደ ኋላ አይሉም፡፡

ከመንግሥት እንደተሰማው ከሆነ፣ እስካሁን በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ ያለው በዋና ኦዲተር በተደረሰባቸው ጥፋቶች ናቸው፡፡ በዋናው ኦዲተር የማይደረስባቸው ነገር ግን በየመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች የሚታወቁ ሙሰኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለዚህ ከየአቅጣጫው ከሕዝብ ለሚቀርቡት ጥቆማዎችም መንግሥት ተገቢውን ትኩረትና ምላሽ መስጠት ይኖርበታል፡፡

በእኔ እምነት በሙሰኞች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ሁለት ውጤቶችን ማስገኘት አለበት፡፡ የመጀመርያው አጥፊዎቹን ለይቶ በሕግ ፊት ማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ እስከዛሬ ድረስ የመዘበሩትን የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ማስመለስ ነው፡፡ ከሕዝብና ከመንግሥት የተመዘበረ ሀብት የወንጀል አሮጌ የለውምና ወደ ኋላ ተመልሰን ልናጠራቸው አንሞክርም ሊባል ከቶውኑ አይገባም፡፡ ያለመሰልቸት አስፈላጊውን ዕርምጃ ሁሉ መውሰድ ተገቢ ነው ብለን አናምናለን፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የሚጠረጠሩ የናዚ ጀርመን ሰዎች እስከዛሬም ድረስ እየታደኑ ለፍርድ እየቀረቡ መሆኑን ማስታወሱ ለዚህ በቂ ምሳሌ ነው፡፡

(ጠንክር፣ ከአዲስ አበባ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...