- ለባንኮች የብድር ጣሪያ ሊቀመጥላቸው ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብር ከሌሎች የውጭ ገንዘቦች በ15 በመቶ ቀንሶ ግብይት እንደሚፈጸምበትና ባንኮች ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፍሉት የወለድ መጠን ወደ ሰባት በመቶ ከፍ ማለቱን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከረቡዕ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውን የ15 በመቶ የምንዛሪ ለውጥ ሲያደርግ፣ ከመስከረም 2003 ዓ.ም. ወዲህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ አዲሱ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ መሠረት በአሁኑ ወቅት በባንኮች በ23.88 ብር የሚመነዘረውን ዶላር ወደ 26.96 ብር ከፍ እንዲል ያደርጋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በመስከረም 2003 ዓ.ም. የዶላር የምንዛሪ ዋጋ በ17 በመቶ ጨምሮ 16.35 ብር እንዲመነዘር ከወሰነበት ጊዜ ወዲህ እስከ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ የብር ምንዛሪ ዋጋ እንዳሁኑ በአንድ ጊዜ ይፋ የምንዛሪ ለውጥ ሳይደረግ፣ በየዕለቱ ይካሄድ በነበረ ግብይት ቀስ በቀስ እየጨመረ መጥቶ 23.88 ብር ደርሷል፡፡ በ2003 ዓ.ም. ከተደረገው የምንዛሪ ለውጥ በኋላ በ2004 ዓ.ም. አንድ ዶላር በአማካይ ሲመነዘር የቆየው በ17.211 ብር ሲሆን፣ በ2005 ዓ.ም. ደግሞ 18.32 ብር ደርሶ ነበር፡፡
አዲሱ የምንዛሪ ለውጥ ባለፉት ሰባት ዓመታት የብር የመግዛት አቅም ከ34 በመቶ በላይ መድከሙን የሚያመላክት ሆኗል፡፡ አዲሱን የምንዛሪ ለውጥ በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የምንዛሪ ለውጡ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት እየተዳከመ የመጣውን የወጪ ንግድ ለማበረታታት ነው፡፡
ለወጪ ንግዱ መቀዛቀዝ እንደ አንድ ምክንያት የሚጠቀሰው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የአገሪቱ ምርቶች በዓለም ገበያ ዋጋቸው እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ በተለይ በወጪና በገቢ ንግድ መካከል ያለውን ክፍተት ለማጥበብ የግድ የወጪ ንግዱን ማሳደግ ስለሚገባ ዕርምጃው ተወስዷል ተብሏል፡፡
የግብርና ምርት የወጪ ንግድን ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ከተያዘው ዕቅድ አንፃር ይህ ዕርምጃ ተገቢ በመሆኑ የተወሰደ እንደሆነም አቶ ተክለ ወልድ ገልጸዋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ አወት ተክኤ እንደሚሉት፣ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጡ የወጪ ንግድን በማበረታታት ጠቃሚ ነው፡፡
‹‹የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግና ኤክስፖርተሮችን ለማበረታታት የምንዛሪ ለውጡ ጠቀሜታ ይኖረዋል፤›› ያሉት አቶ አወት፣ በአገር ውስጥ ምርት የመጠቀም ልምድ ለማዳበርም እንደሚረዳ ጠቁመዋል፡፡
የመስከረም 2003 ዓ.ም. የብር ምንዛሪ ለውጥ ከተደረገ በኋላ በተከታታይ ለተገኙት የወጪ ንግድ ገቢ እመርታዎች መነሻ እንደነበር የሚታወስ መሆኑን፣ በጥቅሉ የብር የምንዛሪ ዋጋ መቀነስ የኢትዮጵያን ወጪ ንግድ ምርቶች ርካሽ በማድረግ የወጪ ንግድ ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ በዋጋ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያስችላል የሚሉ አሉ፡፡ በሌላውም ዓለም ቢሆን የምንዛሪ ለውጡ ዕርምጃ የወጪ ንግድ ተወዳዳሪነትን በመጨመር ረገድ ተመራጭ እንደሆነም ይናገራሉ፡፡
እንደ አንዳንድ ኢኮኖሚ ባለሙዎች ገለጻ ከሆነ ደግሞ የምንዛሪ ፖሊሲ ላይ በመንተራስ የሚደረግ የወጪ ንግድ እመርታ ዘላቂ አይሆንም፡፡ ይህም ሲባል የወጪ ንግዱ ከምንዛሪ ፖሊሲ ውጪ በሆነ መንገድ ለምሳሌ በዓለም አቀፍ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በመጠንና በዓይነት በመጨመር፣ ጥራት ላይ በመሥራት፣ እንዲሁም የምርታማነትን በማሻሻል በዋጋ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚገባው ያመለክታሉ፡፡ በ2003 ዓ.ም. የምንዛሪ ለውጡ ሲደረግ የመንግሥት ኃላፊዎችም የምንዛሪ ለውጥ ፖሊሲን በመጠቀም የወጪ ንግድን ማሻሻል ዘላቂ ያለመሆኑን ገልጸው እንደነበር አይዘነጋም፡፡
እንዲህ ዓይነት የገንዘብ ምንዛሪ ለውጥ ለወጪ ንግዱ ሊሰጥ ከሚችለው ጠቀሜታ ባሻገር አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረውም የሚከራከሩ አሉ፡፡ እንደ አቶ አወት ገለጻ፣ ይህም ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ የሚያስከትል ነው፡፡ አቶ ተክለ ወልድ በበኩላቸው የዋጋ ግሽበት ይከተላል ብለው አያምኑም፡፡ የገንዘብ ለውጡን ምክንያት አድርጎ የሚከሰት የዋጋ ግሽበት እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡ የዋጋ ግሽበቱን ምክንያት ያደረገ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ እንደማይኖርና የነዳጅ ዋጋ እስካሁን ባለው አሠራር እንደሚቀጥል አመልክተዋል፡፡ የግብርና ምርቱም እየጨመረ ስለሚሄድ የዋጋ ግሽበት እንደማይኖር ታሳቢ ተደርጎ የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑንም ይከራከራሉ፡፡
በሌላ በኩል እንዲህ ዓይነት የምንዛሪ ለውጥ ሲኖር አስመጪዎችን ብዙም የሚያበረታታ ላይሆን ይችላል፡፡ ይህም ዜጎች ከውጭ የሚገባውን ምርት በመተካት በአገር ውስጥ ምርት እንዲጠቀሙ ሊያበረታታ እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡ አቶ አወት እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የአገር ውስጥ ጫማን ነው፡፡ የአገር ውስጥ ጫማ በጥሩ ሁኔታ እየተመረተ ስለሆነ አሁንም ጥራቱን እየጨመረ ከሄደ ተጠቃሚው ይበዛል ይላሉ፡፡ ይህም ከውጭ የሚገባውን ጫማ መጠን እንዲቀንስ በማድረግ የአገር ውስጥ የጫማ አምራቾችን ያበረታታል ይላሉ፡፡
አቶ አወት ትልቁ ጉዳይ ግን እንዲህ ያለው የምንዛሪ ለውጥ በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ያሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር መሆኑ ነው ይላሉ፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ ትልልቅ ግንባታዎች ይገነቡበታል ተብሎ ከተያዘላቸው በጀት በላይ ወጪ እንዲጠይቁ ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም ሜጋ ለሚባሉ ፕሮጀክቶች የሚሆኑ ግብዓቶች አብዛኛዎቹ ከውጭ የሚገነቡ በመሆናቸው፣ ከዚህ በኋላ የሚፈጽሙት ግዥ ደግሞ በአዲሱ የምንዛሪ ዋጋ በመሆኑ የመገንቢያ ወጪያቸው እንደሚጨምር ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ለባንክ አስቀማጮች የሚታሰበው የወለድ ምጣኔ እስካሁን ከሚሠራበት አምስት በመቶ ወደ ሰባት በመቶ ከፍ እንዲል ተደርጓል፡፡ ይህ ውሳኔ ከገንዘብ ምንዛሪ ለውጡ ጋር የተያያዘ እንደሆነ አቶ ተክለ ወልድ ገልጸዋል፡፡ የገንዘብ ምንዛሪ ለውጡና ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፈለው የወለድ መጠን ተያያዥ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የገቢ ንግዱ በአብዛኛው ተመሠረተው በባንክ ብድር ላይ ነው፡፡ የብድር መጠኑ ከፍ እያለ ከመጣ የገቢ ንግድ እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አስቀማጮችን ለማበረታታትና፣ የባንክ ተጠቃሚዎችን ለማበራከትና የተቀማጭ ገንዘብ መጠንን ለማሳደግ እንደሚረዳ ታምኖ ተግባራዊ መሆኑ ይገለጻል፡፡
የተቀማጭ ገንዘብ የወለድ መጠን ማደግ ግን ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳለው የሚያመለክቱ አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ እንደገለጹት፣ ባንኮች ለተቀማጭ ገንዘብ የሚከፍሉት የወለድ መጠን ከፍ ባለ ቁጥር እነርሱም ለሚያበድሩት ገንዘብ የሚያስከፍሉት ወለድ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ ይህም ኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል ይላሉ፡፡ አሁን ባለው አሠራር የግል ባንኮች ለሚሰጡት ብድር እየተከፈለ ያለው የወለድ መጠን እስከ ከ12 እስከ 17 በመቶ ደርሷል፡፡ ከዚህም በላይ ብድር የሚሰጥባቸው የንግድ ዘርፎች አሉ፡፡ የተቀማጭ ወለድ ማደግ ባንኮች የሚያስከፍሉትን የብድር ወለድ መጠን ከዚህም በላይ ማሳደጋቸው ስለማይቀር፣ በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል የሚል እምነት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ በሌላ በኩል እስካሁን በነበረው የወለድ ምጣኔ ተጎጂዎች አስቀማጮች ስለሆኑ የወለድ መጠኑ ከዚህም በላይ መጨመር አለበት የሚሉ አሉ፡፡ በአስቀማጮች ጫንቃ ባንኮች ከፍተኛ ትርፍ እንንሚያገኙም ይከራከራሉ፡፡
በአሁኑ ወቅት ባንኮች የተቀማጭ የገንዘብ መጠናቸውን ለመጨመር እያደረጉ ያሉት ፉክክር ለረዥም ጊዜ ለሚቀመጥ ገንዘብ እስከ 12 በመቶ እየከፈሉ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሰሞኑን የባንኮች አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን 560 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የንግድ ባንኮች ከዚህ በኃላ ከኤክስፖርት ውጪ ላሉ ብድሮች ጣሪያ እንደሚቀመጥላቸው ታውቋል፡፡ እንደ መረጃው ከሆነ ባንኮች በሚቀመጥላቸው የብድር ጣሪያ መሠረት ብድር እንዲሰጡ ከውሳኔ ላይ የተደረሰው የወጪ ንግድን ለማበረታታት ነው ተብሏል፡፡
ማክሰኞ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለባንኮች የሥራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ ከብሔራዊ ባንክ በተሰጠ ማብራሪያ፣ ከኤክስፖርት ውጪ ላሉ ብድሮች የሚቀመጠውን የብድር ጣሪያ መጠን ምን ያህል እንደሚሆን ወደፊት የሚገልጽላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረት ለገቢ ንግድ፣ ለግብርና፣ ለኢንዱስትሪና ለመሳሰሉት ዘርፎች የሚሰጠው ብድር ከጠቅላላ ብድራቸው ምን ያህል በመቶ መያዝ እንዳለበት ብሔራዊ ባንክ ያሳውቃቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የወጪ ንግድ ብድር ግን ያለምንም ገደብ የሚሰጥ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የ15 በመቶ የብር ምንዛሪ ለውጡንና የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ መጠን አስመልክቶም ለባንኮቹ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡