Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ለህዳሴ ግድቡ መታሰቢያ የሚሆን ብሔራዊ ፓርክ ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አጠቃላይ ገጽታ የሚገልጽና በውስጡ ከቤተ መጻሕፍት ጀምሮ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ክፍሎች ያሉት መታሰቢያ ብሔራዊ ፓርክ በአዲስ አበባ ሊገነባ ነው፡፡

የህዳሴ ግድቡ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገብረ ሥላሴ ማክሰኞ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የግድቡን የ2010 በጀት ዓመት ከባለድርሻ አካላት ጋር በኢትዮጵያ ሆቴል ሲያስተዋውቁ እንደተናገሩት፣ ህዳሴ ግድቡን የሚገልጽ ብሔራዊ ፓርክ በአዲስ አበባ በቅርቡ ይገነባል፡፡

ወ/ሮ ሮማን ለፓርኩ የሚሆን ቦታ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንደፈቀደ ገልጸው፣ ‹‹በቅርብ ጊዜ የሳይት ርክክብ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

ኩዬ ፈጬ አካባቢ የሚገነባው ፓርክ በ2010 ዓ.ም. ጨረታ በማውጣት የግንባታ ሥራው እንደሚጀመር ተገልጿል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት የፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ የአካባቢ ጥበቃና የሥነ ጥበብ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ተካ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ የህዳሴ ግድቡን ዕውን ለማድረግ በ2009 ዓ.ም. ከተከናወነው ሥራ የሶማሌ ክልል ከሁሉም ክልሎች ዝቅተኛ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ ‹‹የሶማሌ ክልል ተልዕኮን በመወጣት ረገድ ከሁሉም ክልሎች ወደ ኋላ የቀረ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በመድረኩ ላይ እንደተገለጸው የህዳሴ ግድቡ ግንባታ በአሁኑ ጊዜ 60 በመቶ መድረሱን፣ በ2009 ዓ.ም. 29 ትልልቅ ሁነቶች ኅብረተሰቡን በማሳተፍ መዘጋጀታቸውን፣ ባለፉት ስድስት ዓመታትም 250 ሺሕ ሰዎች ግድቡን እንዲጎበኙ መደረጉን አቶ ሰለሞን ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በቦንድ ግዥ ባደረጉት ተሳትፎም 1.2 ቢሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡ ይኼም የዕቅዱን 74.2 በመቶ ማሳካት እንደቻለ፣ ከዚህ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት የመንግሥትና የግል ሠራተኞች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡ ከዳያስፖራውም እስካሁን ከ42 ሚሊዮን ዶላር በላይ ድጋፍ እንደተገኘ ገልጸዋል፡፡

ከቦንድ ተሳትፎ አንፃር ባለሀብቶች ቃል የገቡትን ከመፈጸም አኳያ፣ አርሶ አደሩን በማሳተፍ፣ እንዲሁም በውጭ የዳያስፖራው ተሳትፎ በተለያዩ ምክንያቶች በተፈለገው መንገድ እየተከናወነ አለመሆኑን ግን አቶ ሰለሞን አስታውቀዋል፡፡

ከ2008 እስከ 2009 ዓ.ም. የህዳሴ ግድቡ ዋንጫ በኦሮሚያ ክልል በነበረው ቆይታ 607 ሚሊዮን ብር በቦንድ ግዥና በልገሳ መገኘቱን ገልጸዋል፡፡ በተመሳሳይ ዋንጫው በደቡብ ክልል በነበረው ቆይታ ከ968 ሚሊዮን ብር በላይ በቦንድ ግዥና  በልገሳ መገኘቱን አክለዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎችን በተመለከተ በ2009 ዓ.ም. በአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ሰፊ የአፈርና የውኃ ጥበቃ እንደተሠራ አቶ ሰለሞን ጠቁመው፣ 23.85 ቢሊዮን ብር የሚገመት ገንዘብ ከ19 ሚሊዮን በላይ የሰው ኃይል በጉልበት ባደረገው አስተዋጽኦ መገኘቱንም አስረድተዋል፡፡

ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ የተደረገው የጉልበት ተሳትፎ 79 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት አስረድተዋል፡፡ በትግራይ፣ በደቡብ፣ በቤንሻንጉል፣ በአማራ፣ በሐረሪ፣ በኦሮሚያና በድሬዳዋ ክልሎች ሰፊ የአፈርና የውኃ ጥበቃ ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡ እስካሁን ድረስ የባለሀብቱ ተሳትፎ በተመለከተ በድርጅት ከፍተኛው 500 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ 30 ሚሊዮን ብር ሆኖ መመዝገቡንም ገልጸዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ዋንጫ በየክልሉ ሲዘዋወር የፀጥታ ችግር እንዳልገጠመ የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አሁንም እንደቀጠለ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጽሕፈት ቤቱ በ2010 የበጀት ዓመትም በየደረጃው ያለው አመራር ዕቅድንና ዲሲፕሊን መሠረት ያደረገ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግና ከክልሎች ጋር በመሥራት የተሻለ ሥራ ለማከናወን ማቀዱም ተገልጿል፡፡ ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግም የተለያዩ ሥጋቶች እንዳሉ ግን ተጠቁሟል፡፡ ከእነዚህ መካከልም በገንዘብ ተቋማት የቦንድ ወለድ ለሚጠይቁና ጊዜው የደረሰ ቦንድ ለማስተናገድ በበቂ ሁኔታ ዝግጁ ሆነው ያለመገኘት፣ ከኅብረተሰቡ የሚገኘው የቦንድ ግዥና ድጋፍ ቃል በተገባው መሠረት በወቅቱና በጊዜው ያለመሰብሰብ፣ ባንኮችና ማይክሮ ፋይናንሶች የቦንድ ሰርተፍኬት አልፎ አልፎ በወቅቱ ያለመስጠት፣ አማራጭ የሀብት ምንጮችን ለመጠቀም የሚያጋጥሙ የአሠራርና የሕግ ማዕቀፍ ችግሮች፣ ክልሎችም በዚህ ረገድ ያላቸው ተሳትፎ ቀዝቃዛ መሆኑና ግብፅና መሰል ኃይሎች የግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ጥረት ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በ2010 ዓ.ም. በዋናነት የሚከናወኑ ተግባራትም የሙዚቃ ኮንሰርት፣ የሥነ ጽሑፍ ምሽት፣ የህዳሴ ንባብና ሌሎች እንደሚገኙበት በመድረኩ ተጠቁሟል፡፡

ተሳታፊዎች በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄና አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡ ከእነዚህ መካከልም ግድቡ በደለል እንዳይሞላና የውኃ መጠኑ እንዳይቀንስ በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋው የእንቦጭ አረም ላይ ለምን ትኩረት አልተደረገም? ቦንድ ገዝተው አምስት ዓመት የሞላቸው ግለሰቦች ገንዘባቸውን እንዲወስዱ ከመፍቀድ ይልቅ ለምን እንደገና ለአምስት ዓመታት እንዲያራዝሙ አይጠየቁም? የዳያስፖራ ማኅበር ለምን በህዳሴ ግድቡ ተሳትፎ አልተካተተም? ግድቡ ከታቀደው ጊዜ በላይ ለምን ተጓተተ? ቃል የገቡ ባለሀብቶች በቃላቸው መሠረት ለምን መክፈል አልቻሉም? መቶ ቢሊዮን ሕዝብ ባለባት አገር ግድቡን 39 ሺሕ ሕዝብ ብቻ እንዲጎበኘው ለምን ተደረገ? ወዘተ የመሳሰሉ ጥያቄዎች ተነስተዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ለጥያቄዎቹ መልስ ሲሰጡ፣ ‹‹የህዳሴ ግድቡ ረዥም ዓመታት ሊኖር የሚችለው በደለል እንዳይሞላ ጥንቃቄ ሲደረግና በጣና ሐይቅ ላይ ያለውን እንቦጭ በጋራ ስንከላከል ነው፡፡ ይኼን ለማድረግም ጽሕፈት ቤታችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ይሠራል፤›› ብለዋል፡፡

ቦንድ ከገዙ አምስት ዓመት የሞላቸው ግለሰቦችን በተመለከተ ደግሞ፣ ‹‹እኛ እያሰብን ያለነው የተለየ ችግር ከሌለ በስተቀር ቦንድ የገዙና አምስት ዓመት የሞላቸው ግለሰቦች እንደገና አምስት ዓመት እንዲያራዝሙ ማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ይኼ የሚሆነው ግን ቦንድ ከገዛው ግለሰብ ጋር በመወያየትና ሲያምንበት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከታቀደው በላይ ለምን ጊዜ ወሰደ ለተባለውም፣ ‹‹ሁላችንም ቤት ስንሠራ ባቀድነው ጊዜ ላይጠናቀቅ ይችላል፡፡ ፕሮጀክቱ ግዙፍ ስለሆነና በጥንቃቄ መከናወን ስላለበት ነው፡፡ ሲጀመር ግድቡ በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል አልተባለም፤›› ብለዋል፡፡ የግድቡ ግንባታ እንደቆመ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እየተወራ መሆኑን ጠቁመው፣ ‹‹እኛ ቆመ፣ አልቆመም የሚል ምላሽ አልሰጠንም፡፡ ሂዱና እዩት ነው ያልነው፡፡ ጉባ አሁንም 24 ሰዓት ሥራ አለ፤›› በማለት አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች