Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየባህል ሙዚቀኛ ሀብተሚካኤል ደምሴ     (1946 - 2010)

የባህል ሙዚቀኛ ሀብተሚካኤል ደምሴ     (1946 – 2010)

ቀን:

በኢትዮጵያ ባህላዊ ሙዚቃ በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ ድምፃውያን ሀብተሚካኤል ደምሴ አንዱ ነው፡፡ ግሩም የመሰንቆ ጨዋታውና ለዛ ያለው ድምፁ በቀድሞውና በአሁኑ ትውልድም መወደድን አትርፎለታል፡፡ በተለይ በመዲናና ዘለሰኛ እንዲሁም በሰርግ ዘፈኖችም ይታወቃል፡፡ ሀብተሚካአል የባህላዊ ሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋችና ድምፃዊ ብቻ ሳይሆን ተዋናይም ነበር፡፡

‹‹ምስጋና›› የተሰኘው የመዲናና ዘለሰኛ አልበሙን ጨምሮ 17 የባህላዊ ሙዚቃ አልበሞችን ለአድማጮች አቅርቧል፡፡ በተለይም በፆም ወራት የሚደመጡት የመዲናና ዘለሰኛ መዝሙሮች ቅኔ አዘልም ናቸው፡፡ በ1971 ዓ.ም. የሀገር ፍቅር ቴአትርን ከተቀላቀለ በኋላ ከድምፃዊነት ባሻገር ግጥምና ዜማ በመድረስም ይታወቃል፡፡

በመሰንቆ ጨዋታው የተማረኩ በርካታ ወጣት መዚቀኞች ወደ ባህላዊ ሙዚቃው ለመግባት እንደ መነሻ ከሚጠቅሷቸው መካከል ሀብተሚካኤል ይገኝበታል፡፡ እሱም ወጣት ድምፃውያንን ከማነሳሳት ባሻገር አብሮ በማቀንቀንም ዘመን አይሽሬ ስጦታውን አበርክቷል፡፡ በቅርቡ የመጀመሪያ አልበሙን ካወጣው ዳን አድማሱ ጋር በጥምረት የሠሩት ዘፈን ምሳሌ ይሆናል፡፡

የባህል ሙዚቀኛ ሀብተሚካኤል ደምሴ

‹‹ባልቻ አባ ነፍሶ››፣ ‹‹መስታወት›› እና ‹‹ታጋይ ሲፋለም›› ከተወነባቸው ቴአትሮች መካከል ናቸው፡፡ የሱን ፈለግ ተከትሎ የሙዚቃ ሕይወትን የተቀላቀለው ልጁ ኤፍሬም ሀብተሚካኤል በዘርፉ ከሚጠቀሱ ሙያተኞች አንዱ ነው፡፡ ሠርግ ሲታሰብ የሀብተሚካኤል፣ ሐሴትን የሚያጭሩ ዘፈኖች የሚታወሷቸውም በርካቶች ናቸው፡፡

ይህ አንጋፋ የሙዚቃ ሰው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ረፋድ ላይ በደረሰበት የመኪና አደጋ ነበር፡፡ በዕለቱ አበበ ቢቂላ ስቴዲየም መግቢያ አካባቢ መንገድ በማቋረጥ ላይ ሳለ ከአስኰ ወደ ፒያሳ በሚሄድ ሀይገር ባስ ተገጭቶ፣ አቤት ጠቅላላ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱ ሊተርፍ አልቻለም፡፡

ድምፃዊው በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወቱ በማለፉ ልባቸው የተነካ አድናቂዎቹ ሙዚቀኞችም ሐዘናቸውን በተለያዩ የማኅበረሰብ ድረ ገጾች መግለጻቸውን እንደቀጠሉ ነው፡፡ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የመኪና አደጋ ከዕለት ወደ ዕለት አሳሳቢነቱ የመጨመሩ ጉዳይም አነጋጋሪ ሆኗል፡፡

ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣ ያለበቂ ልምድ ማሽከርከር፣ እያሽከረከሩ በስልክ መነጋገርና ሌሎችም የትራፊክ ሕጋግት ጥሰቶች የሕይወት ዋጋ ማስከፈላቸውን ቀጥለዋል፡፡ በአገሪቱ የተሰማውን የሀብተሚካኤል ሕልፈት ጨምሮ ያልተሰሙ በርካታ አሰቃቂ አደጋዎችም ሰዎችን እየቀጠፉ ነው፡፡ በቅርቡ ታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያ ዶ/ር ወልዳይ አመሀ፣ ከጥበብ ሰዎች መካከል በመኪና ግጭት ያለፈችው ተዋናይት ሰብለ ተፈራ ይጠቀሳሉ፡፡ እልባት ያልተገኘለት የመኪና አደጋ ዛሬም ሌላ አንጋፋ የጥበብ ሰው አሳጥቷል፡፡

በቀይ አልያም አረንጓዴ ጃኖ ባህላዊ ልብስ ለብሶ፣ መሰንቆውን ይዞ መድረክ ላይ በሚያቀነቅነው ሀብተሚካኤል ዜማዎች የብዙዎች ልብ ረክቷል፡፡ በመዲናና ዘለሰኛው መንፈሳቸው ታድሷል፡፡ ሰርጋቸውም ደምቋል፡፡

በቀድሞው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት ለጋምቦ ወረዳ ልዩ ስሙ ደረባ በተባለ አካባቢ በ1946 ዓ.ም. የተወለደው ሙዚቀኛው፣ በ1963 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ነበር መሰንቆ የገዛው፡፡ በደጃች ውቤ ከበላይነሽ አመዴ (ኩንስንስ)፣ ዘነበች ታደስ (ጭራ ቀረሽ) ጋር መሰንቆውን በሚጫወትበት ወቅት፣ በ1971 ዓ.ም. ሀገር ፍቅር ማስታወቂያ አወጣ፡፡ ተወዳድሮም በባህል ክፍል ሙዚቀኝነት ተቀጠረ፡፡

በ1968 ዓ.ም. የተባበሩት የባህል ሙዚቃ ጓድ ማኅበር አቋቁሞ ዋና ጸሐፊ የነበረ ሲሆን፣ ከወረታው ውበት፣ አያሌው ይመኑና ሌሎችም ሙያተኞች ጋር ሠርቷል፡፡ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋች ቢሆንም፣ በ1983 ዓ.ም. በዝክረ ኪነ ጥበብ መርሐ ግብር ላይ እንዲዘፍን ተደረገ፡፡ በ‹‹አንቻሮ ቃሉ›› ዘፈን የጀመረው የመድረክ ሕይወትም ለአሠርታት ዘለቀ፡፡

‹‹መሰንቆና ክራር ይዤ በቀኝ እጄ፤

ያቅበጠብጠኛል በገና ወድጄ›› ከቅኔ አዘል ሙዚቃዎቹ ይጠቀሳል፡፡ ‹‹ተመለሽ››፣ ‹‹ንቦዬ››፣ ‹‹ሸሞንሟና›› እና ሌሎችም በርካታ ሥራዎቹ እንደተወደዱ ዘመናት አስቆጥረዋል፡፡ ከማሪቱ ለገሰ ጋር የሠሩት ‹‹ባዝራው ይዤሻለሁ›› እንዲሁም ከሌሎችም አንጋፋ ድምፃውያንና ከልጁም ጋር የተጣመረባቸው ዘፈኖችም አይዘነጉም፡፡

በ1983 ዓ.ም. ‹‹አንቻሮ ቃሉ›› የተሰኘ የመጀመረያ አልበሙን አሳትሟል፡፡ ከዜድ ሙዚቃ ቤት፣ ኢትዮ ሙዚቃ ቤትና ሌሎችም ሙዚቃ ቤቶች ጋር በመሆን ቀጣይ አልበሞቹን ለሕዝብ አስደምጧል፡፡

አንጋፋዎቹ ባህሩ ቃኜና አሰፋ አባተ ለሙዚቃ ሕይወቱ መነሻ እንደሆኑ ድምፃዊው በአንድ ቃል ምልልስ ተናግሮ ነበር፡፡ አምባሳል፣ ባቲ፣ ትዝታ፣ አንቺ ሆዬን በመሰንቆ ለማስደመጥ ባህር ተሻግሮ ግሪክ፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ እንግሊዝ፣ ስዊዘርላንድና ሌሎችም በርካታ አገሮች ተዘዋውሯል፡፡ ሽልማቶችና የእውቅና ሰርተፍኬቶችም ተበርክቶለታል፡፡

ከሀብተሚካኤል ቤተሰብ ጥበቡን የተቀላቀለው ድምፃዊ ኤፍሬም ብቻ ሳይሆን ሴት ልጁ ልዩወርቅም ናት፡፡ በ1966 ዓ.ም. ጋብቻ የመሠረተው ድምፃዊው፣ አራት ሴትና ሦስት ወንድ ልጆች እንዲሁም የልጅ ልጆችም አፍርቷል፡፡

ከጥቂት ዓመታት ወዲህ መሰንቆ መጫወቱን ትቶ በድምፅ ብቻ ያቀነቅን የነበረው ነፍስ ኄር ሀብተሚካኤል ደምሴ፣ በ64 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብሩ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት በአስኮ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...