የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ የሚያስቃኙ ግልጽነት የተላበሱ ነገሮች ሲጠፉ እስኪ እውነቱን እንነጋገር መባል አለበት፡፡ ሰኞ መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባ የፌዴራል መንግሥቱ ፕሬዚዳንት ሰፋ ያለ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ በዚህ ንግግር በርካታ ጉዳዮች እንደሚዳስሱና በወቅታዊ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ተጠብቆ ነበር፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፌዴራል መንግሥቱና በክልሎች መካከል እየታየ ያለው ግራ የገባው ግንኙነት ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ያጋጠመው አሳዛኝ ደም አፋሳሽ ግጭትና በበርካታ ሺዎች የተፈናቀሉበት ክስተት የንግግሩ ሰፊ ክፍል መሆን ሲገባው፣ በአጭሩ ቀርቦ የንግግሩ መደምደሚያ ሆኗል፡፡ ሕዝብ ሁሌም መሠረታዊ ብሎ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ተትተው ላይ ላዩን ብቻ መጓዝ ያዳግታል፡፡ እውነቱን እንነጋገር ቢባል እኮ ይኼ አንደኛው ወይም ዋነኛው የወቅቱ ጉዳይ ነበር፡፡ በአገር ላይ ሥጋት የሚፈጥር ዋነኛ ችግር በአፅንኦት መነጋገሪያ መሆን ነበረበት፡፡
እርግጥ ነው የፕሬዚዳንቱ ንግግር የአገሪቱን የአንድ ዓመት የሥራ ዕቅድና አፈጻጸም ፍኖተ ካርታ ማሳየቱ አይታበልም፡፡ ነገር ግን ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ትንታኔ ይልቅ ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ጥቅም በፍትሐዊነት እያንዳንዱ ጎጆ የመድረሱ ጉዳይ የሕዝብ መሠረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት መሻሻል ያላሳየው የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ አሁንም ብዙዎችን ያሳስባል፡፡ ፍትሕ እንደ ውኃ የጠማቸው ዜጎች እንግልትና መከራ አሁንም ብዙ የሚባልበት ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ዕውቅና የተቸረው በገዛ አገር ውስጥ ከቦታ ወደ ቦታ ተዘዋውሮ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብት የገጠመው መከራ ዛሬም መነጋገሪያ ነው፡፡ በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ አማካይ ሥፍራ ይዞ ለመነጋገርና ለመደራደር አለመቻል አሁንም መዳን ያልቻለ የአገር ሕመም ነው፡፡ ይህ ሁሉ ችግር ባለበት አገር ውስጥ ሕዝብና መንግሥት እንኳን ሊናበቡ መደማመጥ አቅቷል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዘው ገደብ የሌለበት ይመስል ያሻውን ሲያደርግ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ መሆናቸው ያከትማል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አንድምታ ነባራዊ ሁኔታዎች እየታለፉ ለሚያጋጥሙ ችግሮች የጋራ መፍትሔ መፈለግ እያቃተ ነው፡፡ ይህንን እውነታ መነጋገር ይጠቅም ነበር እንጂ አይጎዳም፡፡
ሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን በይፋ ተናግረዋል፡፡ የአገሪቱን ሕዝብ ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ይወክላል የሚባለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በድንገት ሥራ ሊለቁ መሆኑ ሲሰማ ግራ ያጋባል፡፡ እሳቸውም ኃላፊነታቸውን እንደሚለቁ ተናግረው ምክንያቱን ወደፊት እንደሚገልጹ ሲያስታወቁ ምክንያታቸው እረፍት ፍለጋ፣ ከጤና ጋር በተያያዘ፣ በሌላ የግል ጉዳይ ወይም በፖለቲካ አለመግባባት፣ ወዘተ ይሁን አይሁን አልታወቀም፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአገሪቱ ትልቁ የሥልጣን ባለቤት መሆኑ እየታወቀ፣ የኃላፊው በድንገት ሥራ ለማቆም መወሰን ምክንያቱ ለሕዝብ ወዲያውኑ ግልጽ የማይሆነው ለምንድነው? ግልጽነትና ተጠያቂነት ቢኖር እኮ ሕዝብ ለመላምቶች አይዳረግም ነበር፡፡ ሕዝብ ድራማ የሚመስሉ ነገሮች ሲበዙበት እንዴት ሆኖ ነው መንግሥትን የሚያምነው? ‹ግልጽነት ባህላችን አይደለም› እየተባለ እስከ መቼ ነው የሚዘለቀው? ሕግ አውጪው አካል ሥራ አስፈጻሚውን መቆጣጠር የሚችለው እኮ፣ ከምንም ነገር በላይ ለግልጽነት ትኩረት ሲሰጥ ነው፡፡ ይህም ትልቁ ኃላፊነቱ ነው፡፡ እውነቱን መነጋገር ይገባል፡፡
የአገሪቱ ሕገ መንግሥት የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት ደንግጓል፡፡ የግልጽነትና የተጠያቂነት መጥፋት ደግሞ ከበድ ያሉ ጉዳቶችን ሲያደርስ ቆይቷል፡፡ አሁንም ውጤቱ በስፋት ይታያል፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱን ችግር ውስጥ የሚከቱ እንከኖች ሲፈጠሩ መንስዔውን በጥልቀት ለማወቅ ከመፈለግ ይልቅ ማድበስበስ እየተመረጠ ቁስሎች ያመረቅዛሉ፡፡ የተድበሰበሱና የተዳፈኑ ችግሮች ሌላ ችግር እያስከተሉ የሰው ሕይወት ይቀጥፋሉ፡፡ መንግሥት ብዙ ጊዜ ችላ የሚላቸው ወይም የሚያጣጥላቸው ጉዳዮች በሌላ ጊዜ መልካቸውን ቀይረው ይመጣሉ፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የሕዝብና የመንግሥት አተያይ መራራቁን ነው፡፡ ባለሥልጣናት ወይም ካድሬዎች ከተጨባጭ ሁኔታዎች ርቀው ሌሎች ጉዳዮች ላይ ሲያተኩሩ ሕመሙና መድኃኒቱ አይገናኙም፡፡ ለዚህ አገር ከፌዴራል ሥርዓት ውጪ ማሰብ እንደማይቻል ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ የሚታዩትን እንከኖች ችላ ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰፊ የሆነ መድረክ ተዘጋጅቶ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ድምፃቸው መሰማት አለበት፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ችግር ገጥሞት እያለ እያበበ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ይልቁንም የፌዴራል ሥርዓቱ ሁሉን አሳታፊና የሚያግባባ ይሆን ዘንድ እውነት እውነቱን መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ ማንንም አይጎዳም፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር ከምንም ነገር በላይ የሚፈልገው ሰላም ነው፡፡ ሰላም ለማኅበራዊ ፍትሕና ብልፅግና መሠረት ነው፡፡ ይህ ሰላም የሚፈጠረው ደግሞ በጋራ መግባባት ላይ በመመሥረት ነው፡፡ የጋራ መግባባት የሚኖረው የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ወገኖች ተሳትፎ ሲጨመርበትና ሲጠናከር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ ከደመኛነት የሚያላቅቅ ሥልጡን ግንኙነት መጀመር አለበት፡፡ ለሕግ የበላይነት የሚገዛ ፖለቲከኛም ሆነ ማንኛውም ዜጋ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ የተመሠረተች ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አገር ይገነባል እንጂ፣ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ አገርን ወደ ፍርስራሽነት ለመቀየር እንቅልፍ አጥቶ ማደር የለበትም፡፡ ሥልጣንን ብቻ ማዕከል ያደረገና ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚቀናቀን ዓላማ የሚጎመራውና መደላድሉ የሚመቻችለት ግልጽነትና ተጠያቂነት በጠፉበት አገር ውስጥ ነው፡፡ በመርህ ሳይሆን በገጠመኝ የሚደረግ የፖለቲካ እንቅስቃሴም ሆነ የፖሊሲ ውሳኔ የሕዝብን የልብ ትርታ አያዳምጥም፡፡ የብዙዎቹ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ የሚመሯቸው ግለሰቦች ችግር መሠረቱ ይኼ ነው፡፡ አገርን የሚመራ መንግሥት ግን ቢያንስ ለመርህ መገዛት አለበት፡፡ ይህ መርህ የሚመነጨው ደግሞ የሕጎች ሁሉ የበላይ ከሆነው ሕገ መንግሥት ነውና፡፡ እውነቱን እንነጋገር ሲባል ይህም ማሳያ ይሆናል፡፡
ሁልጊዜ እንደምንለው የኢትዮጵያ ኩሩ ሕዝብ ከምንም በላይ የሚጨነቀው ለአገሩና ለወገኑ ነው፡፡ ይህ ኩሩ ሕዝብ በገጠመኝ ሳይሆን በመርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ የአገሩን ዕድገት እየተመኘ ዘለቄታዊ ደኅንነቷንም ማረጋገጥ እንዲሁ ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ግን የሚጎረብጡት ችግሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ያለምንም ማድበስበስና መሸፋፈን በመገላለጥ ከሕዝብ ጋር ተነጋግሮ ለመፍትሔው መትጋት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ ሁሉንም ነገር ሚስጥር ማድረግ አይቻልም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ አገር ችግር ሲጋጥማት እንኳ በፍጥነት እታች ድረስ ወርዶ መነጋገር ያለበት ከሕዝብ ጋር ብቻ ነው፡፡ ሕዝብ ሕመሙን በግልጽ ሲናገር ፈውሱን ማግኘት አለበት እንጂ፣ እባክህ ቻለው ወይም እርሳው አይባልም፡፡ አሁን በብዛት እንደሚታየው ሁሉንም ነገር የመመስጠር አባዜ ወይም እንዳላዩ ሆኖ የማለፍ አመል ቁጣ እንጂ ምሥጋና አያስገኝም፡፡ ‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ› ዓይነት ተጠያቂነት የሌለባቸው አሠራሮች ፋይዳ የላቸውም፡፡ ፋይዳ ያለው ተግባር እስኪ እውነቱን እንነጋገር ማለት ብቻ ነው!