Wednesday, April 17, 2024

ከፍተኛውን የሥልጣን አካል የሚጠይቁ ድምፆች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

‹‹የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በክልሎች የሚታይ የዜጎች መብት ጥሰትን ለማረም የሚጫወተው ሚና ምን ያህል ነው?›› የሚለውን ጥያቄ ያነሱት የሚዲያ ባለሙያና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት አቶ ዘሪሁን ተሾመ ናቸው፡፡ አቶ ዘሪሁን ይህንን የተናገሩት በግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የ15 ዓመታት የዴሞክራሲ ጉዞውን ለመገምገም ባዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው፡፡

‹‹የፌዴራል መንግሥት ማለት የአገሪቱ ብሔራዊ ክልሎች ውህድ አካል ነው፡፡ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት በየራሳቸው የቆሙ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ ልክ ፌዴሬሽኑ ህልውናውን ከክልሎች እንደሚያገኘው እነርሱም የተናጠል ህልውናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ ነው ለጋራ ነገር በፌዴሬሽን ውስጥ በአንድነት የሚቆሙት፤›› በማለት አቶ ዘሪሁን ማብራሪያቸውን በማከል፣ ‹‹ታዲያ የፌዴራሉ ፓርላማ በክልሎች የመብት ጥሰቶች ሲከሰቱ ክልሎችን ጠርቶ መጠየቅ የለበትም ወይ?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን ያቀረቡትን ጥያቄ ለማንሳት ምክንያት የሆናቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የተለያዩ ክልሎች የተከሰቱ ግጭቶች ናቸው፡፡ በአማራ ክልል ከቅማንት የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በተነሳ ግጭት የሰው ሕይወትና ንብረት ከማጥፋቱም ባለፈ፣ ብሔር ተኮር ግጭት መነሳቱ ይታወሳል፡፡ በመቀጠል በዚሁ ክልል ከወልቃይት ጠገዴ/ፀገዴ የማንነትና የወሰን ክልል ጋር በተያያዘ በተነሳ ግጭት ተመሳሳይ ብሔር ተኮር ጥቃት መፈጸሙ፣ የሰዎች ሕይወት ማለፉና ንብረት መውደሙ አይዘነጋም፡፡

ፓርላማው ከላይ የተጠቀሰውን ውይይት ባደረገበት ወቅት ማለትም ግንቦት 2009 ዓ.ም. በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ነገሮች የተረጋጉ ቢመስልም፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሐምሌ ወር ከተነሳ በኋላ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች አለመረጋጋቶች መቀስቀሳቸውና በአሁኑ ወቅትም በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ወሰኖች አካባቢ የተቀሰቀሰ ግጭት መልኩን ቀይሮ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡

በሁለቱ ክልሎች አዋሳኞች አካባቢ የተነሳውን ግጭት መነሻ በማድረግ የሁለቱ ክልሎች ሕዝቦችን ለዘመናት የተገነባ አብሮ የመኖር እሴት በመናድ ላይ ነው፡፡ ሪፖርተር በቅርቡ ወደ ሥፍራው በመሄድ ባሰባሰበው መረጃ በሶማሌ ክልል ይኖሩ የነበሩ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ንብረታቸውንና ሀብታቸውን ተቀምተው ከክልሉ እንዲፈናቀሉ ተደርጓል፡፡ በርካቶችም ተገድለዋል፡፡ ከሶማሌ ክልልም እንዲሁ፡፡

ከፍተኛውን የሥልጣን አካል የሚጠይቁ ድምፆች

አቶ ራይስ አባ ሜጫ ይባላሉ፡፡ በ30ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆን የሦስት ልጆችም አባት ናቸው፡፡ በሐረር መጠለያ ጣቢያ ከሪፖርተር ዘጋቢ ጋር ቆይታ ያደረጉት አቶ ራይስ ከልጅነታቸው ጀምሮ በሶማሌ ክልል መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጅግጅጋን ነበር የማውቀው፡፡ ቤቴ ብዬ የምቆጥረው ጅግጅጋን ነው፡፡ አሁን ግን ሁሉንም አጣሁ፡፡ በቡድን በቡድን የመጡ ታጣቂዎች በየቤቱ እያንኳኩ የኦሮሞ ተወላጅ እንዳሉ ይጠይቁናል፤›› በማለት ከሶማሌ ክልል የማፈናቀሉ ሒደት እንዴት እንደተከናወነ ይገልጻሉ፡፡

አቶ ራይስ በሶማሌ ክልል በሆቴል ባለቤት የነበሩ ሲሆን፣ እርሳቸው በሆቴሉ እየሠሩ በነበረበት ወቅት የታጠቁ ቡድኖች ወደ መሥሪያ ቤቱ ሄደው ሚስታቸውን በማስፈራራት ያላቸውን ንብረት እንደዘረፉባቸው ይናገራሉ፡፡

በአሁኑ ወቅትም ሆቴላቸውንና አጠቃላይ ንብረታቸውን ተቀምተው (ተዘርፈው) በሐረር በሚገኝ የመጠለያ ካምፖች ውስጥ ይገኛሉ፡፡ አቶ የራይስ ታሪክ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ የበርካታ ኦሮሞዎች ታሪክን ይወክላል፡፡ በሁለቱ ክልሎች የተቀሰቀሰው የድንበር ግጭት ብሔር ተኮር መልክ ከመያዙ ባለፈም፣ ከሶማሌላንድ ኦሮሞዎች ተፈናቅለዋል፡፡

እስካሁን ባለው መረጃም ከሦስት ሺሕ በላይ ኦሮሞዎች ከሶማሌላንድ መፈናቀላቸውንም ሪፖርተር መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የአገሪቱ አንድነትን የሚፈትኑ እንደዚህ ዓይነት ግጭቶች ተፈጥረው የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት ለማስቆም እስካሁን ያደረገው ጥረት የለም፡፡

ምክር ቤቱ በክረምት የእረፍት ጊዜው ላይ ቢቆይም፣ አስቸኳይ ስብሰባዎችን መጥራት የሚችልበት ሕጋዊ አሠራር ያለው ከመሆኑም ባለፈ በዚሁ በእረፍት ወቅትም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማንሳት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቶ የነበረ መሆኑን በማስታወስ፣ ለጉዳዩ በሰጠው ትኩረት ላይ ወቀሳቸውን የሚሰነዝሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች አያሌ ናቸው፡፡

ፓርላማውን የሚጠይቁ ድምፆች

‹‹አገር የሚያናውጡ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ የክልል ምክር ቤቶችም ይሁኑ የፌዴራል ፓርላማ ፀጥ ብሎ የመመልከት ልማድ ነው ያላቸው፤›› በማለት በግንቦት 2009 ዓ.ም. በተካሄደው መድረክ ላይ የተገኙት የሕዋሓት/ኢሕአዴግ መሥራችና ጎምቱ ፖለቲከኛ አቶ ዓባይ ፀሐዬ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ዓባይ፣ ‹‹የፌዴራሉ ፓርላማ ምንድን ነው እየሆነ ያለው የሚለውን በራሱ መንገድ የማይመረምረው ለምንድን ነው?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ገዥው ፓርቲ በራሱ መንገድ ይፈትሽ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በራሱ መንገድ ይፈትሽ፣ ፓርላማው ግን በራሱ መንገድ አጣርቶ የሚመለከታቸውን አካላት ለጥያቄ መጥራት አለበት፤›› ሲሉ ሐሳባቸውን ሰጥተው ነበር፡፡

በዚሁ ተመሳሳይ ርዕስ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸውም የፓርላማውን ዳተኝነት በምሬት ይጠይቃሉ፡፡ በአምቦ ዩኒቪርሲቲ መምህር የሆኑን አቶ ሥዩም ተሾመ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ በየአካባቢው በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው የመብት ጥሰትና ግድያ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ተጠቅመው መንግሥትን ስለጠየቁ ብቻ የሆነ ነው ይላሉ፡፡

ዜጎች ለተቃውሞ አደባባይ የሚወጡትና የሥራ አድማ የሚጠሩት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 እና 42 ላይ በግልጽ የተደነገጉ ዴሞክራሲያዊ መብቶች በመሆናቸው እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡

ነገር ግን ዜጎች አደባባይ ሲወጡ የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱዋቸው ከመጠን ያለፉ የኃይል ዕርምጃ፣ የብዙዎች ሕይወትና ንብረት መጥፋቱ እንደሚያሳዝናቸው ገልጸዋል፡፡

ይህ ሁሉ የሆነው የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 55 መሠረት የተሰጣቸውን ሥልጣንና ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ስለ መፍትሔውም ሲናገሩ፣ ‹‹የምክር ቤቱ አባላት ለኢሕአዴግ መንግሥት ሳይሆን ለሕገ መንግሥቱ፣ ለሕዝቡና ለህሊናቸው ተገዥ በመሆን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ይወጡ፤›› ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡

ፓርላማውና የሕዝብ ተወካዮች በሕዝብ ጥቅም ጉዳይ ላይ ማተኮር አለባቸው የሚሉት ደግሞ የሸማቾች ጥበቃ ተሟጋች የሆኑት አቶ ገብረ መድኅን ቢረጋ ናቸው፡፡ ፓርላማው ሥራ አስፈጻሚውን በጥብቅ በመከታተል ለሠሩት ጥፋት ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ምኒሊክ ተሠራ የተባሉ የመንግሥት ሠራተኛ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየትም በተመሳሳይ ፓርላማውን ይወቅሳሉ፡፡ ‹‹ፓርላማውና የፓርላማው አባላት ሕዝቡን ወክለው እየሠሩ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የዚህ ምክንያት ደግሞ የኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነው፤›› ይላሉ፡፡

‹‹የኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔዎችን ያሳልፋል፡፡ እነዚህን ውሳኔዎች የኢሕአዴግ አባላትና የመንግሥት መዋቅሮች እንዲቀበሉ በሚገደዱበት ሥርዓት ውስጥ፣ ፓርላማውና የፓርላማው አባላት የመረጣቸውን ሕዝብ መብት ለማስከበር ይሠራሉ ብሎ መጠበቅ ዘበት ነው፤›› ይላሉ፡፡

ፓርላማው ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው ምላሽ የሰጡት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በጥቅሉ፣ ፓርላማው በክልሎች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት ሕጋዊ ድጋፍ የለውም ብለዋል፡፡

‹‹እንደፈለግን ተነስተን በክልሎች ጉዳይ ጣልቃ የምንገባበት ሕጋዊ ድጋፍ የለም፡፡ የምንከተለው ፌዴራላዊ ሥርዓት ነው፤›› ሲሉ በወቅቱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በወቅቱ ጥያቄ የቀረበው የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች ሲጣሱ ማለትም ተዘዋውሮ የመሥራትና ንብረት የማፍራት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ሲጣስ፣ ተቀውሟቸውን የመግለጽ መብታቸው ሲደፈጠጥ ፓርላማው ለምን ዝም ብሎ ያያል የሚል ነበር፡፡ ወደ ኋላ ላይ ግን አቶ አስመላሽ ከላይ የሰጡትን መልስ የሚቃረን ፓርላማውም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በክልል ጉዳዮች ላይ ጣልቃ የሚገቡበት ሦስት ሕጋዊ መንገዶች ስለመኖራቸው ገልጸዋል፡፡

ፓርላማው ከዚህ ቀደም ያጣራቸው ጉዳዮች መኖራቸውም ግልጽ ነው፡፡ ለአብነት ያህልም ከአሥራ አራት ዓመታት በፊት በጋምቤላ ክልል ተከስቶ የነበረው ግጭት በተመለከተ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚቴ አቋቁሞ ያጣራበት፣ እንዲሁም የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ በተከሰተው ግጭት የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን በላይ ኃይል ስለመጠቀማቸው በኮሚቴ የመረመረበትን ማንሳት ይቻላል፡፡

ፓርላማው ሰኞ መስረከም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. አራተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑን በይፋ ሲጀምርም፣ በእነዚህ የሕዝብ ጥያቄዎችና በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት 70 ሺሕ የሚገመቱ ወገኖች ንብረታቸውን አጥተው በተፈናቀሉበት ወቅት ነው፡፡

‹‹አንድ ፓርላማ ሊሠራው የሚችለው ወሳኝና ትልቅ ቁም ነገር እውነተኛ የሕዝብ ተወካይ መሆኑ ነው፡፡ ከላይ የተዘጋጀ ሕግን ያለምንም ተቃውሞ ማፅደቅ ብቻ ሥራው ከሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚለው ስያሜ አይገባውም፤›› ሲሉ አቶ ምኒሊክ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

(ዮናስ ዓብይ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል)

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -