Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቅድመ ክፍያ ካርዶችን ከማተም የተሻሉ አማራጮችን የዘነጋው ቴሌ

ከሰሞኑ የሞባይል ስልክ የቅድመ ክፍያ ካርዶች ከገበያው በመጥፋታቸው በየሚዲያው፣ ‹‹ኧረ የካርድ ያለህ›› ሲባል ከርሟል፡፡ እየተነሳ ለሚገኘው እሮሮ ምላሽ መስጠት የሚጠበቅበት ኢትዮ ቴሌኮም እንደ ካርዶቹ ሁሉ ድምፁን አጥፍቶ ቢከርምም፣ ካርድ የጠፋበትን ምክንያት አሳውቋል፡፡

በየኪዮስኩና በየመንገዱ ከሚሸጡ ነጋዴዎች የባለ5፣ የባለ10 እና የባለ15 ብር ዋጋ ያላቸው ካርዶች ብቻ እየተሸጡላቸው ተጠቃሚዎች ሲማረሩ ከርመዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ባለ25፣ ባለ50 እና ባለ100 ብር ካርዶችን ማቅረብ ተስኖት ደንበኞቹን ሲያማርር ሰንብቷል፡፡ ለተፈጠረው እጥረት አፋጣኝ መፍትሔ ሲሰጥም አልታየም፡፡ ችግሩ ከሳምንት ሳምንት ሊቀረፍ አልቻለም፡፡ የችግሩ ምንጭ ምንድን ነው? ሲባል ዘግይቶ የተነገረን፣ ካርዱን ለሚያትሙት የውጭ ኩባንያዎች የሚከፈል የውጭ ምንዛሪ በመጥፋቱ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመላው አገሪቱ የተጋረጠ ችግር በመሆኑ፣ ቴሌ የቅድመ ክፍያ ካርድ ለማቅረብ እጅ አጠረኝ ቢል አሳማኝ ምክንያት ነው፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በብርታቱ በ50 ሚሊዮን የሚቆጠሩ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ ደንበኞች አፍርቷል፡፡ ይሁንና ከሦስት አራተኛ በላይ ደንበኞቹ የቅድመ ክፍያ ካርድ ተጠቃሚዎች እንደመሆናቸው መጠን፣ ይህንን ሁሉ ደንበኛ ‹‹ምንም ላደርግ አልችልም፤›› በሚል ሰበብ አፌን በዳቦ ማለት አይቻለውም፡፡ ለካርድ ማሳተሚያ የሚሆን ዶላር ከዚህም ከዚያም ፈላልጎ እንደሚያሳትም ይታመናል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የቴሌኮም አቅራቢው ኩባንያ፣ ለቅድመ ክፍያ ካርዶች ማሳተሚያ የሚሆን ዶላር የሚያጥርበት ጊዜ ካለ ሰሞኑን የተፈጠረው ችግር ሊደገም ይችላል ማለት ነው፡፡

ከውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ እጥረት አኳያ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ሌሎች አማራጮችን መመልከት እንደሚኖርበት የታወቀ ነው፡፡ ለካርድ ማሳተሚያ የሚያውለውን የውጭ ምንዛሪ ሊያስቀር የሚችልባቸው ዕድሎች እንዳሉትም ይታመናል፡፡ የቅድመ ክፍያ የሞባይል አገልግሎት ሲጀመር አቅርቦልን ከነበረው ካርድ ጀምሮ አሁን ጥቅም ላይ እስካለው ካርድ ድረስ ባለው ሒደት ውስጥ አዝጋሚውን ለውጥ ማስታወስ ይበጃል፡፡ የቅድመ ክፍያ ካርድ አገልግሎት ሲጀመር ቴሌ ያቀርብ የነበረው የካርድ መጠን ከዛሬው ጋር ሲነፃፀር በአራት እጅ ይገዝፍ ነበር፡፡ በዚያም ላይ እያንዳንዱ የቅድመ ክፍያ ካርድ በላስቲክ ታሽጎና ተሽሞንሙኖ ለገበያ ይቀርብ ነበር፡፡

እንዲህ ባለው አኳኋን ይቀርብ የነበረውን ካርድ ለማሳተም ይወጣ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ዛሬ ላይ ስናስበው ምን ያህል ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት አይከብድም፡፡ የቀድሞው የክፍያ ካርድ መጠኑ ብቻም ሳይሆን፣ ፕላስቲክ ነክ በመሆኑም ለኅትመት የሚወጣውን ወጪ ከፍተኛ እንደሚያደርገው እንገምታለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፕላስቲኩ ካርድ በአካባቢ ብክለት ላይ ያለው ተፅዕኖም አይዘነጋም፡፡ ቆየት ብሎ ካርዱ በመጠኑ አነስ ተደርጎ ቢታተምም፣ የተፈበረከበት ጥሬ ዕቃ ግን ከቀድሞው ብዙም የተለየ አልነበረም፡፡ የዝግመተ ለውጡ ሒደት እንዲህ እያለ ተጉዞ ቀስ በቀስ ወረቀት ቀመስ እየሆነ አሁን የምንጠቀምበት ዓይነት ላይ ደርሰናል፡፡

በዚህ ሒደት ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም ለአንድ የቅድመ ክፍያ ካርድ ያወጣ የነበረው የኅትመት ወጪ እንደቀነሰለት ይታመናል፡፡ የሞባይል ስልክ ተገልጋዩ እየበዛ ሲመጣም እንደ ቀድሞው ዓይነት ካርዶች አሳትሞ ማቅረቡ አዋጭ እንደማይሆን ተረድቶ የወሰደው ዕርምጃ እሰየው የሚያስብል ነው፡፡

የአሁኖቹ ካርዶች ከቀደሙት የተሻሉ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ቢሆንም ግን ቀላል የማይባል የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ መሆናቸው አልቀረም፡፡ እነዚህን ካርዶች እዚሁ ለማሳተም የተደረገ ጥረት አለመደረጉም አነጋጋሪ ጉዳይ ነው፡፡ ለካርድ ኅትመት የሚወጣውን ወጪ ለመቀነስ አሁን የምንጠቀምባቸውን ካርዶች ከዓመታት በፊት ሊተካ ይችላል የተባለ አሠራር እንደሚዘረጋ ኢትዮ ቴሌኮም ሲናገር ቢቆይም፣ ሊተገብረው ባለመቻሉ ግን እንደ ፈጣን ሎተሪ ቁጥር እየፋቅን እንድንኖር አስገድዶናል፡፡ የቅድመ ክፍያ ካርዶችን በዲጂታል ዘዴ በመጠቀም አገልግሎት የሚሰጥበት ቴክኖሎጂ በእጁ እያለ ሳይተገብረው መቆየቱ ለምን የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

በሳምንቱ መጀመርያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የፋይናንስ አከታችነት ስትራቴጂን ዕውን ባደረገበት ወቅት እንደተሰማው፣ ኢትዮ ቴሌኮም በቀላሉ ደንበኞቹን ከባንክ ጋር በማስተሳሰር እየፋቅን የምንሞላውን ካርድ ማስቀረት የሚችልበት፣ በ‹‹ኦንላይን›› ማቅረብ የሚችልበት አሠራር አለ፡፡ በተጨማሪም የጽሑፍ መልዕክት በመላክና በሌሎችም ዘመናዊ አሠራሮች አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጉት መሠረተ  ልማት አውታሮች እያሉ ዶላር ጠፋ በሚል ሰበብ ካርድ ማሳተም አልችልም ማለት አግባብ አይደለም ተብሎ እየተተቸ ነው፡፡ ስለዚህ የቅድመ ክፍያ ካርድን የሚተካ ዘመናዊ አገልግሎት መጀመሩ የእኛንም እርካታ የሚያመጣ፣ የቴሌንም ሥራ የሚያቃልል ይሆናል፡፡ በእርግጥም ይህንን ማድረግ ይችል እንደነበር ስናስብ፣ ካርድ ውጭ እያሳተምንና እየፋቅን ገንዘብ ወደ ስልክ የምንሞላበት አሠራር ላይ ተመርኩዘን እንድንገፋ መደረጉ ለምን? ያሰኛል፡፡

ስለዚህ ኢትዮ ቴሌኮም በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ሳይሆን፣ ከዚያም በላይ ወፎች ማውረድ የሚያስችሉት ዕድሎችን ተጠቅሞ አገልግሎቱን ማዘመን፣ የውጭ ምንዛሪ ወጪን ማዳንና ካርድ አጠረ በተባለ ቁጥር የሚፈጠረውን የአገልግሎት መስተጓጎል በቀላሉ መታደግ የሚችልባቸው መንገዶች ሰፋፊ መሆናቸውን ተረድቶ ይህንኑ ይተግብር፡፡

የቅድመ ክፍያ ካርዱን በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ማካሄዱም እየተደከመበት ያለውን የፋይናንስ አካታችነት ግብ ለማሳካት የሚጫወተውን ሚና ብሎም አገራዊ ፋይዳውን የሚያጎለብት ባለውለታ ያደርገዋል፡፡ የባንክ ባለሙያዎች እንደገለጹት፣ የቅድመ ክፍያ ካርድ ተጠቃሚዎች በሙሉ የባንክ ሒሳብ እንዲኖራቸው በማገዝ ለዘመናዊው የፋይናንስ አገልግሎት አለኝታ የመሆን ግዴታም ተጥሎበታል፡፡ ለሞባይል ክፍያ ካርድ ማሳተሚያ የሚወጣው የውጭ ምንዛሪም ለሌላ የልማት ተግባር እንዲውል መንገዱን ይከፍታል፡፡  

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት