Sunday, September 24, 2023

ለፖለቲካዊ ጉዳዮች አነስተኛ ትኩረት የሰጠው የፕሬዚዳንቱ ንግግር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሰኞ መስከረም 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡10 ሰዓት ላይ አራት ኪሎ በሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ያልተገኘ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዲሁም የብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት ፕሬዚዳንቶች (ከኦሮሚያ ክልል በስተቀር) ተገኝተዋል፡፡ ዕለቱ አምስተኛው ዘመን የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ሦስተኛ ዓመት የሥራ ዘመናቸውን በጋራ በመሆን በሚያካሂዱት ስብሰባ የሚጀምሩበት ቀን ነው፡፡

የአገሪቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካላት የሆኑት ሁለቱ ምክር ቤቶች ዓመታዊ ሥራቸውን የሚጀምሩት፣ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የሚያደርጉትን ንግግር በማዳመጥ ነው፣ የፕሬዚዳንቱን ንግግር ከማዳመጣቸው አስቀድሞ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ከመቀመጫቸው በመነሳት ይዘምራሉ፡፡

ለፖለቲካዊ ጉዳዮች አነስተኛ ትኩረት የሰጠው የፕሬዚዳንቱ ንግግር

ሰኞ ዕለት የሆነውም ይኸው ነበር፡፡ የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት ከሆኑት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና በአጠቃላይ ከ600 በላይ ከሚሆኑት የሁለቱ ምክር ቤቶች አባላት፣ አብዛኞቹ የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ስንኞች አያውቋቸውም፡፡ በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ግጥም የታተሙባቸው ወረቀቶችን ለሁለቱም ምክር ቤቶች አባላት ለማደል ተገዷል፡፡

የአንድ አገር ብሔራዊ መዝሙር ዓላማ በሕዝቦች ላይ የብሔራዊነት ስሜትን መፍጠር፣ ታማኝነትን፣ አንድነትን፣ የጋራ ሰብዕናን፣ ሰላምንና በአገር መኩራትን በሕዝቦች ወስጥ ለማስረፅ ወደር የሌለው መሣሪያ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙርም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ጭማቂ ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ አራት የተደነገገውም ይህንኑ ያመለክታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ መዝሙር የሕገ መንግሥቱን ዓላማዎችና የኢትዮጵያ ሕዝቦች በዴሞክራሲ ሥርዓት አብረው ለመኖር ያላቸውን እምነት፣ እንዲሁም የወደፊት የጋራ ዕድላቸውን የሚያንፀባርቅ ሆኖ በሕግ ይወሰናል፤›› በማለት ይደነግጋል፡፡

የምክር ቤቶቹ አባላት ምንም እንኳን ከተሰጣቸው ወረቀት ላይ እያነበቡ ቢሆንም፣

‹‹የዜግነት ክብር በኢትዮጵያችን ፀንቶ

ታየ ሕዝባዊነት ዳር እስከ ዳር በርቶ›› በሚሉት ስንኞች በመጀመር

‹‹እንጠብቅሻለን አለብን አደራ

ኢትዮጵያችን ኩሪ እኛም ባንቺ እንኩራ›› በሚሉ ስንኞች ቃል በመግባት የሚያሳርገውን ብሔራዊ መዝሙር በጋራ ዘምረው ወደ መቀመጫቸው እንደተመለሱ፣ በድጋሚ ከመቀመጫቸው እንዲነሱ ተጠይቀዋል፡፡

የምክር ቤቶቹ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት መጀመሪያው ቁጭ ብድግ የሆነባቸው አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ስሜታቸውን በፈገግታ ገልጸዋል፡፡ በድጋሚ እንዲነሱ የተጠየቁበት ምክንያት፣ ከአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ስንኞች ከሚገልጹትና ለማስረጽ ከሚፈልጉት ጋር ተቃራኒ ለሆነ አሳዛኝ ክስተት የህሊና ፀሎት ለማድረግ ነው፡፡

በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች አዋሳኞች መካከል እስከ ዛሬ ድረስ ባልታወቀ ምክንያት በተቀሰቀሰው ግጭት የሁለቱም ብሔሮች ተወላጆች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ያፈሩትን ንብረት ተነጥቀው ከልባሽ ጨርቅ ውጪ ምንም ሳይዙ ከሶማሌ ክልል እንዲወጡ ተደርገዋል፡፡ ሪፖርተር ወደ ሐረር በተጓዘበት ወቅትም ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉ በርካታ ሺዎች በመጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው ተመልክቷል፡፡

የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ የተጀመረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ከአፈ ጉባዔነታቸው ለመልቀቅ ወስነው መልቀቂያ ማስገባታቸውን በይፋ በገለጹበት ማግሥት መሆኑ ደግሞ ሌላው ተቃርኖ ነው፡፡

አፈ ጉባዔ አባዱላ እሑድ መስከረም 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ማምሻውን በሚዲያ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹አሁን በደረስኩበት ደረጃ በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ሁኔታዎች ስላሉና ፍላጎቱም ስለሌለኝ ለመልቀቅ፣ ድርጅቴንና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጠይቄያለሁ፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

አፈ ጉባዔው ይህንን ይበሉ እንጂ አስተያየት ሰጪዎች የአፈ ጉባዔው የቅርብ የፌዴራል መንግሥት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች መካከል የተከሰተውን ግጭት በተመለከተ የያዘውን የአፈታት መንገድ ቅር አሰኝቷቸው የሚለቁ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎች ይህንን ቢሉም አሁንም ጥርት ያለው ነገር አይታወቅም፡፡

የሁለቱን ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን በማስመልከት የመክፈቻ ንግግር ለማድረግ በፓርላማው የተገኙት ፕሬዚዳንት ሙላቱ (ዶ/ር) መንግሥት በ2010 ዓ.ም. ትኩረት ሊያደርግባቸው ይገባል ያሏቸውን ነጥቦች የያዘ ንግግር አቅርበዋል፡፡ ንግግራቸው በ20 ገጾች የቀረበ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በአገሪቱ በተደጋጋሚ ስለሚከሰቱ ግጭቶች፣ እንዲሁም የቅርቡን የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ግጭት አስመልክቶ የተናገሩት በአራት ገጾች ብቻ የተጨመቀ ነው፡፡

‹‹በኦሮሚያና በኢትዮጵያ ሶማሌ አካባቢ ጥቂት ያልተስተካከሉ አፍራሽ አመልካቾች የወለዷቸው ግጭቶች ተከስተው የሰው ሕይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ያለፈበትና ንብረቶች የወደሙበት ሁኔታ መኖሩ ይታወቃል፡፡ ይህ ሁኔታ በፍፁም መወገዝ ያለበት ነው፡፡ መንግሥት ፀጥታውን ከማስከበር ባሻገር አጥፊዎችን ወደ ሕግ ለማቅረብ ሳይታክት እየሠራ ይገኛል፤›› ብለዋል፡፡

በማከልም 2010 ዓ.ም. እንደዚህ ዓይነት በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የቆየውን አንድነት የሚያፈርስ አካሄድ በጭራሽ ሊፈቀድ የማይገባው በመሆኑ የሁለቱም ክልል የአገር ሽማግሌዎች፣ ባህላዊ መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም መላው የሁለቱ ክልል ሕዝቦች ሁኔታው ወደነበረበት እንዲመለስና የተፈናቀሉ ወገኖችንም መልሶ ማቋቋም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የሁለቱም ክልሎች ሕዝቦች ከመንግሥት ጎን እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ንግግር አገሪቱን ሰንገው የያዟት አለመረጋጋቶችን በተመለከተ ብዙ ትኩረት አይሰጥም፡፡ ይልቁንም በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችና ያለፉትን ሁለት ዓመታት የኢኮኖሚ አፈጻጸም ሪፖርት ማቅረቡን መርጠዋል፡፡

ለዚህም ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን ሲጀምሩ በዚህ ጉዳይ ለምን ማተኮር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤትነትን ከማንኛውም ግለሰብና የፖለቲካ ኃይል አምባገነንነት አውጥቶ ብሔሮችን፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ባደረገው ሕገ መንግሥታችን ውስጥ ትልቅ ሚና የሚጫወቱት ሁለቱ ምክር ቤቶቻችን የሥራ ዘመኑን መርሐ ግብር አሀዱ ብለው በሚጀምሩባት በዚህች ቀን፣ አገራችን የተያያዘችውን የህዳሴ ግስጋሴ በተሻለ ፍጥነት በሚያስቀጥሉ ብሎም ወደ ላቀ ከፍታ በሚያሸጋግሯት ዓበይት ጉዳዮች ላይ ትኩረታችንን አድርገን መወያየት እንዳለብን ዕሙን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. የአገሪቱ ኢኮኖሚ 10.9 በመቶ ማደጉን የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህም ከግብርናው በላይ የአገልግሎት ዘርፉ 39.3 በመቶውን አስተዋጽኦ በማድረግ ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ግብርናው ደግሞ 36.3 በመቶ አስተዋጽኦ በማድረግ ሁለተኛ ሆኗል ብለዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. የአገሪቱ ኢኮኖሚ 11 በመቶ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ ዘንድሮ የአገሪቱን የውስጥ ገቢ ለማሳደግ በትልልቅ ታክስ ከፋዮች ላይ በማተኮር መሥራት እንደሚገባ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽንና በሌሎች ዘርፎች የታክስ ዕፎይታ ካገኙ በኋላ በሕጉ መሠረት የማይከፍሉት ላይ ዕርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም. የሞት ሽረት የሚጠይቀው ሌላው ጉዳይ የአገሪቱን የኤክስፖርት ገቢ ማሳደግ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -