Wednesday, April 17, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ለአገር የሚጠቅሙ ጥናቶች የአቧራ መጫወቻ አይሁኑ!

አገር በዘፈቀደ አይመራም፡፡ የአቅጣጫ መጠቆሚያ (Compass) ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በባለሙያ የታገዘ ጥልቀትና ስፋት ያለው፣ ለሚነሱ ሁለገብ ጥያቄዎች በብቃት ምላሽ የሚሰጥ፣ ለአሠራር ቀላልና አመቺ የሆነ፣ ከዘመኑ የዕድገት ደረጃ ጋር የሚጣጣምና ሁሉንም ወገን የሚያግባባ በጥናት ላይ ብቻ የሚመረኮዝ አሠራርና አመራር መኖር አለበት፡፡ በተለይ አመራሩ በሁሉም የሥራ መስኮች በጥናት መታገዝ ይገባዋል፡፡ አሁን እየታየ እንዳለው ግን ለአገር የሚጠቅሙ ጥናቶች መደርደሪያ ላይ አቧራ እየጠጡ ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት፣ የሰው ኃይልና ጊዜ የባከነባቸው በርካታ ጥናቶች የሚሠራባቸው በመጥፋቱ ብቻ በተለያዩ መስኮች እንቅፋቶች እየበዙ ነው፡፡ ሥራን በአግባቡ ለመሥራት የሚያውኩ ጋሬጣዎች በመብዛታቸው ብቻ መልካም አስተዳደር ማስፈን አልተቻለም፡፡ ፍትሕን ተደራሽ ማድረግ ዳገት ሆኗል፡፡ ሙስና እንደ ሰደድ እሳት አገር እየለበለበ ነው፡፡ ሕገወጦች በሕዝብ ላይ እየቀለዱ ነው፡፡ ራሳቸውን ከሕግ በላይ ያደረጉ ግለሰቦች በአገርና በሕዝብ ላይ እየፈነጩ ነው፡፡  የሕግ የበላይነት ቀልድ እየሆነ ነው፡፡ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

ገዥው ፓርቲ የሚከተለው መንግሥት መር የኢኮኖሚ ሞዴል ከብዙ ችግሮቹ ጋር ውጤት ማምጣቱ አይካድም፡፡ የእዚህ ፖሊሲ ዋና መነሻ ሐሳብ ደግሞ ዕድገትና ብልፅግና የሚገኘው ከምንም በላይ አገር በሚመራው አካል የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው ይላል፡፡ ይህ በእስያ አገሮች ልምድ የታየ [መንግሥት ይህንን ምሳሌ ይወደዋል] ነው የሚባልለት የገዥው ፓርቲ የፖለቲካ ተነሳሽነት ለተመዘገበው ‹አንፀባራቂ ዕድገት› መሠረታዊና ወሳኝ ነው ይባላል፡፡ ነገር ግን በፖለቲካ ቁርጠኝነትና በኢኮኖሚ ዕድገት መሀል ሊኖር የሚገባው ጥምረት ገደብ ሊበጅለት ይገባል፡፡ ይህ ማለት ከተወሰነ ደረጃ በኋላ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ በጥናት የሚታገዝና ሳይንሳዊ መሠረት ያለው አመራር ማምጣት ካልተቻለ ዕድገቱን በፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ብቻ ወደፊት መግፋት አዳጋች ይሆናል፡፡ በተለይ ወደፊት በኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በዝርዝር ጥናትና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ መተላለፍ አለበት፡፡ ይህ ደግሞ በጥናት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ አስፈላጊነትን አጉልቶ ያወጣዋል፡፡

የአገሪቱን ኢኮኖሚ በተመለከተ በርከት ያሉ የተዘጋጁ መረጃዎች አሉ፡፡ እነዚህን መረጃዎች የሚተነትንና የሚያደራጅ አካል አለመኖሩ ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡ ቀደም ሲል በተለያዩ ዘርፎች ጥናቶችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ለዘርፉ ተዋናዮች የሚያቀርቡት የጥናትና ምርምር ተቋማት መክሰም ደግሞ ክፍተቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡ አሁን ግን መንግሥት በራሱ በጀት የሚያስተዳድረው የፖሊሲና የምርምር ማዕከል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምሥጋና የሚቸረው ጥረት እያደረገ ነው፡፡ የአገሪቱን የመልካም አስተዳደር ችግሮችና የሕዝብ ተሳትፎ መገደብን አስመልክቶ በጥልቀት የሠራቸው ጥናቶች ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ችግሮችን ከሥር ከመሠረታቸው ያለምንም መሸፋፈን ባለድርሻ አካላት እንዲያውቋቸው ሲደረግ፣ አስፈጻሚው የመንግሥት አካልም ውሳኔ ለመወሰን አይቸገርም፡፡ አሁን እየታየ ያለው ችግር ግን እንዲህ ዓይነት ጥናቶች ቢቀርቡም ለመወሰን ማቅማማት ነው፡፡ ሕዝብን የሚያበሳጩት እንዲህ ዓይነቶቹ ተስፋ አስቆራጭ ድርጊቶች ናቸው፡፡

የጥናት ውጤቶች ሥራን በአግባቡ ለማከናወንና የሕዝብን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ ካልቻሉ ምንም ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የፖሊሲና የጥናት ማዕከል በመልካም አስተዳደር ችግሮች ላይ የተሠራ 800 ገጾች ያሉት የጥናት ሪፖርት ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበት ነበር፡፡ ነገር ግን የአገሪቱን የመልካም አስተዳደር ዕጦት ለማስተካከል ያደረገው አስተዋጽኦ በግልጽ አልታየም፡፡ መንግሥት በራሱ ተቋም የተሠራ ጥናትን አምኖ ተቀብሎ ማስፈጸም ካቃተው ተስፋው ምንድነው? ሌላው ቀርቶ በገለልተኛ አካላት የተጠኑ ጠቃሚ ጥናቶችን ለፖሊሲ ግብዓትነት መጠቀም ሲኖርበት፣ በከፍተኛ ድካም የተሠራ ጥናትን አቧራ ማጠጣት ያሳዝናል፡፡ በዚህ ዘመን በትሪሊዮን የሚቆጠር ብሔራዊ ሀብት ላይ ውሳኔ የሚሰጥ መንግሥት፣ የመረጃ ቋቱን በማጠናከርና ውሳኔዎቹንም በዚህ ላይ መመሥረት ካልቻለ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የልማትና ምርምር ተቋም (EDRI) ብዛት ያላቸው ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ የጥናት ሰነዶችን ያወጣል፡፡ በድረ ገጹ ላይ ሳይቀር በርካታ የጥናት ውጤቶች ይገኛሉ፡፡ ብዙዎቹ በሥራ ላይ እንዳልዋሉ የመንግሥት ደካማ ፖሊሲዎች ማሳያ ናቸው፡፡

በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግብይትን በተመለከተ በውጭ ኩባንያ አንድ ጠቃሚ ጥናት ተሠርቶ ነበር፡፡ በጥናቱ መሠረት የብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግብይት ሥርዓት ለችግር የተጋለጠ በመሆኑ፣ ተገቢ ጥንቃቄ እንዲደረግና አሠራሩ እንዲሻሻል ምክረ ሐሳብ ይቀርባል፡፡ በወቅቱ ለጥናቱ ተገቢው ትኩረት በመነፈጉ ብቻ አደገኛ ችግር ይፈጠራል፡፡ በወቅቱ በጋዜጦች በሰፊው እንደተዘገበው ወርቅ በማስመሰል የባሌስትራ ብረት እየቀረበ ባንኩ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ይዘረፋል፡፡ በፍርድ ሒደቱም ብዙ አስገራሚ ነገሮች ተሰምተዋል፡፡ ጠቃሚ ጥናቶች ችላ እየተባሉ አገር በጠራራ ፀሐይ ትዘረፋለች፡፡ በሕዝብ ኑሮ ላይ ጫና የሚፈጥሩ የተዝረከረኩ አሠራሮች እንዲወገዱ የሚጠቅሙ ጥናቶች አቧራ እየጠጡ፣ ሕዝብን የሚያስመርሩ ድርጊቶች ይፈጸማሉ፡፡ ብቃት የሌላቸውና የአገር ጉዳይ ደንታ የማይሰጣቸው ሕግ እየጣሱ ሲዘርፉ፣ ፍትሕ ሲያጣምሙ፣ በስልክ ትዕዛዝ ያሻቸውን ሲያስፈጽሙ፣ ባለሙያዎችን አላሠራ ሲሉ፣ በአገር ላይ ቀውስ እንዲፈጠር ሲያደርጉ፣ ወዘተ ዝም ይባላል፡፡ መጠነኛ መፍጨርጨሮች ቢታዩም በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ በመሆናቸው ብቻ ውጤታቸው ፋይዳ ቢስ ነው፡፡

መንግሥትን የሚመራው አስፈጻሚው አካል በአግባቡ ሥራውን ማከናወን ሳይችል ሲቀር ተጠያቂነት አለበት፡፡ በሕገ መንግሥቱ አስፈጻሚው አካል አሠራሩ ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ አስፈጻሚውን አካል የሚቆጣጠረው ሕግ አውጪ  (ፓርላማ) ለመንግሥት ግብዓት መሆን ያለባቸው ጥናቶች ትኩረት ሲነፈጋቸው ማፋጠጥ አለበት፡፡ በበርካታ መድረኮች ላይ የመንግሥት አሠራር ግልጽነት ማጣትና ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ መንጎዱ በተደጋጋሚ ሲሰማ ዝምታው እስከ የት ድረስ ነው? የመንግሥት አሠራርንና ተጠያቂነትን በሚመለከት ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ መሆኑ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጓል፡፡ ሕዝብ በመረጠው ተወካይ ላይ እምነት ባጣ ጊዜም ከቦታው ማንሳት ይችላል፡፡ አስፈጻሚው አካል በመርህ ላይ ተመሥርቶ መሥራት ሲያቅተው ሕግ አውጪው ካልተቆጣጠረው ኃላፊነቱን አልተወጣም ማለት ነው፡፡ አገርን በፖለቲካ ቁርጠኝነት ብቻ ለመምራት አይቻልም፡፡ በጥናት ላይ ያልተመሠረተ አሠራር ለጊዜው ቢሳካ እንኳ ዘለቄታ የለውም፡፡ ጥናቶች ተለፍቶባቸው ለአስፈጻሚው አካል ሲቀርቡ ሥራ ላይ መዋል ይገባቸዋል፡፡ ሕግ አውጪውም የመቆጣጠር ኃላፊነቱን መዘንጋት የለበትም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት እየጠፉ አገር ስትበደልና ሕዝብ የመከራ ገፈት ቀማሽ ሲደረግ በሕግ መባል አለበት፡፡ የሁሉም ነገር ማጠንጠኛው የሕግ የበላይነት ነውና፡፡ በመሆኑም ለአገር የሚጠቅሙ ጥናቶች የአቧራ መጫወቻ አይሁኑ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...

እጥረትና ውጥረት!

ጉዞ ከስድስት ኪሎ ወደ ቃሊቲ፡፡ ‹‹ይገርማል ቀኑ እንዴት ይሄዳል?››...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለፋይዳ ቢስ ጉዳዮች የሚባክነው ጊዜና ሀብት ያሳስባል!

ኢትዮጵያ በወጣት የሰው ኃይል፣ ዕውቀትና ልምድ ባካበቱ አንጋፋዎች፣ በሰፊ ለም መሬት፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ በሌለው የውኃ ሀብት፣ በበርካታ የማዕድናት ዓይነቶች፣ ብዛት ባላቸው የቱሪዝም መስህቦችና የአየር...

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...