Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከኬንያ ድንበር የተመለሰው ስኳር ለአገር ውስጥ እንዲቀርብ ሊወሰን ይችላል ተባለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወደ ኬንያ ኤክስፖርት ለማድረግ ታስቦ ሞያሌ ድንበር ደርሶ የነበረው 4,400 ቶን ስኳር፣ ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርብ ሊወሰን እንደሚችል ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተገለጸውን መጠን ስኳር አግሪኮሞዲቲስ ኤንድ ፋይናንስ ለተባለ ኩባንያ ከሸጠ በኋላ፣ ኩባንያው ወደ ኬንያ የሚገባበትን ሁኔታዎች ባለማመቻቸቱ በሞያሌ ድንበር በእርጥበታማ ሙቀት ለሁለት ወራት በተሽከርካሪዎች ላይ ለመቆየት ተገዷል፡፡

ይህንን ስኳር ኩባንያው መረከብ ባለመቻሉ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ ስኳሩን የጫኑ 110 ተሽከርካሪዎች ወደ ወንጂ ስኳር ፋብሪካ እንዲመለሱ ተወስኖ፣ በጉዞ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ስኳሩ ከተመለሰ በኋላ ምን ይሆናል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽኑ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው አይችሉም፣ የስኳሩ መጠንና ያለበት የጥራት ደረጃ ከተፈተሸ በኋላ ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርብ ሊወስን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

ግዥውን የፈጸመው ኩባንያ የፈረመው የግዥ ውል ‹‹ፋክተሪ ኤግዚት›› የኮንትራት ውል ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ምርቱ ከወንጂ ስኳር ፋብሪካ ከወጣ በኋላ የገዛበትን ዋጋ 2.2 ሚሊዮን ዶላር መክፈል ይጠበቅበት ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ኩባንያው ስኳሩ በእጁ እንዳልገባና የስኳሩን መጠን ማወቅ ባለመቻሉ ገንዘቡን እንደማይከፍል መግለጹን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ አቶ ጋሻውም ይህንኑ አረጋግጠዋል፡፡ ከዚህ አልፎም ለተሽከርካሪዎቹ የከፈለውን ግማሽ ክፍያ ኮርፖሬሽኑ እንዲከፍለው በደብዳቤ መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኩባንያው ለኢትዮጵያ መንግሥት ታዋቂ ማዳበሪያ አቅራቢ መሆኑን የገለጹት አቶ ጋሻው፣ በስኳር ኮርፖሬሽን ላይ ለደረሰው ጉዳት በሕግ ይጠየቃል ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በከተማዋ ስኳር አጥተው በመቸገራቸው፣ ኮርፖሬሽኑ የአገር ውስጥ ችግር ሳይፈታ ኤክስፖርት ለማድረግ መሞከሩ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፡፡

ኤክስፖርት የማድረግ ፍላጎቱ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች