Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየውኃ ስፖርት ፈተና

የውኃ ስፖርት ፈተና

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚገኙ ጅረቶች፣ ኩሬዎች፣ ወንዞችና ሐይቆች ለበርካታ ወጣቶች የዋና ችሎታ ባለውለታዎች ናቸው፡፡ ምንም እንኳ እንደ አዲስ አበባ ያሉ የውኃ መገኛ ወንዞች እንኳንና ለዋና ቀርቶ በአጠገባቸው ለማለፍ የሚያዳግቱ እየተበራከቱ ቢመጡም፣ በክልሎች ግን ወጣቶች እንደ ልብ የሚንቦራጨቁባቸው ወንዞች የትየለሌ ናቸው፡፡ ይህ የተፈጥሮ ዕድል ግን በቀላሉ ወደ ዘመናዊ የውኃ ስፖርት እንቅስቃሴ የሚያመጣው አጥቶ፣ የስፖርቱ ፍቅር ያላቸው ታዳጊ ወጣቶች መልምሎና ተገቢውን ሥልጠና ሰጥቶ ለአገርም ሆነ ለዓለም አቀፍ መድረኮች ማብቃት ፈተና ሆኗል፡፡ በምትኩ የግል ፍላጎትን መነሻ ያደረጉ እሰጣ ገባዎች አደባባይ እየወጡ ይገኛሉ፡፡

የውኃ ስፖርት እስከዚህም በማይዘወተርበትና በማይታወቅበት አገር ውስጥ ዘርፉን የሚመሩና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የሚያሳዩዋቸው የአደባባይ ሽኩቻና ንትርክ አስገራሚ እየሆነ መምጣቱን የሚያመላክቱ መድረኮች መታየት ጀምረዋል፡፡ ይልቁንም ፍላጎቱ፣ ብቃቱና ችሎታው ያላቸው የስፖርቱ ተዋናዮች ዞር ብሎ የሚያያቸው እያጡ መሆም እየተስተዋለ ነው፡፡

ባለፈው ነሐሴ በተከናወነው የሪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ ኢትዮጵያ ከአትሌቲክስና ከብስክሌት ተካፋይነቷ በተጨማሪ፣ ለታዳጊ አገሮች በውኃ ስፖርት በተሰጠው ኮታ መሠረት በሁለቱም ጾታዎች ሁለት ተወዳዳሪዎች አቅርባ ነበር፡፡ በተለይ በወንዶች ምድብ የተካፈለው ሮቤል ኪሮስ ተክለ ሰውነትና ብቃት በበርካታ የዓለምና የአገር ውስጥ ሚዲያ መሳለቂያ ከመደረጉም በላይ አገሪቷ ሌላ ተወዳዳሪ  የላትም ወይ? አሰኝቶ ነበር፡፡ 

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአገር ውስጥ የኅብረተሰቡን ቅሬታና ተቃውሞ መነሻ በማድረግ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤትን እንዲታሸግ አድርጎ ማቆየቱ ይታወሳል፡፡

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይሰነዘሩ የነበሩትን ትችቶች መነሻ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርት ፌዴሬሽን በወቅታዊ የውኃ ስፖርት ላይ ያተኮረ መድረክ፣ በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዴሚ መጋቢት 27 ቀን 2009 ዓ.ም. አዘጋጅቶ ነበር፡፡

አራት አሠርታትን ያስቆጠረው የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን በቀደምት ዓመታት በተሻለ መልኩ ይንቀሳቀስ እንደነበረ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አቋሙ አሳሳቢ መሆኑ በመድረኩ ተወስቷል፡፡

በውይይቱ ሆኖ እያንዳንዱ ተናጋሪ በተረዳው መጠን ክፍተት ነው ብሎ ያመነበትን ሁሉ ያለ አንዳች ገደብ እንዲያንሸራሽር የተደረገበት መንገድ የመድረኩ ጠንካራ ጎን ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚቻልም ተመልክቷል፡፡

ይሁን እንጂ በስፖርት አካዴሚው በተዘጋጀው የውይይት መድረክ በአጠቃላይ የውኃ ስፖርት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ብቻ ሳይሆን፣ ስፖርቱ ይመለከተናል የሚሉት የተዋናዮቹ አመለካከትና መልዕክት በራሱ ጥያቄ የሚያጭር ነበር፡፡ ይነሱ የነበሩት አስተያየቶችና ቅሬታዎች የአገሪቱን የውኃ ስፖርቶች ስትራቴጂክ ዕቅዶች ላይ ከማተኮር ይልቅ ምርጫና ከውጭ ጉዞ ጋር የተገናኙ የአሠራር ክፍተቶች ላይ ያዘነበሉ ነበሩ፡፡  

ከቀደምቱ የውኃ ስፖርት ባለሙያቶች ሲነገር እንደተደመጠው፣ የአገሪቱ የውኃ ስፖርት ተወዳጅና ተዘውታሪ ነበር፡፡ ከነበረው አንፃር በአሁኑ ወቅት አዳዲስ ተተኪ ወጣቶች ቀርቶ በስፖርቱ ያሉት ራሳቸውን ከስፖርቱ እያራቁ ስለመሆኑ ቁጭትና ሐዘኔታ በቀላቀለ ስሜት ነበር ሲናገሩ የተደመጠው፡፡

ውይይቱ ሁለት ዓይነት አመለካከት ሲንፀባረቅበትም ነበር፡፡ በአንድ በኩል ለችግሩ የፌዴሬሽኑን አመራሮች ተጠያቂ የሚያደርጉና በሌላ ወገን ደግሞ ችግሩ የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ባለድርሻ እንደሚመለከት የሚጠቁም ነው፡፡

‹‹የምናገረው ስለ እውነት ነው፤›› የሚሉ አስተያየቶች ግን ከሁለቱም ወገኖች የመድረኩን ሰፊውን ጊዜ ወስደው ታይተዋል፡፡ የሚዲያውን ሚና በተመለከተ በሪዮ ኦሊምፒክ የውኃ ስፖርት ተሳትፎ መጥፎ ጎኑ ብቻ ጎልቶ እንዲወጣ ሲደረግ እንደነበር በመጥቀስ፣ ለቀጣይ ግን ‹‹መንግሥት እጁን አጣጥፎ መቀመጥ እንደሌለበት›› የተናገሩ አስተያየት ሰጪዎችም ነበሩ፡፡

በመድረኩ የተገኙት የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ይገዙ በሚዲያው ጉዳይ ለተሰነዘረው አስተያየት፣ የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽንና ሌሎችም ሚኒስቴሩን ጨምሮ መጀመሪያ ወደ ራሳቸው ተመልሰው የተጣለባቸውን የሕዝብና የመንግሥት አደራ በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባ፣ ሚዲያው ደግሞ ያለውን እውነታ ለሕዝብ የማድረስ መብት እንዳለው አስረድተዋል፡፡ አያይዘውም፣ ‹‹የመድረኩ አስፈላጊነት ስፖርቱ ኅብረተሰቡ በሚፈልገው መጠንና ይዘት ማደግ ይችል ዘንድ ከክፍተቶች ለመማር ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ የዚህ ተመሳሳይ መድረክ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡ እንደ መንግሥት ተወካይነታቸው ይኼ ጣልቃ መግባት እንዳልሆነና ይልቁንም መንግሥት በተቀመጠው ፖሊሲ መሠረት የመደገፍና የማብቃት ሚና ብቻ እንዳለውም አልሸሸጉም፡፡ ከሪዮ ኦሊምፒክ በኋላ ታሽጎ የቆየው የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ተከፍቶ ሥራውን እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኪሮስ ሀብቴ በበኩላቸው፣ በእሳቸውም ሆነ በተቋሙ አጠቃላይ አሠራር ላይ የቀረበው ቅሬታና አስተያየት ለውኃ ስፖርቶች ዕድገት ከመመኘት እስከሆነ ድረስ እንደሚቀበሉት፣ በቅርቡም አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ አቅጣጫ እንደሚቀመጥና በተጓደሉ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ምትክ የማሟያ ምርጫ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መጋቢት 23 ቀን 2009 ዓ.ም.  በአዳማ ባደረገው የሥራ አመራር ቦርድ ምርጫ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን የወከሉት አቶ ኪሮስ ሀብቴ በአባልነት መመረጣቸው ይታወሳል፡፡

  

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...