Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ጫማ ውስጥ የሚገቡት ማጠንከሪያዎች እንኳን የስኳር ሕሙማንን  የደህና ሰውን እግር ይልጣሉ››

ወ/ት ፀደይ ሚኬኤሌ፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሌዘር ኤንጂነሪንግ የአራተኛ ዓመት ተማሪ

ፀደይ ሚኬኤሌ ትባላለች፡፡ ተወልዳ ያደገችውና የመሰናዶ ትምህርቷን  ያጠናቀቀችው አዲስ አበባ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሌዘር ኢንጂነሪንግ የአራተኛ ዓመት ተማሪ ናት፡፡ ባላት የፈጠራ ችሎታ ለስኳር ሕሙማን አገልግሎት የሚውል ጫማ እንዲሁም ዓይነ ሥውራንን ከመኪና አደጋ የሚታደግ ሴንሰር (ጠቋሚ) ሠርታለች፡፡ ሥራዎቿንም ሰሞኑን አዲስ አበባ በተዘጋጀ ኤግዚቢሽን አቅርባለች፡፡ ታደሰ ገብረማርያም በሥራዎቿ ዙሪያ አነጋግሯታል፡፡

ሪፖርተር፡- የስኳር ሕሙማንን ጫማ ለመሥራት ያነሳሳሽ ምክንያት ምንድነው?

ወ/ት ፀደይ፡- አያቴ የስኳር በሽተኛ ስለነበሩና በዚህም የተነሳ ዓይናቸውንና እግራቸውን ስላሳጣቸው ነው፡፡ አሁን ላይ ቁጭ ብዬ ሳሰበው እግራቸውን ሊያሳጣቸው የቻለው ያኔ ያደረጉት ወይም ይጫሙት የነበረው መደበኛው ጫማ ልክ ስላልነበረ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የጠቆረውና የቆሰለው ጣታቸው ወዲያውኑ ቢቆረጡ ኖሮ አለበለዚያም ለስኳር ሕሙማን የሚያገለግልለው ጫማ ቢኖራቸው ወይም ቢጫሙ ኖሮ እግራቸው ከመቆረጥ ይድን ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ለአያቴ ያላደረኩላቸውን ለሌሎች ማድረግ እንድችል ብዬ ጫማውን ለመፍጠር ቻልኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ጤናን አስመልክቶ በነበረው ጉባኤና ኤግዚቢሽን ላይ ሥራው አዲስ ነው ስትይ ነበር፡፡ ስለዚህ ብታብራሪልን?

ወ/ት ፀደይ፡- የስኳር ሕሙማን ጫማ ኢትዮጵያ ውስጥ አይመረትም፡፡ የእኔ ሥራ አዲስ ነው፡፡ ሶሉ ቶሎ የማያልቅ ከመሆኑም በላይ እግራቸው ከመሬት ጋር አይገኛኝም፡፡ ወደ ሥራው የገባሁት መጀመሪያ  የስኳር በሽተኞች በጫማ የሚገጥማቸው በሽታ ምንድነው? የሚጎዳቸውስ እንዴት  ነው? በሚሉት ዙሪያ ተገቢ የሆነ ጥናት ካካሄድኩ በኋላ ነው፡፡ በዚህ ጥናት ላይ የስኳር ሕሙማን በሚያደርጉት ጫማ እግራቸው ምን ያህል እንደተጎዳ ተዘዋውሬ አይቻለሁ፡፡ የስኳር ሕመማን ማኅበርንና በየሆስፒታሉ ያሉ የስኳር ሕሙማንን አነጋግሪያለሁ፡፡ ይህ ጫማ በዓይነቱ አዲስ ለመሆኑ ሌላው ማረጋገጫ እንደዚህ ዓይነት ጫማ በአገር ውስጥ የሚያመርት ግለሰብ ወይም ተቋም ፈልጌ አላገኘሁም፡፡ ከዚህም ሌላ ጥናቶችን አድርጌያለሁ፡፡ የስኳር በሽተኞችም ‹ለእኛ የሚሆነውን ጫማ እምናገኘው ከውጭ ነው› ብለው ነግረውኛል፡፡ ጫማውንም የሠራሁት በአገር ውስጥ የሚገኙ ማቴሪያሎችን በመጠቀም ነው፡፡ ጫማውን የሠራሁት በራምሴ ጫማ ፋብሪካ ውስጥ ነው፡፡ እዚህም ፋብሪካ ልገባ የቻልኩት ለአፓረንትሺፕ (የሙያ ልምምድ) ተልኬ ነው፡፡ የፋብሪካው ባለቤትና ሌሎቹም የፋብሪካው ባለሙያዎች  የሐሳብ እገዛና ትብብር አድርገውልኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የስኳር ሕሙማን ጤናማ የሆነው የሚያደርገውን ጫማ በመጫማታቸው ምን የተለየ ጉዳት እንደደረሰባቸው ካካሄድሽው ጥናት የተገነዘብሽው ነገር አለ?

ወ/ት ፀደይ፡- የስኳር ደረጃችውን ባልተቆጣጠሩት ቁጥር የደም ስሮቻቸውንና ነርቮቻቸውን ያበላሸዋል ወይም ይጎዳዋል፡፡ ነርቭ ሲበላሽ ወይም ሲጎዳ ‹‹ኔሮፓት›› የተባለ አካልን በድን የሚያርግ በሽታ ያስከትላል፡፡ በዚህም የተነሳ ወደ እግራቸው የሚወርደው ደምና ነርቫቸው ሲጎዳ የተጠቀሰው በሽታ ይከሰትና እግራቸው በድን ይሆናል፡፡ ጫማቸው ይጥበባቸው ይስፋቸው፣ እግራቸው ይላጥና ይቆረጥም አይሰማቸውም፡፡ ከቆየ በኋላ ነው የሚታወቃቸው፡፡

      በአገራችን የሚመረተው ጫማ የቆዳው ቅጥነት ትልቅ ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በተለይ የወንድ ጫማ ለዲዛይኑ ሲባል ብዙ ስፌት አለው፡፡ ሶሉም ሆነ ከውስጥ የሚገቡት ማጠንከሪያዎች እንኳንስ የሰኳር ሕሙማንን ቀርቶ የደህናውን ሰው እግር እንዲላጥ ያደርጋሉ፡፡ የስኳር ሕሙማን ደግሞ የተላጠው አካላቸው ዘንድ ነጭ የደም ሴል እንደልብ ስለማይደርስ ቶሎ አይድንም፡፡ ይህም ቁስል ይፈጥርና ወደ ጋንግሪን ይቀየራል፡፡ ያለው አማራጭ በጋንግሪን የተጠቃውን አካል ቆርጦ ማውጣት ብቻ ይሆናል፡፡ ይህንን ዕድል ሳያገኙ የሚሞቱም አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ስንት የስኳር በሽተኛ ጫማዎችን ነው የሠራሽው?

ወ/ት ፀደይ፡- የሠራሁት ለናሙና አንድ ነው፡፡ ይህም ጫማ ለስኳር በሽተኞች ተባለ እንጂ ብዙ ሰዓት ቆመው የሚያሳልፉና በእግር ብዙ የሚጓዙ ሰዎች እግራቸው እንዳይጎዳ ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ እንዲጠቀሙበትም ይመከራል፡፡ የሠራሁት ጫማ ወቅቱን የሚከተል ነው፡፡ ለክረምት ጊዜ እግራቸውን ከብርድ መከላከል የሚያስችል ፈር የገባለት ሲሆን፣ በአጠቃላይ እግር ላይ ጉዳት ያደርሳሉ የሚባሉ ነገሮችን በመቀነስ ነው፡፡ በአጠቃላይ ችግር ያመጣሉ የሚባሉ ነገሮችን 100 ፐርሰንት ባይሆንም እስከ 95 ፐርሰንት እንዲቀንሱ ተደርጎ ተዘጋጅቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የፈጠራ ችሎታሽን በመጠቀም የሠራሽውን ጫማ በኤግዚቢሺን ለሕዝብ አቅርበሻል፡፡ ጉዳዩ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል እውቅና ተሰጥቶሻል?

ወ/ት ፀደይ፡- ጫማውን ከሠራሁ በኋላ በመጀመሪያ ያሳየሁት ለስኳር ሕሙማን ማኅበር ነበር፡፡ ከዚያም ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ ለባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ለኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አቅርቢያለሁ፡፡ ውጭ ባሉ ጆርናሎችም እንዲታተም ልኬያለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጆርናል ላይም ታትሞ ይወጣል፡፡ ከዚህም ሌላ ‹‹የስኳር በሽተኞችን ጫማ ለኢትዮጵያ ጫማ ፋብሪካዎች ማስተዋወቅ›› በሚል ርዕስ በኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አዳራሽ በኤግዚቢሽን አቅርቤያለሁ፡፡ በተረፈ ተገቢውን ዕውቅና ወይም ፓተንት ራይት ለማግኘት ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የፕሮፖዛል ቅጽ መልሼ አስገብቼያለሁ፡፡ በቅርቡ ዕውቅና ይቸረኛል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ዓይነ ሥውራንን ከመኪና አደጋ የሚከላከል ጠቋሚ (ሴንሰር) እንዴት ሠራሽው?

ወ/ት ፀደይ፡- የመሰናዶ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ለዓይነ ሥውራን አገልግሎት የሚውሉ ሦስት ዓይነት የፈጠራ ሥራዎችን አበርክቻለሁ፡፡ ከእነዚህም መካከል አንደኛው መኪና ሲመጣ ርቀቱንና ፍጥነቱን ለይቶና ሴንስ አድርጎ የሚነዝር እና በሰዓት መልክ የተዘጋጀ እንዲሁም 250 ቮልት ባትሪ የሚገጠምለት ሴንሰር ይገኝበታል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሴንሰር ምናልባት ከአቅም በላይ ቢሆንባቸው በዱላቸው አማካይነት መስማት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ሌላውና ሁለተኛ የፈጠራ ሥራዬ ነው፡፡ ይህም የተመቻቸው በአስፋልቱና በመኪናው መካከል የሚፈጠረውን ፍሪክሽን እንደ ኢርፎን በዱላቸው ውስጥ እንዲሰሙ ተደርጎ መሠራቱ ነው፡፡ ነገር ግን ዓይነ ሥውራኑ ‹እኛ የመኪናን ድምፅ በጆሯችን መለየት እንችላለን፡፡ ትልቁ ችግራችን ግን ጉድጓዶች ናቸው፡፡ ብዙ ኮንስትራክሽኖች ስላሉ ጉድጓዶቹ ለዓይነ ሥውራን ብዙ ጉዳት ያደርሳሉ፡፡ እያደረሱም ነው፤› ብለው ስለነገሩኝ ለዚህም የሚስማማና ጉድጓድን ሴንስ የሚያርግ ዱላ በዲዛይን ደረጃ ሠርቼያለሁ፡፡ በዲዛይን ደረጃ ብቻ እንድሠራ ያደርገኝም ምክንያት ለዚህ የሚሆን ጥሬ ዕቃ በማጣቴ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚሀን የፈጠራ ሥራዎች በትዕይንት መልክ ለሕዝብ አቅርበሻቸዋል? በአሁኑ ጊዜስ በምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?

ወ/ት ፀደይ፡- የፈጠራ ሥራዎቼን አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በተካሄደው የመሰናዶ ተማሪዎች የፈጠራ ሥራዎች ውድድር ላይ አቅርቤያለሁ፡፡ ውድድሩ ሽልማት አለው፡፡ የእኔ ሥራዎች ግን ሽልማት አልተቸራቸውም፡፡ ምክንያቱም ኤግዚቢሽኑን ያዘጋጁት አካላት ‹ያንቺ የፈጠራ ሥራዎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ስለሚጠቀሙና አሁን የቀረበው የጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ውጤቶችን ብቻ በመሆናቸው ሽልማቱ ተላልፎሻል› ብለውኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የወደፊት ዕቅድሽ ምንድ   ነው? ከትምህርት ውጭ በትርፍ ሰዓትሽ ምን ትሠሪያለሽ?

ወ/ት ፀደይ፡- ራሱን የቻለ የስኳር በሽተኛ ጫማ የሚመረትበትና ለስኳር ሕሙማን የእግር አጠባበቅ ትምህርት የሚሰጥበት ተቋም ለመክፈት እፈልጋለሁ፡፡ ይኼንንም የማደረገው ችግሮችን ከመቅረፍ እንጂ ትርፍ ከማግኘት አንፃር አይደለም፡፡ በዚህም ብቻ ሳልወሰን አዕምሮዬን ዘና የሚያደርግልኝን ሙያ እፈልጋለሁ፡፡ ራሴን ያለማመድኩት በመልካም ነገር መደሰትን ነው፡፡ በዚህም የተነሳ በደም ባንክ፣ በባህር ዳር አረጋውያን መርጃ ማዕከል ውስጥ በትርፍ ጊዜዬ እሠራለሁ፡፡ አያቴ ስላሳደጉኝ አረጋውያንን ስንከባከብ አያቴን እንደተንከባከብኩ ዓይነት ይሰማኛል፡፡ አገሬንም እንድወድ ያደረጉኝ አረጋውያን ናቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ምንም የከፋ ሒደት ውስጥ ቢሆኑም ብዙ ተሞክሮና ልምድ አላቸው፡፡ ያሳለፉትን ጊዜያት ሲያወጉ በጣም ደስ ይላል፡፡ ረዳት የሌላቸው ሰዎች ሲታመሙ አስታምማለሁ፡፡ ሰዎች ሲሰቃዩ ማየት ለኔ በጣም ከባድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አሁን ከተያያዝኩት ትምህርት ሌላ በትርፍ ጊዜዬ የነርስነትን ሙያ በመከታታል ላይ ነኝ፡፡

 

 

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ጦርነቱና ሒደቱ

ሦስት ሳምንታት ያስቆጠረው ሦስተኛው ዙር የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት አሁንም...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...

ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤ የአዲስ አበባን ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት በተደረገው ምርጫ አሸነፉ

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትን በፕሬዚደንትነት ለመምራት፣...