Friday, June 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ ድህነት ቢቀንስም የኑሮ ልዩነት እየጨመረ መምጣቱን የመንግሥት ጥናት ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሐረሪ ድሬዳዋና አዲስ አበባ ከአገሪቱ ዝቅተኛ የድህነት መጠን የታየባቸው ሆነዋል

ባለፈው ዓመት በተካሔደ የድህነት ትንተና ጥናት መሠረት በ2008 ዓ.ም. በአገሪቱ የነበረው አጠቃላይ የድህነት መጠን 23.5 በመቶ (ከ94 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ በድህነት ውስጥ የሚገኘው) እንደነበር በማሳየት ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው የ29.6 በመቶ ይልቅ የስድስት በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ሆኖም ግን በሀብታምና በድሃው ብቻም ሳይሆን፣ በድሆች መካከልም የኑሮና የገቢ ልዩነቱ እየሰፋ መምጣቱን ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡ የምግብ ድህነትን በተመለከተም በአጠቃላይ የከ33.6 በመቶ ወደ 24.8 በመቶ መቀነሱ ይፋ ተደርጓል፡፡

ብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የተሠራው አምስተኛው የድህነት ትንተና ጥናት የቅድመ ማጠናቀቂያ ሪፖርት መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ በተደረገበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ጥናቱ 30255 የቤተሰብ አባወራዎችንና እማወራዎችን ያካተተ ነው፡፡ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው አደም (ዶ/ር) እንዳስታወቁት፣ የድህነት ትንተና ጥናት ማካሄድ ያስፈለገው ከደርግ መንግሥት መውደቅ በኋላ የተወሰዱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎች የሕዝቡን በተለይም የድሃውን ክፍል ምን ያህል ጉዳት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ለመረዳትና ተገቢውን የፖሊሲ ማስተካከያ ለማድረግ እንደሆነ ነው፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያው ጥናት በ1987 ዓ.ም. ከተደረገ ጀምሮ በየአምስት ዓመቱ ሲካሄደ የቆየው ይህ ጥናት፣ ባለፈው ዓመትም በአገሪቱ ክፍሎች ሁሉንም ሕዝብ ሊወክሉ የሚችሉ የቤሰተብ ናሙናዎች መካተታቸውን አስረድተዋል፡፡

የትንተና ጥናቱን በአማካሪነት የመሩትና ትንታውን የሠሩት የኢኮኖሚ ባለሙያና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ጣሰው ወልደሃና  (ፕሮፌሰር) እንዳስታወቁት፣ በአገሪቱ የታየው የድህነት ቅነሳ በምግብና ምግብ ነክ ባልሆኑ የፍጆታ ወጪዎች ላይ ተመርሥቶ በተደረገ ጥናት የተረጋገጠ ነው፡፡

በመሆኑም በገጠር የታየው አጠቃላይ የድህነት መጠን ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረው የ30.4 በመቶ፣ ባለፈው ዓመት ወደ 25.6 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ በገጠር የተመዘገበው የምግብ ድህነት መጠንም ከ34.7 በመቶ ወደ 27 በመቶ መቀነሱን ይጠቅሳል፡፡ በከተሞች የተመዘገበው አጠቃላይ ድህነትም ወደ 14 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት በተደረገው ጥናት መሠረት ግን አጠቃላይ የድህነት መጠን 26 በመቶ ገደማ እንደነበር ጥናቱ አስታውሷል፡፡ ከከተማ ነዋሪዎች አጠቃላይ የተመዘገበው የምግብ ድህነትም ወደ 15 በመቶ ሲንቀስ ከአምስት ዓመት በፊት ግን 28 በመቶ እንደነበር ታውቋል፡፡ የድህነት ትንተናው ውጤት በጥቅሉ የሚያሳየው ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ 5.3 ሚሊዮን ሰዎች ከድህነት መውጣታቸውን እንደሆነ ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ 

የቤተሰብ የገቢና የፍጆታ ወጪ ላይ ያጠነጠነውን የናሙና ጥናት በመተንተን ያብራሩት አቶ ጣሰው፣ በፍጆታ ላይ የተመሠረተው የድህነት ትንተና ጥናት በኑሮ ደረጃ ወይም በነፍስ ወከፍ የፍጆታ አለመጣጠን ረገድ ከአምስት ዓመታት ወዲህ ወደ 33 በመቶ ከፍ ማለቱን አሳይተዋል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የነበረው የነፍስ ወከፍ የፍጆታ ወጪ የልዩነት ምጣኔ 30 በመቶ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲጨምር፣ የኑሮ ልዩነትም እንደሚጨምር በኢኮኖሚ ሙያ ዘርፍ የሚጠቀሰውን ኩዝኔት የተሰኘውን የትንታኔ ቀመር በማጣቀስ፣ በኢትዮጵያ እየታየ የመጣው የኑሮ ልዩነት በከተማና በገጠር አካባቢዎች በመሆኑ በተለይ በገጠር ለሚኖረው ሕዝብ አማራጭ የገቢ ምንጮችን በመፍጠር የድህነት መጠኑን መቀነስ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. ወዲህ በከተማ የሚታየው የድህነት መጠን እየቀሰነ ለመምጣቱ ተጠቃሽ የተደረገው መንግሥት የቤት ልማት ፕሮግራሞችን ጨምሮ፣ መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች ላይ ድጎማ ማደረጉ፣ በከተማው ክፍል የታየው ልዩ ልዩ የመሠረተ ልማት ግንባታ ያሳየው ዕድገት የፈጠራቸው ዕድሎችን ያብራሩት አቶ ጣሰው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም መጀመሩም ለከተማ የድህነት መቀነስ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ አብራርተዋል፡፡ በገጠር ደረጃም ቢሆን የተከናወኑ ድሃ ተኮር የልማት ፕሮግራሞች፣ በድርቅ ወቅት የሚደረጉ አስቸኳይ የምግብ ድጋፎች፣ የምግብ ለሥራ ፕሮግራሞችና ሌሎችም ለድህት ቅነሳ ያገዙ የመንግሥት እንቅስቃሴዎች እንደሆኑ ተጠቅሰዋል፡፡ 

ምክትል ኮሚሽነር ጌታቸው በበኩላቸው፣ በአገሪቱ የታየው የኑሮ ልዩነት በድሃ ቤተሰቦችና በኢኮኖሚ ደረጃቸው ደህና ከሚባሉት ሕዝቦች አኳያ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ያስገኛቸውን ጥቅሞች በእኩል የመጋራት ድርሻውን አነስተኛ አድርጎታል ብለዋል፡፡ ስለሆነም በአገሪቱ የታየው የኑሮ ልዩነት በጊዜ ሒደት እየተባባሰ ከመምጣቱ በፊት፣ እንዲሁም የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ልማት ወደኋላ ከመጎተቱ በፊት ትኩረት ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ይህም ሆኖ የአገሪቱ የነፍስ ወከፍ ገቢ (አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ለጠቅላላው ሕዝብ ሲካፈል የሚገኘው አኃዝ) በ2008 ዓ.ም.  የተመዘገበው መጠን 793 ዶላር እንደነበርና በ2009 ዓ.ም. ግን ከ890 ዶላር በላይ መድረሱን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቅሰው፣ ይህ አኃዝ ከሰባት ዓመት በፊት የነበረው የነፍስ ወከፍ ገቢ መጠን 377 ዶላር እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለም፣ በአገሪቱ ከሚገኙ ክልሎችና ከተሞች ውስጥ ዝቅተኛ የድህነት መጠን ያስመዘገቡት የሐረሪ ክልል፣ የድሬዳና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደሮች መሆናቸውን ፕሮፌሰር ጣሰው ባረቀቡት የቅደመ ማጠናቀቂያ የጥናት ሪፖርት አመላክተዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም. ከተመዘገው አጠቃላይ የድህነት መጠን ውስጥ የሐረሪ ክልል ያስመዘገበው የድህነት መጠን የ7.1 በመቶ አጠቃላይ የድህነት መጠን በማስመዝገብ ከአገሪቱ ክልሎች ዝቅተኛው ድህነት የሚታይበት ተብሏል፡፡ ድሬዳዋ የ15.4 በመቶ፣ አዲስ አበባም የ16.8 በመቶ የድህነት መጠን በማስመዝገብ የሐረሪን ክልል ይከተላሉ፡፡

በአንፃሩ ከፍተኛ የድህነት መጠን ከታየባቸው መካከል የትግራይ ክልል የ27 በመቶ አጠቃላይ ድህነት መጠን በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆኗል፡፡  የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 26.5 በመቶ ሲያስመዘገብ፣ አማራ የ26.1 በመቶ፣ ኦሮሚያ የ23.9 በመቶ፣ አፋር የ23.6 በመቶ፣ ጋምቤላ የ23 በመቶ፣ ሶማሌ የ22.4 በመቶ እንዲሁም ደቡብ ሕዝቦች ክልል የ20.7 በመቶ አጠቃላይ የድህነት መጠን አስመዝግበዋል፡፡

በምግብ ድህነት ረገድም ሐረሪና ድሬደዋ በቅደም ተከተላቸው መሠረት የ6.3 በመቶና የ12.2 በመቶ ዝቅተኛውን የምግብ ድህነት መጠን እንዳስመዘገቡ ሲታይ፣ ጋምቤላ የ17.2 በመቶ፣ አዲስ አበባ የ19.1 በመቶ አጠቃላይ የምግብ ድህነት ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ የአማራ ክልል ከፍተኛውን የምግብ ድህነት መጠን በማስመዝገብ በ33 በመቶ ቀዳሚው ሆኗል፡፡

ከሐምሌ 2007 ዓ.ም. እስከ ሰኔ 2008 ዓ.ም. ባሉት 12 ወራት ውስጥ በተሰበሰበ መረጃ መሠረት የተጠናቀረው ዋናው የጥናት ትንተና ውጤት በሰኔ ወር ይፋ እንደሚደረግ፣ በአሁኑ ወቅት ይፋ የተደረገው የጥናት ውጤት ግን ቅደመ ማጠናቀቂያ ሪፖርት የቀረበበት እንደሆነ አቶ ጣሰው አስታውቀዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች