Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሕንፃ ግንባታ ድንጋጌዎችን የጣሱ ኩባንያዎች በሕግ ሊጠየቁ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕንፃ ግንባታ አዋጅ የደነገገውን በመተላለፍ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ 23 ኩባንያዎች ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም፣ ባለማረማቸው ምክንያት በሕግ ሊጠየቁ ነው፡፡ ወደ ሕግ ከተወሰዱት መካከል የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ይገኝበታል፡፡

የሕንፃ አዋጁን ለማስፈጸም የወጡ ደንብና መመርያዎች፣ እየተገነቡ የሚገኙ ሕንፃዎች የመጠቀሚያ ፈቃድ ሳይሰጣቸው አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ይደነግጋሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የግንባታ ፈቃድ ሲወስዱ ውል ገብተው የተፈራረሙበትን አገልግሎት የቀየሩና እየቀየሩም የሚገኙ ኩባንያዎች አሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መለስ አለቃ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የመጠቀሚያ ፈቃድ ሳይኖራቸው አገልግሎት እየሰጡ ያሉና አገልግሎት የቀየሩ 172 ኩባንያዎች ተለይተዋል፡፡

‹‹ከእነዚህ ከተለዩት 172 ኩባንያዎች መካከል 90 የሚሆኑት ማስተካከያ አድርገዋል፡፡ 58 የሚሆኑት ደግሞ ማስተካከያ ለማድረግ ጊዜ ይሰጠን ብለው በማመልከታቸው ጊዜ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የተቀሩት 23 ኩባንያዎች ግን ምንም ምላሽ አልሰጡም፣›› ሲሉ አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ 23 ኩባንያዎች ሕጉን አክብረው እንዲሠሩ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ምላሽ ሊሰጡ ባለመቻላቸው፣ ጉዳዩን ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መምራታቸውን አቶ መለስ አስረድተዋል፡፡   

ከእነዚህ 23 ኩባንያዎች ውስጥ 12 የሚሆኑት ንግድ ባንኮች ናቸው፡፡ ከንግድ ባንኮች ውስጥ ደግሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝ አቶ መለስ ጠቁመዋል፡፡

በዋናነት የንግድ ባንኮቹ የሕግ ጥሰት የሚያጠነጥነው ባልተጠናቀቁ ሕንፃዎች የመጠቀሚያ ፈቃድ ሳይኖራቸው ቅርንጫፎችን መክፈት ነው፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በበርካታ ሕንፃዎች ላይ ቅርንጫፎችን ከፍቷል፡፡ የተቀሩትም 11 ባንኮች በተመሳሳይ ቅርንጫፎችን እየከፈቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ በልሁ ተክሌ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ባንኩ በተለያዩ ሕንፃዎች ቅርንጫፎች የሚከፍተው አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ነው፡፡

ከባንኮች በተጨማሪ ሕግ እየተጣሰ የሚገኘው የአገልግሎት ለውጥ በማድረግ ነው፡፡ አቶ መለስ እንደሚያስረዱት፣ በርካታ ሕንፃዎች ለተሽከርካሪ ማቆሚያ መዋል ያለበትን ቦታ ለሱፐር ማርኬትና ለምሽት ክለብ አገልግሎት መስጫዎች እያዋሉ ይገኛሉ፡፡ ይህም ሕገወጥ አሠራር ነው ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች