Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየ‹‹ተፈሪ መኰንን›› ትምህርት ቤት 92ኛ ዓመት

የ‹‹ተፈሪ መኰንን›› ትምህርት ቤት 92ኛ ዓመት

ቀን:

‹‹ይህ ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት በሐኪም ወርቅነህ ዋና ሹምነት፣ ሙሴ ጆን ጉዮ በተባለ ፈረንሣይ ዳይሬክተርነትና አስተማሪነት፣ ለትምህርት ቤቱ በሰጠነው በውስጥ ደንብ እየተመራ ሥራውን ጀመረ፡፡ በውስጣቸውም የፈረንሣዊና የእንግሊዝ ቋንቋ መምህራኖች፣ የውጭም፣ የኢትዮጵያም የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ተማሪዎች የአውሮፓን ትምህርት ቤቶች ፈተና እዚሁ እንደሆኑ እንዲቀበሉ ሲደረግ ፈተናውን ለማለፍና የመጀመሪያውን ደረጃ የምስክር ወረቀት ለመቀበል የቻሉ ብዙ ተገኙ፡፡ በዚያም ጊዜ የኢትዮጵያ ልጆች ብልህነት የመምህራኖች ትጋት እጅግ ደስ እንዳሰኘን ድካማችንም እጥፍ እንዲሆን የሚያበረታታን ሆነ፡፡ ትምህርት ቤቱን ለመጎብኘት በመጣን ቁጥር የሚያደርጉን ትጋት ራሳችን እንመለከትና የትጋታቸውንም ፍሬ በተማሪዎቹ መቅደም ይታይ ስለነበር በዚያም ጊዜ ተማሪዎች በትምህርታቸውና በትጋታቸው ብቻ የተገቡ ሆነው የተገኙት የተመረጡ ወደ ውጭ አገር ሄደው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አደረግን፡፡ ከዚህም መካከል ኢጣልያን አገራችን ውስጥ ባደረገችው የወጣት እልቂት ይህ ትምህርት ቤት በትምህርት የፈጠራቸው የወጣት አበቦች የሚበዙት ሲጠፉ በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ አንዳንዶቹ የተረፉት አሁንም አገራቸውን ያገለግላሉ፤››

የቀድሞው ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923 – 1967) የቀድሞው ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት የአሁኑ እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኮሌጅ የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት አስመልክተው ካደረጉት ንግግር የተቀነጨበ ሲሆን፣ ንግግሩን ካደረጉ ከ67 ዓመታት በኋላ በ1917 ዓ.ም. የተመሠረተው ኮሌጁ 92ኛ ዓመቱን ሚያዝያ 19 ቀን 2009 ዓ.ም. ያከብራል፡፡

ንጉሡ በንግግራቸው፣ ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በኢትዮጵያ ትምህርትን ለማስፋፋት የተጫወተውን ሚና አውስተው፣ በወራሪ ጠላት በግፍ የተገደሉ ተማሪዎች በርካታ ቢሆኑም ትምህርት ቤቱ ከጉዞው እንዳልተገታም ተናግረው ነበር፡፡ ትምህርት ቤቱ ዛሬ ከሚገኝበት ደረጃ የደረሰው በብዙ ውጣ ውረድ ሲሆን፣  በተለያዩ ሙያዎች ለአገሪቱ ያበረከታቸው ምሁራን በርካቶች ናቸው፡፡ ተማሪዎችን ውጪ እየላኩ ከማሠልጠን ባለፈ ንጉሡ በትምህርት ቤቱ እየተገኙ የተማሪዎችን ሥራ የተመለከቱባቸው ጊዜያትም ነበሩ፡፡ ትምህርት ቤት በኢጣልያን ወረራ ወቅት ቪክተር ኢማኑኤል ተብሎ የኢጣልያን ባለሥልጣኖች ልጆች መማሪያ ሆኖም ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ነፃነት በኋላ ወደ አገሪቱ ንብረትነት ተመልሶ ተማሪዎች ማፍራቱን ቀጥሏል፡፡

ኮሌጁ ዘንድሮ 92ኛ ዓመቱን የሚያከብረው፣ ትምህርት ቤቱ ያፈራቸውን አንጋፎች በሚያስታውስ መርሐ ግብር እንደሆነ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ገልጸውልን ወደ ኮሌጁ ጋበዙን፡፡ ተማሪዎች ከኮሌጁ 11 የትምህርት ክፍሎች በአንዱ ማለትም የኤስተቲክስ ትምህርት ክፍል (ሥነ ውበት) የቴአትር፣ የሥነ ጥበብና ሙዚቃ የዘንድሮ ተመራቂዎች ሲሆኑ፣ በየሙያቸው ለበዓሉ እየተሰናዱ ነው፡፡

ዘንድሮ ከቴአትርና ፊልም ትምህርት ክፍል የሚመረቀው እዝራ ሙላቱ እንደሚናገረው፣ እሱና ሌሎችም ተመራቂ ተማሪዎች በዓሉን በማስታከክ ቀደምት የትምህርት ቤቱ ምሁራን ሥራዎችን በማሰባሰብ በኮሌጁ የመረጃ ማዕከል የማስቀመጥ ሥራ ጀምረዋል፡፡ የኪነ ጥበቡ ባለሙያዎች ያበረከቷቸውን ጥበባዊ ሥራዎች እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ያሉ ምሁራንም የሠሯቸው ጥናቶች ተሰንደው ቢቀመጡ፣ ለትምህርት ቤቱ ታሪክ ማሳያነትና ለማስተማሪያነትም እንደሚያገለግሉም ይገልጻል፡፡

እዝራ ተመራቂዎቹ ትምህርት ቤቱን ከመልቀቃቸው በፊት በጽሑፍና በቪዲዮ ያሉ ሰነዶችን በማሰባሰብ ለኮሌጁ የመረጃ ማዕከል የማበርከት ተነሳሽነታቸውን የኮሌጁ አመራር እንዲደግፍ ጠይቀው ቀና ምላሽ ማግኘታችን ያስረዳል፡፡ ኮሌጁን በጎበኘንበት ወቅት በመረጃ ማዕከሉ ስለ ተቋሙ ታሪክ የሚያወሱ ጥናቶች፣ ያለፉት ዓመታት ዋና ዋና ክንውኖችንና ቀደምት መምህራንና ተማሪዎችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ተመልክተናል፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹ ፎቶግራፎች የመስታወት ሽፋን ሳይደረግላቸው በመቀመጣቸው ለአቧራና ለንክኪ ተጋልጠዋል፡፡ የነዚህና ወደ ማዕከሉ የሚገቡ አዳዲስ ሰነዶችም አያያዝ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ መረጃዎችን አሰባስቦ ከማከማቸት ጎን ለጎን አያያዛቸውም ቦታ ሊሰጠው የግድ ይላልና፡፡

ትምህርት ቤቱ ያፈራቸው ባለሙያዎችን ሥራዎች ከማሰባሰብ ሥራ ጋር በተያያዘ ከባለሙያዎቹ መካከል ወደ 40 የሚሆኑት ምስለ አካል (ፖርትሬት) በአንድ ሸራ የመሣል ዕቅድ እንዳለም የሥነ ጥበብ ተመራቂው ቃለአብ ምሕረቱ ይናገራል፡፡ የጀግናው አርበኛ ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎን ሐውልት በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ለማቆምም አቅደዋል፡፡ አያይዞም በሙዚቃ ትምህርት ክፍል ለበዓሉ የሚሆኑ ሙዚቃዎች እየተዘጋጁ መሆናቸውን ይናገራል፡፡ የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎችን ውጤታማነት በማሳየት አሁን ያሉትና ለወደፊት ወደ ኮሌጁ የሚገቡትንም ማነሳሳት እንደሚቻል ያምናል፡፡ ተመራቂ ተማሪዎች እንደመሆናቸው በየሙያቸው ለኮሌጁ የሚጠቅም ነገር የማድረግ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት መንገድ እንደሆነም ይገልጻል፡፡

ተማሪዎቹ ትምህርት ቤቱ ያፈራቸውን ጀግና አርበኛ ሐውልት ለማቆም ማቀዳቸው ተመራቂዎቹ አሁን በግቢው ያለውን ሌላ ሐውልትም ያስታውሳል፡፡  ለከፍተኛ ትምህርት ውጭ አገር ከተላኩ የትምህርት ቤቱ የመጀመርያ ዙር ተማሪዎች መካከል የእንስሳት ሐኪም ዶ/ር እንግዳ ዮሐንስ የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በኮሌጁ መታሰቢያ ሐውልት ቆሞላቸዋል፡፡ ቃለአብ እንደሚለው፣ ሌሎችንም አንጋፋ ባለሙያዎችን በተለያየ መንገድ መዘከር ተገቢ ነው፡፡ በትምህርት ቤቱ ታሪክ ከሚጠቀሱ አንጋፎች መካከል ቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ፣ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ፣ ተስፋዬ ገሠሠ፣ ሃይማኖት ዓለሙ፣ ሰለሞን ደሬሳ፣ ገነት ዘውዴ፣ ተስፋዬ ካሳና አለባቸው ተካን መጥቀስ ይቻላል፡፡

በኪነ ጥበብ አንቱ ከተባሉ ባለሙያዎች መካከል ተስፋዬና ሃይማኖት በትምህርት ቤቱ በሚገኘውና ቸርች በመባል በሚታወቀው አዳራሽ ቴአትር ካሳዩት ውስጥ ይገኙበታል፡፡ ንጉሡ ትምህርት ቤቱን በሚጎበኙበት ወቅት ቴአትር የሚመለከቱትም በአዳራሹ ውስጥ ነበር፡፡ ሲሲ ቲቪ ‹‹ፌስስ ኦፍ አፍሪካ›› በተሰኘው መርሐ ግብር ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የዘመናዊነት መስፋፋት ባቀረበው ዘጋቢ ፊልም ለተስፋዬና ሃይማኖት ቃለ መጠይቅ ተደርጎ ነበር፡፡ ባለሙያዎቹ በፊልሙ በቸርች አዳራሽ ንጉሡ በተገኙበት መተወን ይሰጣቸው የነበረውን ስሜትም ገልጸዋል፡፡ ለዓመታት በርካታ ታሪክ ያስተናገደውን አዳራሽ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በቅርስነት መዝግቦታል፡፡ አዳራሹ እንደ ቅርስነቱ ተጠብቆ ጥቅም ላይ መዋል ካለበትም በቴአትር  ትምህርት ክፍል ስር መተዳደር ቢገባውም፣ በአሁን ወቅት እየተገለገለበት ያለው ሌላ የኮሌጁ የሥራ ክፍል ነው፡፡ ይህንን እንደ መነሻ በመውሰድ ኤስተቲክስ ትምህርት ክፍል ማለትም የሙዚቃ፣ የሥነ ጥበብና የቴአትር ክፍሎች የሚገኙበትን ሁኔታ ቃኝተናል፡፡

የቴአትር ትምህርት ክፍል ለዓመታት አልባሳትና ሌሎችም ቁሳቁሶች የሚቀመጡበት ክምችት ክፍል አልነበረውም፡፡ ይህንን ክፍተት ያስተዋለው ተመራቂ ተማሪ ዳንኤል ተሰማ አምና የቴአትር ግብዓቶች ክምችት ክፍል አቋቁሟል፡፡ ክፍሉን ያቋቋመው ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ከቤቱና ከኮሌጁ ግቢም በማሰባሰብ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ተማሪዎች ቴአትር ሲሠሩ ለሚጫወቱት ገፀ ባህሪ የሚሆን ልብስና ዕቃ ከቤታቸው እያመጡ ወይም ከሌላ ትምህርት ክፍል እየተዋሱ ከሚሆን፣ እስከዘለቄታው የሚጠቀሙባቸው ቁሳቁሶች በክምችት ክፍሉ መሟላት እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡

 በራሱ ተነሳሽነት ባቋቋመው ክፍል አልባሳት፣ ሲነሪዎችና የሥነ ጽሑፍ መጻሕፍትን አሰባስቧል፡፡ ኮሌጁ ያላሟላቸውን ነገሮች ከመጠየቅ በፊት ተማሪዎች በአቅማቸው መሥራት እንደሚችሉ የሚገልጸው ዳንኤል፣ እሱ ተመርቆ ከወጣ በኋላ ክምችት ክፍሉን ተረክቦ የሚያስተዳድረው አካል መኖር እንዳለበትም ያስረግጣል፡፡

ተመሳሳይ አስተያየት የሰጠን የቴአትር መምህሩ ባረከ ታደሰ፣ ተማሪዎቹ በራሳቸው ጥረት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በኮሌጁ መደገፍ አለበት ይላል፡፡ የክምችት ክፍልን ከማዋቀር በተጨማሪ፣ ቸርች አዳራሽን በቴአትር ትምህርት ክፍል ይዞታ ማድረግና የተቋሙን እንዲሁም የዕውቅ ተማሪዎችን ታሪክ የመሰነድ ነገር ሊታሰብበት እንደሚገባ ይገልጻል፡፡ የኮሌጁን 92ኛ ዓመት በተመለከተ የተመራቂ ተማሪዎች እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን የሚገልጸው መምህሩ፣ በዓሉ በየዓመቱ በድምቀት መከበር እንዳለበትም ያምናል፡፡ በዓሉ ሲከበር የቀድሞ ተማሪዎች ስለሚገኙ በተያያዥ ችግሮች የሚፈቱበት መድረክ እንደሚፈጠርም ተስፋ ያደርጋል፡፡

በሙዚቃና ሥነ ጥበብ ትምህርት ክፍሎች ከግብዓትና የትምህርት መስጫ ቦታ ጋር የተያያዙ ክፍተቶች ተመልክተናል፡፡ በእርግጥ የሥነ ጥበብ ትምህርት ክፍሉ ጥሩ ጋለሪ ያለው ሲሆን፣ የተለያየ ዓመት ተማሪዎች የሚማሩባቸውና የሚሠሩባቸውም ስቱዲዮዎችም አሉ፡፡ በጋለሪው ትምህርት ክፍሉ በተመሠረበት ወቅት የነበሩ ተማሪዎች ፎቶግራፎችና ያለፉት ዓመታት ተማሪዎች መመረቂያ ሥራዎች ይገኛሉ፡፡ በጋለሪው ውስጥና በአቅራቢያው ባለው ሜዳም በተመራቂዎች የተሠሩ ቅርጾችም አሉ፡፡

የትምህርት ክፍሉ ኃላፊና መምህር ተስፋ ሰለሞን እንደሚለው፣ በተለይም የቀለምና ወረቀት ግብዓቶች እጥረት ይገጥማቸዋል፡፡ ገበያ ላይ የሚፈልጉት ዓይነት ግብዓት ካለመገኘቱ በላይ ከግዥ ጋር የተያያዙ ችግሮች ቢኖሩም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ መታየቱ ተስፋ ይሰጣቸዋል፡፡ የሥነ ጥበብ መምህራን ለትምህርት ክፍሉ ግብዓት እንዲሟላና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ በቀጥታ በመሳተፍ ትልቁን ድርሻ መውሰድ እንዳለባቸው ያምናል፡፡

የኤስተቲክስ ትምህርት ክፍል አስተባባሪና የሙዚቃ መምህር ጥበቡ ወልደዮሐንስ እንደሚናገሩት፣ በትምህርት ክፍሉ ያሉት ተማሪዎችና የሙዚቃ መሣሪያዎች ቁጥር አይመጣጠንም፡፡ ከሙዚቃ መሣሪያዎች ግዥ ጋር በተያያዘ የአቅርቦት እጥረት እንዳለም ይናገራሉ፡፡ ትምህርት ክፍሉ የሚገኝበትን ሕንፃ ከስፖርትና የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍሎች ጋር እንደሚጋራም አስተውለናል፡፡ መምህሩ ኮሌጁ 92ኛውን ዓመት ሲያከብር የሚገኙ የቀድሞ ተማሪዎች ለለውጡ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ዕድል እንደሚፈጠር ከሌሎች መምህራን ጋር ይስማሙበታል፡፡

ሐሳቡን የሚጋሩት የኮሌጁ ዲን ወ/ሮ ሙሉ አጽብሓ እንደሚሉት፣ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንዲያገኙ ለትምህርት ሚኒስቴርና የተራድኦ ድርጅቶችም ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ የሥነ ጥበብ ትምህርት ክፍል በቂ ወርክሾፖች ቢኖሩትም በግብዓት ረገድ ክፍተቶች አሉ፡፡ እነዚህ ግብዓቶች በጨረታ ወጥተው ስለማይመጡላቸው በቀጥታ ከሻጮች ለመግዛት ይገደዳሉ፡፡ ግዥው መንግሥት ለቀጥታ ግዥ በዓመት ከመደበው 60,000 ብር የሚበልጥበት ጊዜ ቢኖርም ኮሌጁ ባለው አቅም ግብዓቶችን ከማሟላት ወደ ኋላ አይልም ይላሉ፡፡

በሌላ በኩል በኮሌጁ ቅጥር ግቢ የሚገኘው ቸርች አዳራሽ ለቴአትር ትምህርት ክፍል ዓላማ እየዋለ ሙዝየም የማድረግ ሐሳብ እንዳለ ይናገራሉ፡፡ የቴአትር ትምህርት ክፍሉ የተደራጀ ባለመሆኑና ለትምህርቱ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ውድ በመሆናቸውም እጥረት መኖሩን ያምናሉ፡፡ እንደ መፍትሔ ያስቀመጡት ቴአትር ቤቶች የተገለገሉባቸውን ዕቃዎች (ለምሳሌ የመድረክ መብራት) እንዲሰጧቸው መጠየቅን ነው፡፡  የኤስተቲክስ ትምህርት ክፍሎች ራሳቸውን ችለው የቆሙና የተደራጁ እንዲሆኑ በቂ ቦታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ለዚህም በኮሌጁ እየተገነቡ ያሉ ሕንፃዎች መልስ እንደሚሆኑ ዲኗ ይገልጻሉ፡፡ እያንዳንዱ ትምህርት ክፍል ራሱን የቻለ ማሠልጠኛ ክፍሎች እንዲኖሩት  እንደሚደረግም ያክላሉ፡፡

መነሻችን ያደረግነው የኮሌጁን 92ኛ ዓመት አከባበር በተመለከተ፣ ተመራቂ ተማሪዎች ያቀረቧቸውን ሐሳቦች እንደሚደግፉ ወ/ሮ ሙሉ ይናገራሉ፡፡ ተማሪዎቹ በቅርቡ ለዓድዋ በዓል አዘጋጅተው የነበረው መርሐ ግብር ለትምህርት ቤቱ ማበርከት የሚችሉትን አስተዋጽኦ እንዳሳያቸው ገልጸው፣ ከቀናት በኋላ የሚከበረውን 92ኛ ዓመት ለማሳካት በገንዘብና ለተጨማሪ ወጪ ስፖንሰር በማፈላለግ እየሠሩ እንደሚገኙ አክለዋል፡፡ በትምህርት ክፍሉ የሚሰጠውን ትምህርት ወደ ዲግሪ የማሳደግ እንቅስቃሴ እንዳለም የገለጹት ዲኗ፣ ይህ ኮሌጁን በመለወጥ ረገድ ከተያዙ ዕቅዶች አንዱ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...