አቶ አብርሃም ሥዩም፤
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር የተመሠረተው በሰኔ 2004 ዓ.ም. ነው፡፡ ማኅበሩ ሲመሠረት በበጎ ፈቃደኞች ይንቀሳቀስ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በቅጥር የሚሠሩ ሠራተኞችን ይዞ ከዚህ ቀደም በተሻለ መልኩ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ ለዳያስፖራው መረጃ በመስጠት፣ በችግሮች ላይ በማወያየትና ለመንግሥት የመፍትሔ ሐሳብ በማቅረብም ይሠራል፡፡ አቶ አብርሃም ሥዩም የማኅበሩ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ማኅበሩ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ማኅበሩ መጀመሪያ አካባቢ እንቅስቃሴ የነበረው ቢሆንም መሀል ላይ ጠፍቶ ነበር፡፡ አሁን ዳግም መታየት ጀምሯል፡፡ ለማኅበሩ እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ ምክንያቱ ምን ነበር?
አቶ አብርሃም፡- ማኅበሩ ከተመሠረተ አምስት ዓመታት ያህል ሆኖታል፡፡ ሆኖም ይመሥረት እንጂ ሲተዳደርም፣ ሲሠራም የነበረው ማኅበሩን በፈቃደኝነት በሚያገለግሉ የቦርድ አባላት ነው፡፡ የተጠናከረ ሠራተኛ፣ ቢሮና ቁሳቁስ ሳይኖረው የበጎ ፈቃደኛ አባላቱ ጊዜ ሲያገኙ ዳያስፖራውን የመርዳትና መረጃ የመስጠት ሥራ ያከናውኑ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ለሦስት ዓመታት ያህል ሲሠራ፣ ሲቀዛቀዝ፣ ሲወድቅና ሲነሳ እንዲሁም ብዙ ውጣ ውረዶችን ሲያሳልፍ ቆይቷል፡፡ በኋላ ግን ይኼ ሁኔታ ሊያስኬድ እንደማይችል በመገንዘብ በዋናነት ማኅበሩ ሙሉ የሰው ኃይል ኖሮት ራሱን የቻለና ማኅበሩን በሙሉ ሰዓት ሊረዳ የሚችል ዋና ዳይሬክተር ቀጥሮ መሥራት ጀምሯል፡፡ ምክንያቱም አገር ውስጥ ያለው ዜጋ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ሚኒስቴሮች ብዙ ጉዳዮች እንዳሉት ሁሉ ዳያስፖራውም አለው፡፡ ዳያስፖራው አንድ የሕዝብ ክንፍ ነው፡፡ መረጃ ይፈልጋል፡፡ በትልልቅ ኢንቨስትመንት በመሳተፍና ካምፓኒዎችን በመምራት ላይ ነው፡፡ ስለሆነም የሚፈልገው አገልግሎት አለ፡፡ ዳያስፖራው ራሱን የቻለ አንድ ክልል ነው ለማለት እንችላለን፡፡ ምክንያቱም እስከ አራት ሚሊዮን የሚደርስ ዳያስፖራ አለ፡፡ ይኼ ሕዝብ በአንድም ሆነ በሌላ ከአገሩ ጋር ቁርኝት አለው፡፡ አገሩም ሲመጣ ኅብረተሰባዊ የሆነ አገልግሎቶችን ይፈልጋል፡፡ አገልግሎት የሚሰጡ መንግሥታዊ ተቋማት ቢኖሩም፣ ዳያስፖራው የሚመጣው የተለየ ጉዳይና ጥያቄ ይዞ ነው፡፡ አንዳንዱ የውጭ አገር መኖሪያ ፈቃድ ያለው ነው፡፡ አንዳንዱ ደግሞ ዜግነት ቀይሮ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ እነዚህን ሊያስታርቅ የሚችል አገልግሎት ከታች እስከ ላይ መኖር አለበት፡፡ በተለይ በዋናነት ዳያስፖራው አገልግሎት በሚሻባቸው ሥፍራዎች ላይ የዳያስፖራ ተወካይ እንዲኖርና ከዳያስፖራው ጋር ቀጥታ ግንኙነት ኖሮ፣ የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚፈታ ግንዛቤው ያለው ሠራተኛ እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ የማኅበራችን ሥራም የዳያስፖራው ድምፅ እንዲሠማ፣ ፍላጎቱ ምን እንደሆነ ማንፀባረቅ፣ ለሚያቀርባቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እንዲሰጠውና በአገሩ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ዘርፎች የነቃ ተሳታፊ እንዲሆን፣ ራሱን፣ ቤተሰቡንና አገሩን እንዲጠቅም፣ የዳያስፖራው ጉዳይ እንዲታወቅና ተቀባይነት እንዲኖረው እንደ ድልድይ መሆን ነው፡፡ ወደ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት የዳያስፖራውን ጉዳይ ይዘን በመሄድ እናቀርባለን፡፡ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡባቸውን መመሪያዎች፣ ሕጎችና አዋጆችን ለዳያስፖራው እናስተዋውቃለን፡፡ ዳያስፖራው ፖሊሲዎችንና ሕጎችን እንዲሁም ጉዳይ የት ተጀምሮ የት መጨረስ እንዳለበትው አያውቅም፡፡ እዚህ ላይ ግንዛቤ እንዲኖር እንሠራለን፡፡ ማኅበሩም ካለፉት ጊዜያት በተሻለ የሰው ኃይል እየተመራ ነው፡፡ ሆኖም ለዳያስፖራው ከሚያስፈልገው አገልግሎት አንፃር በቂ ሠራተኛ የለንም፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማትና በክልል ደረጃም የዳያስፖራውን ጉዳይ የሚያዩ ዴስኮች ተቋቁመዋል፡፡ ከእነሱ ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? ችግሮችን የመፍታት አቅማቸውንስ አይታችኋል?
አቶ አብርሃም፡- እኛ ከምናደርገው ትግልና ውትወታ በመነሳት መንግሥት በተቻለ መጠን በየሴክተር መሥሪያ ቤቱ የዳያስፖራ ዴስክ ከፍቷል፡፡ የእኛ አባላት ለአገልግሎት በሚመጡበት ጊዜ ከየዴስኩ ተጠሪ ጋር እንዲገናኙ እናደርጋለን፡፡ ከየዴስኩ ኃላፊዎች ጋር ማኅበሩ ግንኙነት አለው፡፡ አንዳንዶቹ የዳያስፖራ ተወካይ ተብለው ቢቀመጡም ያን ያህል በአዋጅ የተሰጣቸው ሥልጣን ስለሌለ ገፍተው አንዳንድ ውሳኔዎችን አይሰጡም ወይም ውሳኔዎችን ለማሰጠት በቂ አቅም የላቸውም፡፡ ዳያስፖራውን ተቀብለው እንዴት መስተናገድ እንዳለበት ከማመቻቸት ባሻገር ውሳኔ በመስጠትና ጉዳዮችን በመፈጸም ዙሪያ ያን ያህል ሥልጣኑ አልተሰጣቸውም፡፡ ለምሳሌ ዳያስፖራው ካለው ችግር አንፃር ለአጭር ጊዜ ወደ አገር ቤት ስለሚመጣ አገልግሎት ሲፈልግ ቅድሚያ ይሰጠው ወይም ይስተናገድ የሚል መግባቢያ አለ፡፡ አንዳንድ ቢሮዎችም ቅድሚያ እየሰጡ ያስተናግዳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ በመመሪያ ወይም በጽሑፍ አልተሰጠንም ይላሉ፡፡ ሌሎች ሰዎች እያሉ ለምን ቅድሚያስ እንሰጣለን ይላሉ፡፡ በየዴስኩ የዳያስፖራ ጉዳይ ኃላፊዎች ቢኖሩም ጠንካራና ወጥ ሥራ ከመሥራት አንፃር ገና ይቀረዋል፡፡ ማኅበሩ ይኼንን እንደ አጀንዳ ይዞ መንግሥት ከታች ላሉ የዳያስፖራ ዴስክ ተወካዮች ሥልጣንና አቅም እንዲፈጥርላቸው እየሠራን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- ዳያስፖራው ኢንቨስትመንት ይዞ ሊመጣ ቢችልም አገልግሎት በማግኘት በኩል አገር ውስጥ ካለው በምን ይለያል? እኩል ተጠቃሚ መሆን አለብን በሚልም በየአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ የሚከራከሩ ያጋጥማሉ፡፡ እንደ ማኅበር እዚህ ላይ ምን አስተያየት አላችሁ? ምክንያቱም ዳያስፖራው ኢንቨስት ለማድረግ መጥቶ ለዓመታት ሳይሳካለት ሲቀር፣ ተሳክቶለት ሲሠራ ደግሞ በአካባቢው ማኅበረሰብ ተቀባይነት ሲያጣ ይስተዋላል፡፡ ታች ድረስ ወርዶ ግንዛቤ በማስጨበጡ ላይስ ምን ሠርታችኋል?
አቶ አብርሃም፡- በዋናነት ችግሩን እናውቀዋለን፡፡ በየግልም የሚያጋጥመን ችግር ነው፡፡ ስለ ዳያስፖራው ያለውን የተሳሳተ አመለካከት መቀየር የሚቻለው ከላይ ከመንግሥት ተቋማት ካሉ ከተማሩና የመንግሥትና የሕዝብ ኃላፊነት ከወሰዱ አመራሮች ጀምሮ ወዳታች ወደ ኅብረተሰቡ በመውረድ ነው፡፡ በአመራር ደረጃ እንኳን ስለዳያስፖራው የተሳሳተ አረዳድ ያላቸው አጋጥመውኛል፡፡ ዳያስፖራው መጥቶ መሬት ነው የሚጠይቀው፣ ይህን ያንን አድርጉልኝ ነው የሚለው፤ በሚል ሁሉንም አንድ ቦታ የመፈረጅ ሁኔታ አለ፡፡ በእርግጥ በኅብረተሰባችን ውስጥ ጥሩ አምራች ዜጋ ያልሆነ እንዳለ ሁሉ በዳያስፖራ ውስጥ አፍራሽ የሆነ፣ የግል ጥቅም ያለው፣ አገራዊ አመለካከትና አጀንዳ የሌለው፣ የሕዝብንና የአገርን ጥቅም በሚጎዳ አቅጣጫ የተሰማራ አይኖርም አይባልም፡፡ ሆኖም ከፍተኛው ቁጥር አምራች፣ አልሚ፣ አገር ወዳድ አገሩን የሚፈልግ፣ በየትኛውም ሥፍራ የአገሩን ሰላም፣ ዕድገትና ዴሞክራሲያዊ ብልፅግና እንዲመጣ የራሱን ኃላፊነት ሲወጣ የኖረ ነው፡፡ የተለየ አመለካከት ያላቸው ጥቂት ናቸው፡፡ በውጭም ፖለቲካና አገርን ቀላቅለው የሚመለከቱ አሉ፡፡ ለፖለቲካ ፓርቲው ካላቸው ጥላቻ ወይም ካላቸው የተለያየ የፖለቲካ ፍልስፍና ተነስተው የአገርን ጥቅም ከዛ ጋር አያይዘው አገርን የሚጎዳ ድርጊት የሚፈጽሙ ጥቂት ናቸው፡፡ አብዛኛው አልሚ ነው፡፡ ሆኖም እኛ ዳያስፖራዎች ተቀበሉን ወይም ስለዳያስፖራ ያላችሁ አመለካከት መቀየር አለበት ከማለት ይልቅ በሥራ ማሳየት ይሻላል፡፡ ዳያስፖራው ምን ሠራ? ቢባል አገራችን በወጪ ንግድ፣ በዕርዳታ፣ በብድርና በተለያዩ መንገዶች የውጭ ምንዛሪ ከምታገኝባቸው መንገዶች እጅግ በበለጠ ሁኔታ (ሐዋላ) ሪሜታንስ ወይም ዳያስፖራው ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ከሚልከው ተጠቃሚ እየሆነች ነው፡፡ በ2009 ዓ.ም. በጀት ዓመት በመጀመሪያዎቹ ስምንት ወራት ብቻ እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ያደረገው ዳያስፖራው ነው፡፡ በዳያስፖራው ላይ ተጠናክሮ ቢሠራ አገሪቱ ያለባትን የውጭ ገንዘብ እጥረት ሊፈታና የኢኮኖሚው ጀርባ አጥንትም ሊሆን የሚችል ነው፡፡ ከመንግሥት ቀጥሎ የሥራ ዕድል በመክፈት እየሠራ ነው፡፡ ለዚህች አገር ዕድገት የዳያስፖራውን አስተዋጽኦ ማጤን ተገቢ ነው፡፡ ዳያስፖራው በርካታ ሥራ ቢሠራም ከመንግሥት ኃላፊዎች ጀምሮ እስከ ታች የኅብረተሰቡ ክፍል የተሳሳተ አመለካከት ያላቸው ግለሰቦች አሉ፡፡ የዳያስፖራውን አበርክቶ የማይገነዘቡ ቢኖሩም የዳያስፖራው ሥራ ገብቶት የሚያበረታታና የሚያግዝም አለ፡፡ ሆኖም አመለካከቱ እየተቀየረ ነው፡፡ ወደፊት የተሻለ እንደሚሆንም እናምናለን፡፡ በተሳተፍንባቸው መድረኮችም ከላይ ጀምሮ ግንዛቤው እንዲኖር ወትውተናል፡፡ የዳያስፖራውን አስፈላጊነትና ምንነት ከላይ ጀምሮ እንዲገነዘቡ ሥልጠና እንዲሰጥ ያስገነዘብንበት ሁኔታም አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ያህል አባላት አሏችሁ?
አቶ አብርሃም፡– የማኅበሩን መታወቂያ የያዙና ዓመታዊ መዋጮ እየከፈሉ የሚገኙ ወደ ስድስት ሺሕ የሚጠጉ አባላት አሉን፡፡ በአዲስ አበባና በየትኛውም ዓለም የሚኖሩም ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- ከእነዚህ ውስጥ በሕክምና፣ በትምህርት በሳይንስና በሌሎችም ዘርፎች አንቱ የተባሉ ይኖራሉ፡፡ የዕውቀት ሽግግር እንዲኖር ማኅበሩ ምን እያደረገ ነው?
አቶ አብርሃም፡- በቅርቡ የዳያስፖራ ወጣቶች ፎረም ተቋቁሟል፡፡ ዓላማው በውጭ የተወለዱ ወይም ያደጉ ዳያስፖራዎች በኔትወርክ እንዲያያዙ፣ ተማሪዎች በኢንተርንሺፕ አገልግሎት እንዲያገኙ፣ ‹‹አገርህን እወቅ›› በሚል አገራቸውን እንዲያውቁ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት አገራቸው ላይ በግል ወይም በጋራ መሥራት እንዲችሉ ነው፡፡ አገሩ ሲመጣ ከነበረው ባህል የተነሳ ባይተዋር እንዳይሆን እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁና ችግሮችን በጋራ እንዲፈቱም ነው፡፡ አገር ውስጥ ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርና ከወጣቶች ማኅበር ጋር በጋራ ሆኖ ወጣቱ ለአገር ሊያበረክተው የሚገባው ምንድነው? ምንስ ይጠበቃል? በሚለው የዳያስፖራው ወጣት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ያደረግንበት ሁኔታ አለ፡፡ የወጣቱ ጉዳይ በዲፓርትመንት ተቋቁሞና የራሱ ኮሚቴ ኖሮት፣ ወጣቶቹ እርስ በርሳቸው በወር አንዴ ወይም ሁለቴ እንደአስፈላጊነቱ እየተገናኙ ሐሳባቸውን የሚለዋወጡበትና የሚያጠናክሩበት መንገድ አመቻችተናል፡፡ የዳያስፖራ የሴቶች ዲፓርትመንትም ተቋቁመናል፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ በሚከበረው የዳያስፖራው አገራዊ ጉባኤ ማግሥት ይህንን በይፋ እናሳውቃለን፡፡ ይህ ዲፓርትመንት ከሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በውጭ የኖረች ዳያስፖራ በውጭ የተማረችውን፣ ያላትን ልምድ አገር ውስጥ እንድታካፍል ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ዳያስፖራዎች በምን መልኩ ሊሳተፉና ምን ሊያበረክቱ ይችላሉ? በግል ከሚያደርጉት በተጨማሪ በጋራስ እንዴት ይሳተፋሉ? የሚለውን የሚያይ ኮሚቴም ተቋቁሟል፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችና በሌሎች የትምህርት ተቋማት በመሥራት ከፍተኛ ልምድ ያዳበሩ ዳያስፖራዎችም አሉ፡፡ አገራችን ከገንዘብ ይልቅ ከዳያስፖራው በስፋት ልትጠቀም ይገባታል የምንለው በዕውቀት ሽግግርና በፈጠራ ሥራ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ፣ በየግል ትምህርት ተቋማቱ ገብተው ሥልጠና የሚሰጡ፣ በሕክምናው ለተወሰነ ጊዜ እየመጡ የልምድና የዕውቀት ሽግግር የሚያደርጉ አሉ፡፡ ነገር ግን በማኅበሩ በኩል ያየነው ክፍተት አሠራሩ የተደራጀና ወጥነት የጎደለው መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ማኅበሩ ምሁራኑን የሚያሰባስብበት ሥራ ጀምሯል፡፡ ጡረታ ወጥተው አገራቸው የመጡም ይኖራሉ፡፡ እነዚህን በአገር ሽምግልና፣ በመንግሥትና በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል አጀንዳዎች ሲኖሩ መሀል ገብተውና ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው፣ የመነጋገሪያ መድረክ በመፍጠር ለአዲሱ ትውልድ ሊያበረክቱ የሚችሉበትን አሠራር ለመዘርጋት ወደፊት ዕቅድ ይዘናል፡፡ አገራችን ከዳያስፖራው መጠቀም ያለባትን ያህል ስላልተጠቀመች መልክ አስይዘን ለመሥራት እየተጋን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- መንግሥትና ዳያስፖራው በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ተፈራርጀዋል፡፡ መንግሥትም ይህንን ያህል አያስቀርባቸውም፣ እነሱም መንግሥትን አርቀዋል፡፡ ሁለቱም ለኢትዮጵያ እስካሉ ድረስ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ፣ ዳያስፖራው በፖለቲካ ልዩነቶቸ ተወጥሮና ግራ ተጋብቶ አገሩን ከመርዳት እንዳይቆጠብ በማኅበሩ በኩል የምትሠሩት ሥራ አለ?
አቶ አብርሃም፡- በሁለቱም አቅጣጫ ጉድለቶች አሉ ማለት እንችላለን፡፡ በዋናነት በዳያስፖራው በኩል ፖለቲካውን የመቃወም አለ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ የአገርን ጥቅም እስማስነካት፣ የአገርን ሰላም እስከማደፍረስ፣ ተቋማት እስከ ማጥፋት ይሄዳል፡፡ ባለፈው በአገራችን ተፈጥሮ በነበረው ችግር የወደሙት ተቋማት የሕዝብና የአገር ናቸው፡፡ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሊሆን አይችልም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲና ድርጅት በአንድ ወቅት ይኖራል፣ በአንድ ወቅት ይቀየራል፡፡ ፖለቲካ ሁል ጊዜም ቅብብሎሽ ነው፡፡ በእኛ አገር ያልተለመደው አሁን ግን እየተለመደ መምጣት የጀመረውና ይቀጥላል ብለን የምናምነው ዘመናዊና በሳል የሆነ አመለካከት እየመጣ ነው፡፡ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ቢሆን፣ የተጀመረውን የሚቀጥል፣ ከነበረው በተሻለ አጠናክሮና አሻሽሎ የሚሄድ የጎደለውን እየሞላ የሚሠራ ይመጣል ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም ሁላችንም ልንሠራ ይገባል፡፡ በዳያስፖራው በኩል አገርንና ፖለቲካን፣ ልማትና ፓርቲን ለይቶ ያለማየት ነገር አለ፡፡ የፖለቲካ ልዩነትና አስተሳሰብ ሁሌም ይኖራል፡፡ ልናቆመው አንችልም፣ ጥሩም ነው፡፡ በዳያስፖራው በኩል መሆን ያለበት በፖለቲካው በኩል በሰላማዊ መንገድ መወያየት ነው፡፡ መነጋገር ይቻላል፣ መድረክም አለው፡፡ ልማትንና አገራዊነትን ከፖለቲካ ነጣጥለን ማየት አለብን፡፡ ዳያስፖራው አገር ቤት የሚመጣው ለማልማት ነው፡፡ ሆኖም አንዳንዴ የመንግሥት ደጋፊ ተደርጎ ስም የሚሰጥበት ሁኔታ አለ፡፡ ማኅበራችንም የዚህ ሰለባ ሆኗል፡፡ ሆኖም ማኅበራችን ከሃይማኖትና ከፖለቲካ የፀዳ፣ ዳያስፖራውን ለልማትና ለኢንቨስትመንት የሚያግዝ ነው፡፡ ነገር ግን ማኅበሩን የመንግሥት መጠቀሚያ አድርገው የሚያስቡ አሉ፡፡ አገር ቤት የሚደረገውን ሁሉ ፖለቲካዊ ነው ብሎ መፈረጅም አግባብ አይደለም፡፡ እነዚህ በዳያስፖራው በኩል መስተካከል አለባቸው ብለን እናምናለን፡፡ አመለካከቱ እንዲዳብርም በማኅበራችን በኩል የተቻለውን ጥረት እናደርጋለን፡፡ አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ዳያስፖራዎች ጥቂት ቢሆኑም ብዙው ሠርቶ የሚገባና የአገሩን ጥሩ ነገር የሚፈልግ ነው፡፡ ሆኖም መንግሥት ከዳያስፖራው ጋር በመቀራረብ፣ በኤምባሲዎች የአገራችንን ገጽታ በማሳየት፣ ትክክለኛው አካሄድ ምን መምሰል እንዳለበት ተቀራርቦ በመሥራት ሕዝብን በማወያየት፣ በዳያስፖራው የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎችን በመመለስ ጠንካራ የኢኮኖሚ ጥቅም እንዲሆን በማድረግ ምን ያህል ሠርቷል የሚለው መታየት አለበት፡፡ በጥቂቶች ሰበብ መበረዝ የለበትም፡፡ ዳያስፖራው ከተለያየ አቅጣጫ ያለውን አመለካከት ማየት እንዲችል መንግሥት በኤምባሲዎች በኩል መሥራት የነበረበት ግን ያልሠራው በርካታ ክፍተት አለ ብለን እናስባለን፡፡ እንደ ዳያስፖራ ማኅበር ዓይነት ገለልተኛና ነፃ ማኅበራት ሲኖሩ በመንግሥት በኩል እነሱን በማበረታታትና በማጠናከር፣ በመካከል ያሉ ውጥረቶችን እንዲያለዝቡ መሥራት አለበት፡፡ ዳያስፖራዎች ዜጎች ናቸው፡፡ የፖለቲካና የአስተሳሰብ ልዩነት ሊኖር ይችላል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጭራሽ ፈጽሞ የሌለ ነገር በውጭ አገር ስለሚነገርና ሰላማዊው የኅብረተሰብ ክፍልም የዚህ ሰለባ ስለሚሆን መንግሥት ይህንን የማስረዳት ኃላፊነት አለበት፡፡ በመንግሥት በኩል ከዳያስፖራው ጋር ለመወያየት ዝግጁነት አለ በተባለ ጊዜ በእኛ በኩል አብረን ለመሥራት ዝግጁ ነን፡፡ የጋራ መድረኮች ይኖራሉ ብለንም እንጠብቃለን፡፡
ሪፖርተር፡- የውጭ ዜጋ በፋይናንስ ተቋማት መሳተፍ እንደማይችል በሕግ የተቀመጠ ቢሆንም፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከባንኮች በርካታ አክሲዮኖች ገዝተው ነበር፡፡ በዚህ ዓመት ግን መንግሥት በሰጠው መመሪያ መሠረት አክሲዮኖቻቸውን እንዲሸጡ ተገደዋል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ልማት እየተሳተፈ ያለውን ዳያስፖራ አስኮርፏል ይባላል፡፡ ማኅበራችሁስ ምን ይላል?
አቶ አብርሃም፡- ማኅበሩ ችግሩ ከመፈጠሩና አባሎቻችን አቤቱታ ከማቅረባቸው በፊት ሕጉ ምን ይላል? መመሪያውስ? ሕጉና መመሪያው ከነበረ ባንኮች የዳያስፖራውን ገንዘብ ተቀብለው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንዴት ተደረገ በሚሉትና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ስንጻጻፍና ስንጠይቅ ቆይተናል፡፡ በኋላም በመንግሥት በኩል እኛ የማናያቸው መንግሥት የሚያያቸው፣ ከአገር ጥቅም ጋር በማስተሳሰር የተነሱ ጉዳዮችም ነበሩ፡፡ ስለሆነም በአባሎቻችን የሚነሱ ጥያቄዎች ቢኖሩም በእኛ በኩል ያሉትን ቅሬታዎች አጠናክረን መንግሥት ምላሽ እንዲሰጥ የማመቻቸት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ አባሎቻችን የአገርን ኢኮኖሚ ሳይጎዱ አገርንና ራሳቸውን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ ሥራዎች ሠርተዋል፡፡ በመሆኑም የአገርን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማይጎዳ መልኩ ሌላ አማራጭ የለም ወይ? በሚል አማራጭ ማቅረብ እንችላለን ብለው በግላቸው አጥንተው ለመንግሥት ለማቅረብ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ አባላት እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በማኅበራችን በኩል የምናደርገው መንግሥት አንዴ ስለወሰነ አክሲዮን ድርሻ የገዙ አባሎቻችን በተቀመጠው አካሄድ መሠረት ድርሻቸውን እንዲወስዱ ማስተዋወቅ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የዳያስፖራው ፖሊሲ ሲወጣ ትውልደ ኢትዮጵያውን በምርጫ የሚሳተፉበት ሁኔታ እንደሚመቻች አካቷል፡፡ ተፈጻሚ ግን አልሆነም፡፡ አባሎቻችሁ ይህንን ያነሱላችኋል?
አቶ አብርሃም፡- ቀጥታ ከምርጫ ጋር ባይያያዝም የሚነሳው ጥያቄ ጥምር ዜግነት የማግኘት ነው፡፡ የዳያስፖራው ተሳትፎና ድምፅ ከፍ እንዲል፣ በኢኮኖሚውም ተፅዕኖ ስላለው፣ በፖለቲካውም በውጭ ያለው ተፅዕኖ አሉታዊና አዎንታዊው ቀላል ስላልሆነ፣ የዳያስፖራው ተሰሚነት እንዲያድግ ዳያስፖራውን ሊወክል የሚችል በተወካዮች ምክር ቤት መኖር አይገባም ወይ? ዳያስፖራውን የሚመለከት ደንብ፣ ፖሊሲና አዋጅ ሲወጣ በቀጥታ ዳያስፖራውን ያሳተፈ አይደለም የሚሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ክፍተቶችም ይታያሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹የውጭ ዜጎች›› እየተባለ የሚወጣ አዋጅ ትውልደ ኢትዮጵያውያኑን ያላገናዘበ ነው፡፡ በዚህም መታወቂያ ለማደስ፣ የልደት ሰርተፍኬት ለማግኘት የተከለከለበት ሁኔታ አለ፡፡ ይኼ ሕጎች ሲወጡ የትውልደ ኢትዮጵያውያኑን ጉዳይ የሚመልሱ ካለመሆናቸው የተነሳ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ለመቅረፍ ከላይ ጀምሮ ስለ ዳያስፖራው ጥሩ አመለካከት እንዲኖር በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ዳያስፖራውን የሚወክል በፓርላማ ሊኖር ይገባል፡፡ ይኼ ካልሆነ ለዳያስፖራው ዳያስፖራውን የማያውቁ፣ ሕይወቱንና ችግሩን የማይገነዘቡ ሰዎች ሕግ ሊያወጡለት ይችላሉ፡፡ በፓርላማ ደረጃ መወከል ከቻልን መንግሥት ትኩረት ሰጥቶናል እንላለን፡፡ በሌሎች አገሮች በሚኒስቴር ደረጃ አላቸው፡፡ ዳያስፖራው ቁጥሩና የኢኮኖሚ ጥቅሙ ከፍተኛ ከሆነ በሚኒስቴር ደረጃ ሊመራ ይገባዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ያነሰ ቁጥር ያላቸው አገሮች በሚኒስቴርና በኮሚሽን ደረጃ አዋቅረዋል፡፡ በእኛ አገር ዳያስፖራው በሚኒስቴር ደረጃ ለምን አይዋቀርም? የሚል ጥያቄ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከዳያስፖራው መጠቀም ያለባትን ያህል አልተጠቀመችም፡፡ በሚኒስቴር ደረጃ ቢዋቀርና ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሆን ብዙ ችግሮች ይፈታሉ፡፡ አሁን ያለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሥር በዳይሬክተር ጄኔራል ነው፡፡ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ብዙ ሥራ አለበት፡፡ በዛ ላይ አንገብጋቢ የሆነው የዳያስፖራው ጉዳይ ሲጨመር ሊሰጠው የሚችለው ትረኩት የጠነከረ አይሆንም፡፡ ኢኮኖሚው ድህነትን እንዲያጠፋ የምናግዝና የዳያስፖራው አበርክቶ አስፈላጊ ከሆነ ዳያስፖራው የሚዋቀርበት መንገድ መፈተሽ አለበት በሚኒስቴር ደረጃ ሊዋቀር ይገባዋልም ብለን እናምናለን አባሎቻችንም ይኼንን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በዓረብ አገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በተለይም በቤት ሠራተኝነት የሚሄዱት ተጎጂ እንደሆኑ በተለያየ ጊዜ ተረጋግጧል፡፡ እንደ ዳያስፖራ ማኅበር በዓረብ አገር ለሚገኙ ዜጎች መብት ምን ሠርታችኋል?
አቶ አብርሃም፡- በገልፍ አገሮች የጀመርናቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ማኅበራችን ዜጎቻችን ከሚያቀርቡት ፍላጎት ጋር ተያይዞ የሚሠራው ሥራ አለ፡፡ ዳያስፖራው የበለጠ ችግር ያለበት የት አካባቢ ነው? ስንል መጀመሪያ የሚመጣው ገልፍ አገሮች ነው፡፡ ማኅበሩም ይህ እጅጉን ያሳስበዋል፡፡ አሜሪካና አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ለመክፈት ዕቅድ ቢኖረንም፣ በዋናነት ቅድሚያ የሰጠነው ዓረብ አገሮች ላይ ለመክፈት ነው፡፡ ከስድስት ወር በፊት የልዑካን ቡድን ይዘን ሳውዲ ዓረቢያ ሄደን ነበር፡፡ ከዓረብ አገር ኢትዮጵያውያን ሲመለሱ በኤርፖርት በኩል የሚገጥማቸው ችግር አለ፡፡ አገራቸው እንደሚመጡ ሳይሆን እንደምንም ተቆጥረው ይዘለፋሉ፣ ይገፋሉ፣ ክብርም አይሰጣቸውም፡፡ ስለሆነም በኤርፖርት ዙሪያ ያሉና ከገቢዎችና ጉምሩክ ኃላፊዎችን ይዘን በመነጋገር በጉዳዩ ላይ መፍትሔ እንዲደረግ አድርገናል፡፡ ከሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከባንክ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ከማኅበሩ የተውጣጡ ልዑካን ይዘን በጅዳና በሪያድ ጉዞ አድርገን ችግሩን ለመረዳት ሞክረናል፡፡ ሪፖርቱንም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሚመለከተው አካል አቅርበናል፡፡ ምላሹም እየጠበቅን ነው፡፡ የማኅበሩ ቅርጫፍ ቢሮ እንዲኖርም ጅማሮዎች አሉ፡፡