Saturday, July 13, 2024

በዝግታ እያደገ ያለው ግድብ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ሱዳንና ግብፅ ህልውናቸው በዓባይ ወንዝ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱ አገሮች አብዛኛው የመሬት ክፍላቸው በበረሃ የተሸፈነ ነው፡፡ 86 በመቶ የሚሆነው የውኃ መጠን ዋነኛ ምንጭ ከኢትዮጵያ የሆነው የዓባይ ወንዝ ከአገሩ ሲወጣ ‹‹ናይል›› የሚል ስያሜ ይሰጠዋል፡፡ ይኼ ወንዝ ከዓመታት በፊት ጀምሮ በተፋሰስ አገሮቹ መካከል የፀብና የጥላቻ መንስዔ መሆን የጀመረው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡

በአብዛኛው ይህ ጥላቻና ፀብ ደግሞ የበለጠ እየከረረ የሄደው ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት አቅዳ ከነበረበት የንጉሣዊ ሥርዓት ጀምሮ እንደሆነ ታሪክ ያስረዳል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ‹‹ዓባይ የኢትዮጵያ ነው፡፡ ንብረታችንን ደግሞ የመጠቀም መብቱ በእጃችን ነው፤›› ብለው በተናገሩበት ጊዜ በግብፅና በሱዳን መንግሥታት ዘንድ ከፍተኛ ቅራኔ አስከትሏል፡፡ ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ የውጭ ወራሪ ኃይልን የመመከት አቅም እንዳላት ትምህርት ከሰጠችበት ታላቁ ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓደዋ ድል በኋላ፣ በአፍሪካ በተለይም በምሥራቅ አፍሪካ ተሰሚነቷ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከኃይል ዕርምጃ ይልቅ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶች የተሻሉ ናቸው በማለት የወቅቱ የግብፅ ፕሬዚዳንት እስማኤል ፓሻ አንድ ጆንያ ሙሉ ወርቅና ሌሎች ዕቃዎችን አስይዘው ለንጉሡ በሥጦታ መልክ እንደላኩ የሚነገረው፡፡

ግብፅ የታላቁ የህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያ እንዳትገነባ ለጋሽ ድርጅቶች ዕርዳታ እንዳያደርጉ ከመወትወትና ከማግባባት ባሻገር፣ ወታደራዊ ዕርምጃ ለመውሰድ አቅዳ እንደነበር በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 ዊኪሊክስ የአሜሪካ የደኅንነት ቢሮን ጠቅሶ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ ሱዳንና ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ለመክፈትና የህዳሴውን ግድብ ለማፍረስ አቅደው ነበር፡፡ ሆኖም ሁለቱ አገሮች መረጃውን ‹‹ሐሰት›› ሲሉ ማጣጣላቸው ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ‹‹አፍሪካን ኢንተለጀንስ›› የተባለ ተቋም በቅርቡ ይፋ ያደረገው መረጃ እንዳመለከተው ደግሞ፣ የግብፅ መንግሥትና ተቋማት ከእጅ አዙር ጥቃት ባሻገር የአፍሪካ አገሮችን በማስተባበር በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያደርጉ መንቀሳቀሳቸውን አረጋግጧል፡፡ መረጃው በቅርቡ ማለትም እ.ኤ.አ. ከመስከረም 13 እስከ 20 ቀን 2016 በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጉባዔ ላይ፣ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የአፍሪካ አገር መሪዎች በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብና ሌሎች ዕገዳዎች እንዲያደርጉ ሲወተውቱ እንደነበር ይፋ አድርጓል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐመድ ቡሃሪ፣ የሶማሊያዊው ፕሬዚዳንት ሁሴን ሼክ መሐመድ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያለችውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመቃወም እንዲተባበሯቸው መጠየቃቸውም ተዘግቧል፡፡

ምንም እንኳ ግብፅ የኢትዮጵያን የበላይነት በጉንደትና በጉራዕ የጦር ሜዳዎች ላይ ያየች ቢሆንም፣ ከማንገራገርና ከማስፈራራት ግን አልተቆጠበችም ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ አገሮች ከእሷ ጎን እንዲቆሙ ስትጠይቅና ስትማልድ ቆይታለች፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገንባት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. መሠረት ከጣለችበት ጀምሮ የዓለም ባንክም ሆነ ሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ለግድቡ ዕርዳታ እንዳይሰጡ ያደረጉትን ጉትጎታና ውትወታ ማስታወስ ይቻላል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መሠረት በተጣለበት ጊዜ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ‹‹ግድቡን ለመሥራት ብድርና ዕርዳታ እንዳናገኝ የተለያዩ ኃይሎች ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ ምክንያት፣ የፕሮጀክቱን ወጪ ለመሸፈን የሚተባበረን አገር ወይም ተቋም ማግኘት አልቻልንም፡፡ ስለሆነም ወጪውን ብቻችንን ለመሸፈን የምንገደድበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የፕሮጀክቱ የገንዘብ ወጪ ከ3.3 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ወይም 78 ቢሊዮን ብር በላይ በመሆኑና ከዚህ ፕሮጀክት በተጨማሪ ሌሎች በራሳችን ወጪ ልንሸፍናቸው የሚገቡን በርካታ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ወጪውን መሸፈን በእጅጉ እንደሚከብደን ጥርጥር የለውም፡፡ ሸክሙን ለማቃለል ያደረግነው ጥረት ስላልተሳካና ያለፉት 50 ዓመታት ታሪካችን እንደማይሳካ ያረጋገጡልን በመሆኑ የሚኖረን አማራጭ አንድም ግድቡን አለመሥራት፣ አለበለዚያ እንደምንም በራሳችን መሸፈን ነው፡፡ ከእነዚህ ከባድ ሁለት አማራጮች መካከል የኢትዮጵያ ሕዝብ ምርጫ የትኛው እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡ በተለመደው ወኔው ምንም ያህል ደሃ ብንሆንም ድህነታችንን ለማስወገድ ማንኛውም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን፡፡ ስለዚህ ፕሮጀክቱ መሠራት አለበት እንደሚል ለአፍታም ያህል አልጠራጠርም፤›› ብለው ነበር፡፡ በዚሁ እሳቤ የተጀመረው የግድብ ግንባታ ዛሬ 57 በመቶው ተጠናቋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ለመገንባት ሥራው ከተጀመረ እነሆ ድፍን ስድስት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ለአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ነው፡፡ አገሪቱ ካላት 1.1 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ውስጥ አንድ ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ያህል ደረቅ፣ 104,300 ካሬ ኪሎ ሜትር ያህሉ ደግሞ በውኃ የተሸፈነ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በተለያዩ የገጸ ምድርና ከርሰ ምድር ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች ብትሆንም በኃይል ልማቱ ከፍተኛ ውስንነቶች የነበሩባት አገር ነች፡፡

እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳይ ከዚህ ውድድር ከተያዘበት የግሎባላይዜሽን ዘመን ጋር አብሮ አስተሳስሮ ለመሄድ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ለዚህም የዓለም አገሮች እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማርካት ብዙ ሲሠሩ ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያም በአሁኑ ወቅት ይህንን ክፍተት ለመሙላት በእንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም ዋነኛው ማሳያ በአፍሪካ አንደኛ፣ በዓለም ደግሞ ስምንተኛ ደረጃ ይዟል የሚባለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ነው፡፡

ይህ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያን አቋርጦ ለመውጣት ሃያ ኪሎ ሜትሮች ሲቀሩት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉባ ወረዳ ውስጥ እየተገነባ ይገኛል፡፡ 246 ኪሎ ሜትሮች ያህል ከዋናው ግድብ ርቆ ሰው ሠራሽ ሐይቅ ይፈጠርለታል፡፡

የህዳሴ ግድቡ ሁለት ዓይን ለዓይን የሚተያዩ የነበሩ የተራራ ሰንሰለቶችን ያገናኘና 145 ሜትር ከፍታ፣ 1.8 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ደብረ ማርቆስ፣ እንጅባራና ቻግኒ ከተሞችን በማቋረጥ በ730 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሲገኝ፣ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ ነቀምትና አሶሳ ከተሞችን በማቋረጥ ደግሞ በ830 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡

አማካይ የውኃ ፍሰት መጠኑም 1,547 ኪዩቢክ ሜትር ሲሆን፣ ይህ በተፋሰስ አገሮቹ መካከል ጂኦ ፖለቲካዊ ፋይዳው ጉልህ የሆነ ወንዝ ለኢትዮጵያ ዋናውን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ሥራ ከተጀመረ ድፍን ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. የግንባታ የመሠረት ድንጋዩ የተጣለው የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 57 በመቶ ተጠናቋል፡፡

የግንባታው የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ዕለት ምክንያት በማድረግም በየዓመቱ መጋቢት 24 ቀን ግድቡ በሚገኝበት ሥፍራ ክብረ በዓል ይደረጋል፡፡ በተለያዩ ዓመታት የተለያዩ መሪ ቃላት የሚወጡለት ይህ ክብረ በዓል ዘንድሮም ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድባችን የአገራችን ኅብረ ዜማ፣ የህዳሴያችን ማማ›› በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በተለያዩ ዝግጀቶች ሲከበር ቆይቷል፡፡

ሪፖርተርም የዚህን የመዝጊያ ሥነ ሥርዓት በጉባ ተገኝቶ ለመከታተል ችሏል፡፡ ጉባ ከአሶሳ 240 ኪሎ ሜትር ያህል የሚርቅ ሥፍራ ሲሆን፣ የአየር ንብረቱ ደግሞ ሞቃታማ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ እየተገነባ ያለው ሁለት የተራራ ሰንሰለቶችን በማገናኘት ነው፡፡ ግድቡ ከሚገነባበት አካባቢ ታችኛው የጉባ ወረዳ ወደ ደቡብ ምሥራቅ ቆሞ ለሚመለከት ሰው በስተምሥራቅ ቢለን  ተብሎ የሚጠራውና ሰው ሠራሽ ሐይቁ የሚፈጠርበት ሥፍራ፣ በስተምዕራብ ደቡብ በኩል ሶዳል ወይም ሲርባባ፣ በስተምዕራብ በኩል ደግሞ የአባ ጉበንና አጋሚቲ ተብለው የሚጠሩ ሥፍራዎችን የሚዋሰን ነው፡፡ በስተሰሜን ደግሞ ወንበራ ወረዳ ያዋስነዋል፡፡ የአካባቢው የሙቀት መጠንም ከ40 እስከ 50 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደሚደርስ የሚቲዮሮሎጂ መረጃዎች ያመለክታል፡፡

ወታደር ቢያድግልኝ ካሳ (የአባቱ ስም ተቀይሯል) ይባላል፡፡ ዕድሜው 31 ዓመት እንደሆነ ለሪፖርተር የሚናገረው ወታደር ቢያድግልኝ ከዋናው ግድብ 30 ሜትር ርቀት አካባቢ ወታደራዊ የደንብ ልብሱን ለብሶና ታጥቆ ቆሟል፡፡ የቀኝ እጅ ጣቱን በክላሽኒኮቭ ጠመንጃው ምላጭ ላይ ደቅኖ የህዳሴ ግድቡን በአራቱም አቅጣጫ በአትኩሮት ይመለከታል፡፡ ግድቡን ለመጠበቅ ጉልበቱ ሳይዝልና ሙቀቱ ሳይበግረው በተንጠቀቅ ቆሞ አካባቢውን በንቃት የሚከታተለው ወታደር፣ ‹‹ይህ ግድብ በአራቱም አቅጣጫ የደኅንነቱ ጉዳይ በማያሳስብ ሁኔታ እየተጠበቀ ነው፤›› ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

የህዳሴ ግድቡን የደኅንነት ጉዳይ በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአገር መከላከያ ሠራዊትና የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ባልደረባ ምክትል መቶ አለቃ ፈለቀ ሰማኸኝ፣ ‹‹ግድቡ ያለምንም እንቅፋት ተሠርቶ እስኪያልቅ ድረስና ካለቀ በኋላም ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን፣ ከውስጥ እስከ ውጭ በሦስት አደረጃጀቶች እየተጠበቀ ነው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና በዓባይ ጉዳይ በርካታ የምርምር ሥራዎችን ያሳተሙት ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ይህ ግድብ አንዱ ሌላውን በማይጠልፍበትና በማይጎዳበት መርህ ላይ ተመሥርቶ የተገነባ ነው፡፡ ወደፊትም በተፋሰስ አገሮች መካከል የጂኦ ፖለቲካዊ ትስስርን በመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ሌሎች አገሮች ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ቢኖሩዋቸውም ይህ ግን በተምሳሌትነቱ ጎልቶ የሚታይ ግድብ ነው፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

ብዙዎች ይህ ግድብ ‹የይቻላል መንፈስ› የፈጠረ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ይህን ሐሳብ የበለጠ የሚያዳብረው ደግሞ የቀድሞው አትሌት ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ማርያም ነው፡፡ ገብረ እግዚአብሔር የግድቡ ስድስተኛ ዓመት የመሠረት ድንጋይ የተጣለበትን ዕለት በማስመልከት በሥፍራው ተገኝቶ የሩጫውን ውድድር ሲያስተባብር  በሰጠው አስተያየት፣ ‹‹ግድቡ እንችላለን በማለት የምንችል መሆናችንን ለዓለም የምናሳይበት አንዱ መሣሪያ ነው፤›› ብሏል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኪሼን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የህዳሴ ግድቡን ለመሥራት የሕዝባችን ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ትልቁ የኢትዮጵያ የልማት አንቀሳቃሽ ሞተር ነው፡፡ ሥጋት ያለባቸው አገሮች ከሥጋታቸው ነፃ እንዲሆኑ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ከማድረግ ባሻገር፣ ባሉን የመረጃ መረቦች እየተጠቀምን ግድቡ ሰላማዊ መሆኑን ለዓለም እየገለጽን ነው፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አንዳንድ ወገኖች ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ወንድ፣ ሴት፣ ልጅ፣ አዋቂ፣ ተቃዋሚና ደጋፊ ሳይል እየተገነባ ያለ ግድብ ነው ይላሉ፡፡ ይህን ሐሳብ የሚያጠናክሩት ደግሞ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ መሥራችና የወቅቱ ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ ናቸው፡፡ አቶ ተሻለ ፓርቲያቸው ቦንድ ከመግዛት ባሻገር ለፓርቲ ሥራ አገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር በሚንቀሳቀስበት ጊዜ ስለግድቡ ጠቀሜታ በማስረዳትና ኢትዮጵያውያን ድጋፍ እንዲያደርጉ ትምህርት እንደሚሰጡ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ይህ ግድብ የመላው ሕዝብ ግድብ ነው፡፡ የሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰቦች ግድብ የማንነታችን ትልቁ ማኅተም በመሆኑ ዕውን እስኪሆን ጥረታችን ይቀጥላል፤›› በማለት ጉባ ተገኝተው አስተያየታችን ሰጥተዋል፡፡

‹‹የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለበት ዕለት ጀምሮ የኢትዮጵያ ደራሲያንና የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች በብዕራቸው ቀለም ለትውልድ ለማስተላለፍ በመጽሐፍ መልክ ከትበውታል፣ ዜማ ተቀኝተውለታል፣ ገጥመውለታል፤›› የሚሉት ደግሞ የወቅቱ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ፕሬዚዳንት ሙሴ ያዕቆብ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ስድስተኛ ዓመት ክበረ በዓል በጉባ ሲካሄድ በክብር እንግድነት የተገኙት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ሲሆኑ ሚኒስትሮች፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችና ሌሎች የአመራር አካላትም ተገኝተው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሙላቱ፣ ‹‹ግድቡ እዚህ ደረጃ የደረሰው ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጉልበታቸው፣ በገንዘባቸውና በዕውቀታቸው ድጋፍ በማድረጋቸው ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ለልማት ጉዞ የጀመርነው አቅጣጫ ነፀብራቅ በመሆኑ፣ ዛሬ በማገባደድ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ ፕሮጀክት በጋራ ተጠቃሚነትና በፍትሐዊነት መርህ ላይ ተመሥርቶ እየተገነባ ያለ ፕሮጀክት በመሆኑ የሁሉም የዓባይ ተፋሰስ አገሮች የኢኮኖሚ ትስስርን የሚያጎለብትና የሚያዳብር የሰላም ምንጭ ሆኖ እንደሚያገለግል እምነታችን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ‹‹ፕሮጀክቱ ከግብ እንዲደርስና ኢትዮጵያን የመገንባት፣ የማዘመን፣ የማልማትና ሕዝቡም ፍትሐዊ ተጠቃሚ እንዲሆን ለማብቃትና ወደ ላቀ ከፍታ እንዲደርስ የቀየስነው የህዳሴ ጉዞ በመላው የአገራችን ሕዝቦች ልብ ውስጥ በቅቡልነት መጓዝ አለበት፤›› የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ሰብሳቢ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በበኩላቸው፣ ‹‹ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የህዳሴውን ትውልድ ቁርጠኝነት ያስተጋባ፣ በይቻላል መንፈስ በአንድ ቋንቋ ያግባባ፣ ለወዳጅና ለጎረቤት አገሮች አርቆ አስተዋይነትን ያስመሰከረ ነው፡፡ ይህ ብርቅዬ ፕሮጀክታችን በአራቱም ማዕዘናት የፈጠረው ሕዝባዊ ማዕበልና ርብርብ ከራሱ አልፎ ሌሎችን ሥራዎች መሥራት እንደሚቻል ያስመሰከረ ነው፡፡ ይህም የታሪክ ሠሪነታችን ቁጭት ጎልቶ እንዲስተጋባ የህዳሴያችን ጉዞ ክስተት ነው፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ (ኢንጂነር) በበኩላቸው፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት መንግሥት በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ኢንዱስትሪዎችን እየገነባ ይገኛል፡፡ ለዚህም የኤሌክትሪክ ኃይሉ ፍላጎት እያደገ የመጣ ሲሆን፣ ይህን ፍላጎት ለማሟላት ይህ ግድብ ከፍተኛ ዋጋ አለው፤›› ብለዋል፡፡ አክለውም፣ ‹‹በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን በኤሌክትሪክ ኃይል መጀመሪያ ላይ ከነበረበት 4,250 ሜጋ ዋት ወደ 17,000 ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዷል፡፡ አሁን ያለው የማመንጨት አቅምና የታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን ጨምሮ በመገንባት ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች ባሻገር በዕቅድ ዘመኑ ከ7,000 ሜጋ ዋት በላይ ሊሰጡ የሚችሉ የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ይጠበቅብናል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ በተጓዘባቸው ስድስት የግንባታ ዓመታት የግድቡ ሮለር ኮምፓክት ኮንክሪት (አርሲሲ) ግንባታው 70 በመቶ፣ የሳድል ግንባታ 57 በመቶ መጠናቀቁን ገልጸው፣ ከዚህ በተጨማሪ የኃይል ማመንጫ ቤቶች ግንባታ፣ የ500 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ፣ የ125 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መዳረሻ መንገዶችና ከግድቡ በታች 240 ሜትር ርዝመት ያለው ድልድይና የአውሮፕላን መንደርደሪያ ሜዳ ግንባታ መከናወናቸውን አስረድተዋል፡፡

በተመሳሳይ የኤሌክትሮ መካኒካልና የኃይድሮ መካኒካል ሥራዎች የዲዛይን፣ የአቅርቦት፣ የተከላና የፍተሻ ሥራዎች በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በተፋጠነ ሁኔታ እየከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ በተለይም ቀድመው ኃይል የሚያመነጩ ሁለት ዩኒቶች የተከላ ሥራቸው እየተገባደደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ የተቀሩት አሥራ አራት ዩኒቶች ተከላ በስፋት የቀጠለ መሆኑን አብራርተው፣ በዚህም የተነሳ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የግንባታ ሒደት በአሁኑ ወቅት 57 በመቶ መድረሱን አስረድተዋል፡፡  

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተገነባው የአባ ሳሙኤል ግድብ የተጀመረውን የስድስት ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም፣ ከአንድ ማመንጫ ጣቢያ ብቻ 6,450 ሜጋ ዋት ያሳደገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ይህ ግድብ ሲጠናቀቅም ከ6,450 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይልና በአማካይ 15,759 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል በዓመት በማመንጨት፣ ለአገር አቀፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ትስስር ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በዝግጅቱ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል 1,874 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋትና 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያለው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ስለሚፈጥር፣ በአካባቢው በታንኳና በጀልባ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሁም ተጨማሪ የዓሳ ሀብት ልማት ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገልጿል፡፡

የውኃ ኃይል ማመንጫ ከካርቦን ዳይኦክሳይድ ልቀት ነፃ በመሆኑ፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአካባቢ ሥነ ምኅዳርንም በመጠበቅ ረገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

በግድቡ ግንባታ ሒደትም እስካሁን 10,958 ያህል ሠራተኞች የተሰማሩ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 353 (ሦስት በመቶ) ያህሉ የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡ የዕውቀት፣ የአሠራር ልምድና ክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር በማስገኘት ረገድም ጉልህ ሚና እንዳለው ተገልጿል፡፡

ዓባይ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች ተነስቶ ወደ ሱዳንና ግብፅ ይፈሳል፡፡ ሱዳን ድንበር ላይ ሲደርስ የወንዙ ዓመታዊ የፍሰት መጠንም 50.6 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በመሆኑም ይህ ግድብ ሱዳን በጎርፍ እንዳትጎዳ ከማድረግ ባሻገር የተመጣጠነ ውኃ ሁሌም እንዲኖር በማድረግ ጥቅም እንዳለው በተለያዩ የመንግሥት አካላት ተብራርቷል፡፡ ለግብፅም የውኃ ትነትና ግድቦቿ በደለል እንዳይሞሉ በማድረግ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ ተገልጿል፡፡  

የግንባታው ዋና ዋና ክፍሎችን በተመለከተም ዋናው ግድብ መጠኑ 10.1 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር አርሲሲ ኮንክሪት ሙሌት ቴክኖሎጂ የሚገነባ እንደሆነ፣ ይህም ከጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ቀጥሎ ዝቅተኛ የሲሚንቶ መጠን የሚጠቀምና ወጪ ቆጣቢ ቴክኖሎጂ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ከግድቡ በስተኋላ የተጠራቀመውን ወደ እያንዳንዱ የኃይል ማመንጫ ዩኒት ውኃ የሚያደርሱ 16 የብረት አሸንዳዎችና የታችኞቹን አገሮች የውኃ ፍላጎት በማገናዘብ አገልግሎት የሚሰጡ ተጨማሪ ሁለት የግርጌ ማስተንፈሻዎች እንዳሉትም ወ/ሮ አዜብ ገልጸዋል፡፡

 የህዳሴ ግድቡ ለመድረስ 20 ኪሎ ሜትር ሲቀር የተጻፈ ማስታወቂያ ‹‹ድሮ ዓባይ ይጠጣ ነበር አሁን ግን ሊበላ ነው፤›› ይላል፡፡ ግድቡ ለምግብነት ለመድረስ አሁንም የሚቀር ከፍተኛ ሥራ ቢኖርም የሚቀረው ጊዜና ሒደት እንዳለፈው የሚከብድ ባለመሆኑ፣ ሁሉም ዜጋ በሚችለው መጠን ሁሉ ግንባታውን ለማጠናቀቅ እየተረባረበለት እንደሚገኝ እየተነገረ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -