ባለፉት ሁለት ቀናት በተለይ በማህበራዊ ድረ ገጾችና በተለያዩ ሚዲያዎች የመልቀቂያ ጥያቄዬን የሚመለከቱ ዜናዎች ሲወጡ ተስተውለዋል፡፡ ይህንን በሚመለከት እስካሁን ያለውን ሁኔታ በአጭሩ መግለጽ ስላስፈለገ ነው፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆኜ ተመርጫለሁ፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በመሆንም እያገለገልኩና ሳገለግልም ቆይቻለሁ፡፡ አሁን በደረስኩበት ደረጃ በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ሁኔታዎች ስላሉና ፍላጎቱም ስለሌለኝ ለመልቀቅ ድርጅቴንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጠይቄያለሁ፡፡
ድርጅቴና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁኔታውን አይተው ሕጋዊ መስመሩን ተከትሎ ጥያቄዬ ተገቢውን ምላሽ ያገኛል፡፡ ጥያቄዬ ተገቢውን ምላሽ ሲያገኝ የምክር ቤት አፈ ጉባዔነቴን ለመልቀቅ የፈለግኩባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር አስረዳለሁ፡፡ እስከዛ ድረስ ግን እንደማንኛውም የሕዝብ ኃላፊነት የምክር ቤት ሥራዬን እቀጥላለሁ፡፡ ባጭር ጊዜም ምላሽ አግኝቼ ጥያቄዬ የተሳካ ይሆናል ብዬ አምናለሁ፡፡
ጥያቄዬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔነት የመልቀቅ ቢሆንም፣ የመረጠኝን ሕዝብና ያስመረጠኝን ድርጅት ስለማከብር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነቴ እቀጥላለሁ፡፡ ከዛ ውጪም ለሕዝብ ይጠቅማል በምላቸው ሥራዎች ባለኝ ጊዜ ተሰማርቼ የማገለግል ይሆናል፡፡ ይሄው እንዲታወቅና ከዚህ ውጪ ያለው ነገር ወደፊት ጥያቄዎቹ ምላሽ ሲያገኙ በዝርዝር የሚቀርቡ መሆኑን ለመግለጽ እወዳለሁ አመሰግናለሁ፡፡