Saturday, May 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገሪቱን የፋይናንስ ተደራሽነት የሚቀይረው ስትራቴጂ አብዛኛውን ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ዕቅዶችን አካቷል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በቴሌኮምና በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማት ይፈተናል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ከወራት በፊት ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች በአትራፊነታቸው በዓለም የመጀመርያውን ደረጃ ይይዛሉ ብለው ነበር፡፡ ባለፉት 23 ዓመታት የባንክ ኢንዱስትሪውን ትርፍና ኪሳራ የሚያሳዩት ዓመታዊ ሪፖርቶች የሚመሰክሩትም በአገሪቱ የግልም ሆነ የመንግሥት ባንኮች ያለ ኪሳራ መዝለቃቸውን ብቻ ሳይሆን፣ የሚያገኙት ትርፍም ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡

የአገሪቱ ባንኮች ከሌላው ዓለም በተለየ ከፍተኛ አትራፊ የመሆናቸውን ያህል የአገልግሎት ተደራሽነታቸው ሲታይ ግን፣ እጅጉን ኋላቀር እንደሆኑም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ባንኮቹ ያላቸው አቅም ምን ያህል እንደሆነ ሲመዘንም፣ አጠቃላይ የካፒታል አቅማቸው ከ50 ቢሊዮን ብር አይበልጥም፡፡ ይህም በኬንያ ወይም በደቡብ አፍሪካ ከሚገኝ አንድ ባንክ ያነሰ አቅም እንዳላቸው አመላካች መሆኑ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ በተለይ 18ቱም ባንኮች የተናጠል አቅማቸው ሲታይ አነስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ የኢንዱስትሪው ዕድገት ከሚመዘንባቸው አንኳር ነጥቦች አንዱ በሆነው በተደራሽነት ሲሰፈሩም፣ በአፍሪካ ያላቸው ደረጃ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡

ብድር የመስጠት አቅማቸው፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው፣ ቁጠባ የማሰባሰብ ብቃታቸውና ሌሎች በዘርፉ የሚጠቀሱ አገልግሎቶች ሲነሱ፣ የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች አኳያ የሚገኙበት አቋም ይህ ነው አይባልም፡፡ የፋይናንስ ተቋማት እንቅስቃሴን ያሳድጋል፣ ዘርፈ ብዙ ለውጦችን ያመጣል ተብሎ በብሐራዊ ባንክ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ ካካተታቸው ነጥቦች መረዳት እንደሚቻለው፣ መደበኛው የፋይናንስ ዘርፍ  ያልተደረሰበትና ያልተነካ መሆኑን ነው፡፡

የዓለም ባንክ እ.ኤ.አ. በ2011 ባካሄደው የኢንተርፕራይዞች የዳሰሳ ጥናት መሠረት፣ በኢትዮጵያ ካሉ የንግድ ድርጅቶች መካከል 94.7 በመቶው በፋይናንስ ተቋማት ውስጥ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ወይም የቁጠባ ሒሳብ የነበራቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን 33 በመቶ ድርጅቶች የባንክ ብድር እንደሚፈልጉት ሊያገኙ ባለመቻላቸው፣ በሥራቸው ላይ ትልቅ እንቅፋት ፍጥሯል፡፡ በ16 በመቶው ብቻ ብድር ማግኘታቸውን የዓለም ባንክ ጥናት አስፍሯል፡፡

ብድር ያገኙት ኢንተርፕራይዞች ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀሩ ቁጥራቸው አነስተኛ ሆኗል፡፡ በሩዋንዳ 46 በመቶው ኢንተርፕራይዞች ብድር አግኝተዋል፡፡ በኬንያ 36 በመቶ፣ በታንዛኒያ 17 በመቶ ብድር ሲያገኙ፣ በኢትዮጵያ ግን 16 በመቶ ብቻ ናቸው ለዚህ የታደሉት፡፡ ይኸው ጥናት በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሦስት በመቶው ብቻ ብድር እንደሚያኙ ሲያሳይ፣ 41 በመቶ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችና 22 በመቶ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ደግሞ የፋይናንስ ተደራሽነት ችግር ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡ 88 በመቶ አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችም የብድር ጥያቄያቸው ውድቅ ተደርጎባቸዋል፡፡

የፋይናንስ አገልግሎት ለማግኘት ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ አይገባም የሚለውና እንደ መለኪያ የተቀመጠው መመዘኛ፣ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይም ብዙ እንደሚቀረው ተመልክቷል፡፡  

የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ተደራሽነት አነስተኛ ስለመሆኑ የሚያሳየው ሌላው ጉዳይ የኤሌክትሮኒክስ ባንኪንግ ተደራሽነት ነው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይልና የሞባይል ኔትወርክ መቆራረጥ ትልቁ የዚህ አገልግሎት ችግር ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው የባንኮች አገልግሎት የሚቋረጠው በኔትወርክ መቆራረጥ ምክንያት ነው፡፡ 80 በመቶው በኤሌክትሪክ በኃይል መቆራረጥ ምክንያት አገልግሎት እንደሚቋረጥ የዓለም ባንክ ጥናት አሳይቷል፡፡ የባንኮች አገልግሎት መቆራረጥ የኤቲኤምና የሽያጭ መዳረሻ ማሽኖችን በሚገባ ሥራ ላይ ለማዋልም እንቅፋት ሆኗል፡፡ ይህም የካርድ ተጠቃሚዎች የኤሌክትሮኒክስ የክፍያ መሣሪዎች ላይ ያላቸውን እምነት ሊሸረሽረው እንደሚችልም ሥጋቱን አስቀምጧል፡፡

እንዲህ ያሉት ተግዳሮቶች እንደተጠበቁ ሆነው በኢንተርኔት፣ በሞባይል፣ በኤቲኤምና በመሳሰሉት ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶች የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 የዓለም ባንክ ባወጣው የፋይናንስ መመዘኛ ጥናት (ፊንዴክስ) መሠረት፣ በሞባይል ገንዘብ የማስተላለፍ አገልግሎት የሚጠቀሙ ኢትዮጵያውያን ጎልማሶች አንድ በመቶ ብቻ ነበሩ፡፡

በ2008 ዓ.ም. ከ18ቱ ባንኮች 4.2 ሚሊዮን የክፍያ ካርዶችን ለተጠቃሚዎቻቸው እንዳሠራጩ የሚገልጸው መረጃ፣ እነዚህን ካርዶች በአግባቡ በደንበኞች ጥቅም ላይ እንዳልዋሉ የዓለም ባንክ የዳሰሳ ጥናት አሳይቷል፡፡ የክፍያ ካርድ ካላቸው መካከል 83 በመቶው በኤቲኤም ማሽኖች የማይጠቀሙ ሆነው ተገኝተዋል ብሏል፡፡ ገንዘብ የሚያወጡት በአካል ወደ ባንክ ሄደው ሲሆን፣ በአጠቃላይ የባንኮች ደንበኞች ውስጥ 9.3 በመቶው ብቻ በኤቲኤም ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የኤቲኤም አገልግሎት ከሌሎች አገሮች ጋር በንፅፅር ሲታይም፣ ከኬንያ የባንክ ደንበኞች ውስጥ 62 በመቶው በኤቲኤም ይገለገላሉ፡፡ በዛምቢያ 68 በመቶው ተመሳሳዩን አገልግሎት ይመርጣሉ፡፡

ይህንን ክፍተት ለማጥበብ ብዙ መሥራት እንደሚገባ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ገልጸው፣ ይህንን ለማምጣትም አዲሱ ስትራቴጂ ትልቁን ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡ እንደ ባንኮች ሁሉ የአገሪቱ የመድን ሽፋን ተደራሽነት እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

የመድን ዘርፉ እያደገ ቢሆንም፣ አብዛኛው ሕዝብ መደበኛ የመድን አገልግሎቶችን አያገኝም፡፡ በስትራቴጂው እንደተጠቀሰው፣ 17 መድን ሰጪ ኩባንያዎች ቢኖሩም፣ ሥርጭታቸው አነስተኛ ነው፡፡ ጠቅላላ የአረቦን ገቢያቸው ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ ያለው ድርሻ 0.44 በመቶ ብቻ ነው፡፡ 17ቱ የመድን ድርጅቶች በ2008 ዓ.ም. ከነበሯቸው 426 ቅርንጫፎች ውስጥ 54 በመቶው በአዲስ አበባ የሚገኙ በመሆናቸው አገር አቀፍ ሥርጭታቸው ውስን እንደሆነ አመላክቷል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዢው እንዳመለከቱት፣ በአገሪቱ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚታዩትን ችግሮች በማቃለል በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ ሊደርስባቸው የሚታሰቡ ግቦች ተካተዋል፡፡

ብሔራዊ ስትራቴጂውን ተግባራዊ በማድረግ ውጤት ለማስመዝገብ ከብሔራዊ ባንክ ባሻገር ሌሎች የግልና የመንግሥት ተቋማት ተሳታፊ የሚሆኑባቸው አሠራሮች ዕቅዶች የተነደፉ ሲሆን፣ ለስትራቴጂው ዋና ኃላፊነት እንዳለባቸው ከተጠቀሱት ውስጥ የገንዘብና የኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር (በአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራውን ብሔራዊ የፋይናንስ አካትችነት ምክር ቤት ያስተባብራል) የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎችም ይሳተፋሉ፡፡ ለተፈጻሚነቱም  ከብሔራዊ ምክር ቤቱ በተጓዳኝ፣ ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ዓብይ ኮሚቴ፣ የፋይናንስ አካታችነት ጽሕፈት ቤትና መሰል ተቋማት ተደራጅተዋል፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የመንግሥትም ሆነ የግል ተቋማት ግብይት ወይም ክፍያ የሚፈጽሙት በገንዘብና በቼክ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ተክለ ወልድ፣ ይህ ቀርቶ በፋይናንስ ተቋማት አማካይነት የሚካሄድ የክፍያ ሥርዓት እንደሚጀመርና በኤሌክትሮኒክስ ዘዴዎች እንደሚታገዝ አስታውቀዋል፡፡  

ይህን ለመተግበር ግን የሞባይል ኔትወርክ መሠረተ ልማትና አገልግሎቱ ጠንካራና ጥራት ያለው መሆን እንደሚጠበቅበት የጠቆሙት አቶ ተክለ ወልድ፣ የማይቆራረጥ የኤሌክትሪክ ኃይል መኖር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ እነዚህ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች የፋይናንስ ዘርፉ በሚጓዝበት ፍጥነት ልክ፣ አሊያም ቀድመው ካልተጓዙ በቀር የታሰበው ሁሉ መንገድ ሊቀር ይችላል ብለዋል፡፡

በስትራቴጂው የተቀመጡትን ግቦች ለማሳካት አዳዲስ ሕግጋት እንደሚወጡና ነባሮቹም እንደሚከለሱ ይጠበቃል፡፡ በስትራቴጂው መሠረት፣ በ2007 ዓ.ም. 22 በመቶ ጎልማሶች የባንክ ተጠቃሚ የነበሩ ሲሆን፣ ይህንን በ2012 ዓ.ም. ወደ 60 በመቶ ማድረስ ዋና ዋና ከሚባሉት የስትራቴጂው ግቦች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡

የፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማግኘት ተጠቃሚዎች ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው መሔድ የለባቸውም በሚለው መሥፈርት መሠረት፣ በ2012 80 በመቶው የአገሪቱ ጎልማሶች በዚህ ሥሌት መሠረት የፋይናንስ አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ መታቀዱን አቶ ተክለ ወልድ ይገልጻሉ፡፡ የመድን ሥራም በ2007 ዓ.ም. ከነበረበት አንድ በመቶ፣ በ2012 ዓ.ም. ወደ አምስት በመቶ እንዲደርስ ማድረግም የስትራቴጂው ግብ ነው፡፡

በእንዲህ ያለውን ተግባር ለመተግበር የመንግሥት ተቋማት በተለይ የውኃና የኤሌክትሪክ ክፍያዎች በባንክ በኩል እንዲፈጸሙ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ስትራቴጂውን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገልጸዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች