Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናለአራተኛ ጊዜ የተፈቀደውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠርጣሪዎች ተቃወሙት

ለአራተኛ ጊዜ የተፈቀደውን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተጠርጣሪዎች ተቃወሙት

ቀን:

በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከታሰሩ ከአንድ ወር በላይ የሆናቸው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ስምንት ኃላፊዎች፣ የፌዴራል ፖሊስ መርማሪ ቡድን ቀሪ የምርመራ ሥራ እንደቀረው ለፍርድ ቤት በማስረዳት የተፈቀደለትን ተጨማሪ ጊዜ ተቃወሙ፡፡

የፈዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው የምርመራ ሥራ ውጤት በተጠርጣሪዎቹ ላይ ቀሪ ምርመራ፣ የተሰበሰቡ ሰነዶችን የመተንተንና ማስተንተን፣ የምስክሮችንና የባለሙያዎችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው የተናገረ ቢሆንም፣ ተጠርጣሪዎቹ  ግን ‹‹ሆን ተብሎ ምርመራው እየተራዘመ ነው፡፡ ከመታሰራችን በፊት ማስረጃዎቹን ሰብስቦ ማጠናቀቅ ሲገባው እኛን አስሮ ማስረጃ መፈለግ መጀመር፣ የሕግ ድጋፍ የሌለውና ተገቢ ያልሆነ አሠራር ነው፤›› ብለዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ምርመራ ማካሄዱን የማይቃወሙ መሆኑን በመግለጽ፣ ሕገ መንግሥታዊ የዋስትና መብታቸው ሊከበርላቸው እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ የተጠየቀባቸው የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜን ግን እንደሚቃወሙና ሊፈቀድም እንደማይገባ አስረድተዋል፡፡

 መርማሪ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው፣ ቀድሞ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ የ30 ምስክሮችን ቃል ተቀብሏል፡፡ ከአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጪ በርካታ ሰነዶችን ሰብስቧል፡፡ ንብረቶችን በመለየትና በማሳገድ ላይ መሆኑንና ትርጉም የሚያስፈልጋቸውን ሰነዶችን የማስተርጎም ሥራ ማከናወኑን፣ የምርመራ ቡድን በማዋቀር በተለያዩ አካባቢዎች ልኮ የምርመራ ውጤት እየተጠባበቀ መሆኑን አብራርቷል፡፡

በቀጣይ የምርመራ ጊዜ የ28 ምስክሮችን ቃል መቀበል፣ 13 የኦዲት ሪፖርቶችን መቀበልና የባለሙያዎችን የሙያ አስተያየት መቀበል፣ ቀሪ በርካታ ሰነዶችን ማሰባሰብና የመለየት ሥራ ማከናወን፣ ከጂቡቲ ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ሰነዶችን ማስመጣት፣ ተጨማሪ የተጠርጣሪዎችን ንብረት ማሳገድ፣ በመስክ ሥራ ላይ ያሉ መርማሪዎችን የምርመራ ሥራዎች መቀበል እንደሚቀሩት በማስረዳት፣ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲፈቀዱለት ጠይቋል፡፡

ፍርድ ቤቱ መርማሪ ቡድኑን በእያንዳንዱ ተጠርጣሪ ላይ ምን ያህል ምስክሮች እንደተሰሙና ምን ያህል እንደቀሩ እንዲገልጽ ጠይቆት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ይኼንን ያህል ምስክር በእከሌ ላይ ለማለት በጣም አስቸጋሪ መሆኑን የገለጸው መርማሪ ቡድኑ፣ ምክንያቱ ደግሞ ሥራው ውስብስብና አንዱን ከአንዱ መለየት ስለሚያስቸግር መሆኑን ተናግሯል፡፡

ተጠርጠሪዎቹ ግን የመርማሪ ቡድኑን አሠራር ተቃውመዋል፡፡ ምርመራው ያላግባብ እየተጓተተ መሆኑንና ላለፉት ሦስት ቀጠሮዎች የሚቀርበው የምርመራ ውጤት ተመሳሳይ በመሆኑ፣ ምንም የምርመራ ሥራ እየተከናወነ አለመሆኑን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡ በየቀጠሮው የስድስት፣ የ15፣ የ30  ምስክሮችን ቃል እንደተቀበለና በቀጣይም 28 ምስክሮችን ቃል መቀበል እንደሚቀረው እየገለጸ፣ ተጨማሪ ጊዜ ለማስፈቀድ የሚያደርገው እንጂ እውነተኛ የምርመራ ሒደት ላይ የተመሠረተ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሰነድ ለመለየት፣ የኦዲት ሪፖርት ለመጠበቅ፣ ከመንግሥት ተቋማት ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ከተጠርጣሪዎች ጋር የሚያገናኘው ነገር ስለሌለ፣ እነሱን አስሮ ማቆየት ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቺፍ ኢንጂነር ዓለሙ አምባዬ ጠበቃ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጹት፣ ደንበኛቸው ከፍተኛ የሆነ የኩላሊት፣ የደም ግፊትና የስኳር ሕመምተኛ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ማስረዳታቸውን አስታውሰው፣ ‹‹ደንበኛዬ ሕይወታቸው አደጋ ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በበቂ ዋስ በውጭ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉና የቤተሰብ እንክብካቤ ቢደረግላቸው የተሻለ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ግን ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ተሰሚነት ስላላቸው በዋስ ቢወጡ ሰነዶችን የማስለወጥና የማስጠፋት፣ ምስክሮችን የማባበልና የማስፈራራት አቅም ስላላቸው ዋስትናውን እንደሚቃወም አስረድቷል፡፡ እያካሄደ ባለው የምርመራ ጊዜ ውስጥ አንድ ሠራተኛ ማስረጃ ሲደብቅ በመገኘቱ ከሥራ መታገዱንም በምሳሌነት  ጠቁሟል፡፡ ሕመምን በሚመለከት መርማሪ ቡድኑ እንደገለጸው፣ ከዕድሜ መጨመር ጋር የተለያዩ ሕመሞች ሊመጡ እንደሚችሉ ጠቁሞ፣ ተቋሙ ሕክምና መስጠት ስለሚችል እንደ ማንኛውም ታካሚ እንዲታከሙ እንደሚደረግ አስረድቷል፡፡ አስፈላጊ ከሆነም በጠየቁበትና በፈለጉበት ቦታ ሊታከሙ እንደሚችሉና ቤተሰቦቻቸው በእስረኛ አስተዳደር በኩል ቀርበው የፈለጉትን ዕርዳታ ሊያደረጉላቸው እንደሚችሉ ገልጿል፡፡

ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ መርማሪ ቡድኑ ሥራውን በትጋት እየሠራ እንዳልሆነ መረዳቱን አስታውቆ፣ ቀሪ ሥራዎቹን በትጋት በመሥራት ምርመራውን እንዲያጠናቅቅ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ከጠየቀው ቀናት ውስጥ ስምንት ቀናትን በመፍቀድ የተጠርጣሪዎቹን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጎ ለጥቅምት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...