Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዘረ መል ቴክሎጂዎችን በአማራጭነት የመጠቀም ዕድል ለሴት አምራቾች እንዲመቻች ባለሙያዎች ጠየቁ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዘረ መል ቴክሎጂዎችን በአማራጭነት የመጠቀም ዕድል ለሴት አምራቾች እንዲመቻች ባለሙያዎች ጠየቁ

የአሜሪካ መንግሥት ባዘጋጀውና መስከረም 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው  ዓውደ ጥናት ወቅት ተመራማሪዎች በግብርናው መስክ የተሰማሩ ሴቶች በዘረ መል ምህንድስና (ጄኔቲካሊ ሞዲፋይድ) የተመረቱ የግብርና ቴክሎጂዎችን በአማራጭነት የመጠቀም ዕድል እንዲመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡ 

በአሜሪካ ኤምባሲና በግብርና መሥሪያ ቤት ትብብር በተዘጋጀው መድረክ ጁዲ ቻምበርስ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጽሑፍ እንዳመለከቱት፣ በርካታ አፍሪካውያን ሴቶች በሚያከውኗቸው የእርሻ ሥራዎችም ሆነ የምርት ሒደቶች ወቅት በውሳኔ ሰጭነት ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው፡፡ ለግብርና ምርታማነታቸው መሻሻል ከሚያግዙ እንደ ዘረ መል የምህድስና ውጤቶች ያሉ የባዮቴክሎጂ ውጤቶችን ለመጠቀም ሲፈልጉም በአማራጭነት ስለማይቀርብላቸው እንደሚቸገሩ ጠቅሰዋል፡፡

በዘረ መል ምህድስና ቴክኖሎጂ ስለሚመረቱ የግብርና ግብዓቶች ያለው የተዛባ አመለካከትም ብዙ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ተመራማሪዋ ቻምበርስ ይናገራሉ፡፡ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሞሎኪውላር ባዮሎጂ መስክ የሠሩት ቻምበርስ፣ ከሳይንሳዊ እውነታዎች ውጭ በሆነ አቀራረብ የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች በሰው፣ በአካባቢና በእንስሳት ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ ከሚገባው በላይ ተጋኖ በመውጣት፣ የንትርክ ርዕሰ ጉዳይ ሲሆን ይስተዋላል ይላሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ፀረ የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች አቀንቃኝ የነበሩ እንቅስቃሴዎች በአብዛኛው ሳይንሳዊ ባልሆኑ ይልቁንም ለስሜት ባደሩ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ቀስቃሽና አስፈሪ ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ እንደቆዩም ምሁሯ ይናገራሉ፡፡ የዚህ ዘመቻ አቀንቃኞች በሳይንሳዊ እውነታዎች ላይ ተመርኩዘው ስለ ዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች ጉዳትና ጥቅም ከመሟገት ይልቅ በሚያስፈራሩና እውነታውን በማያሳዩ ቅስቀሳዎች ላይ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ እንቆዩ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ‹‹አግሮ ኢኮሎጂካል ሙቭመንት›› የተባለ ዘመቻ መጀመሩን ጠቅሰው፣ ይህ ዘመቻ ምንም እንኳ በሥነ ምህዳርና በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ላይ ያጠነጠነ አካሔድ እንደሚከተል ቢያስታውቅም፣ ዘመቻው ግን በአብዛኛው የቀደመውን የፀረ ዘረ መል ምህንድስና አቀንቃኞች ግልባጭ መሆኑ በተግባር እየታየ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ ይህ ንቅናቄ በአብዛኛው በሴቶች ላይ ያተኮረና በሴቶች የሚመራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ እንደ አፍሪካ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ሴቶች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ቻምበርስ ገልጸዋል፡፡

ይህም ሲባል ግን የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች የችግር ሁሉ መፍቻ ናቸው ማለታችን አይደለም የሚሉት ቻምበርስ፣ ሳይንስ ካበረከታቸው የምርምር ውጤቶች ውስጥ በአማራጭነት ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኙ መፍትሔዎች ናቸው ይላሉ፡፡ ይህም ቢባል ቅሉ በመላው ዓለም በተፈጥሮ ምርቶች አምራቾችና በዘረ መል ውጤቶች አቅራቢ ኩባንያዎች መካከል የጥቅምና የገበያ ሽሚያ የለም ማለት እንዳልሆነም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

በዘረ መል ምርቶች ላይ ከሚነሱ የሥጋት ነጥቦች መካከል፣ ምርቶቹን በሚያመርቱና በሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ተፅዕኖ ሥር አገሮችና ሕዝቦች እንዲወድቁ ያስገድዳሉ የሚለው አንዱ ነው፡፡ የምርት አቅርቦትና ዋጋን እንዳሻቸው ለመወሰን የሚችሉበትን ዕድል ይፈጥርላቸዋል ከሚለው ባሻገር፣ የሥነ ምግባር፣ የሃይማኖትና የማኅበረሰባዊ እሴቶችና አስተሳሰቦችን ይጋፋሉ የሚሉ ትችቶችም ይሰነዘራሉ፡፡ ምንም እንኳ እነዚህ ሥጋቶች የማይናቁ ቢሆኑም፣ ሳይንሳዊ እውነታዎቹ ግን እንዲህ ያሉት ጉዳዮችም ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጡ ተመራማሪዋ ይሟገታሉ፡፡

በመሆኑም በአፍሪካ በግብርና ሥራ ላይ ለተሰማሩ ሴቶች ከሚሰጡ ድጋፎች መካከል እንዲህ ያሉ አማራጭ ቴክኖሎጂዎችም ቀርበውላቸው፣ ጥቅምና ጉዳታቸውን አመዛዝነው የመጠቀሙ ፈንታ ለሴቶች ብቻም ሳይሆን፣ የትኞቹም ማኅበረሰቦች ተጠቃሚ እንደሆኑ ዕድሉ ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያዋ ፓትሪሺያ ዛምብራኖም ተመሳሳይ ሐሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ በተለይ ቢቲ ኮተን እየተባለ በሚጠራውና ነፍሳትን የመቋቋም አቅሙ እንዲዳብር በተደረገው የዘረ መል ጥጥ ተጠቃሚ በመሆን የግብርና ምርታቸውን ያሻሻሉ፣ የኑሮ ደረጃቸውን ያሳደጉ የኮሎምቢያ፣ የቡርኪና ፋሶ እንዲሁም የሆንዱራንስ ሴቶችን በምሌነት አጣቅሰዋል፡፡

ምንም እንኳ ምሁራኑ እንዲህ ያሉትን መከራከሪያዎች ቢያቀርቡም፣ ከታዳሚዎች መካከል የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች በሥነ ምኅዳርና በብዝኃ ሕይወት ላይ ሊያሳድሩ ስለሚችሉት ተፅዕኖ ያላቸውን ሥጋቶች በመጥቀስ ጥያቄ ያቀረቡም ነበሩ፡፡ አብዛኛው የአገሪቱ ሴቶች በብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ካላቸው አስተዋጽኦ አኳያ፣ በአብዛኛው በባለቤትነት ጭምር ያላቸውን ተሳትፎ ሊነሳ እንደሚችል ሥጋታቸውን ሲገልጹ የተደመጡም ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዘረ መል ምህንድስና ውጤቶች ከፍተኛ ግብዓት የሚጠይቁ እንደመሆናቸው፣ በግብርና ዘርፍ ለተሠማሩ ሴቶች የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ምን ያህል ነው የሚሉ ጥያቄዎችም ተክሎችን ከሚያዳቅሉ ባለሙያዎች ቀርበዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ምርታማ ከሆነው መሬት ውስጥ 20 በመቶው ብቻ እንደተሸፈነ፣ 80 በመቶው ወደፊት እንዲለማና አብዛኛውን የግብርና ልማት ሥራ የሚያከናውኑትም አነስተኛ አምራቾች እንደመሆናቸው መጠን፣ የዘረ መል ቴክኖሎጂዎች በኢትዮጵያ እንዲዘወተሩ ማድረጉ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው አያመዝንም ወይ የሚሉ ጥያቄዎችም ሲሰነዝሩ ተደምጧል፡፡

እንዲህ ላሉት ጥያቄዎች ቁጥብ ምላሽ የሰጡት ጁዲ ቻምበርስ፣ የቴክሎጂዎቹ መነሻ የማዳቀል ሥራዎች በመሆናቸው በዚህ ሥራ መስክ የተሰማሩ አካላት ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ አይኖርም ብለዋል፡፡ በብዝኃ ሕይወትም ሆነ በሥነ ምኅዳር ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ እንዳይኖርም የባዮሴፍቲ ሥራዎች አስቀድመው እንደሚሠሩ ጠቅሰው፣ ቴክሎጂዎቹ ግን አማራጭ እንጂ ብቸኛ መፍትሔ ተደርገው መታየት እንደሌለባቸው አሳስበዋል፡፡

በአሜሪካ ኤምባሲ የግብርና ቆንፅላ እንዲሁም በግብርናው መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ኅብረት ተወካይ ማይክል ፍራንኮም በበኩላቸው፣ በአሜሪካ ከሚመረተው የበቆሎና የአኩሪ አተር ምርት ውስጥ 90 በመቶው በዘረ መል ምህንድስና ቴክኖሎጂ አማካይነት ተመርቶ ለተጠቃሚው እንደሚቀርብ ገልጸው፣ የቴክኖሎጂው ጠቀሜታ ዘርፈ ብዙ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የዘረ መል ምህንድስና እንቅስቃሴዎችን የአሜሪካ መንግሥት እንደሚደግፍ ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የዘረ መል ምህንድስና ቴክኖሎጂ እየተሞከረባቸው ከሚገኙ መካከል የጥጥ ምርት ይጠቀሳል፡፡ መንግሥት የጥጥ ምርት እጥረትን ለመቅረፍ የቢቲ ኮተን የተሰኘውን የጥጥ ምርት በኢትዮጵያ በሰፊው እንዲመረት ለማድረግ የቤተ ሙከራና የመስክ ጥናት በማካሄድ ወደ መጨረሻው ደረጃ እንደተቃረበ ይታወቃል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች