Sunday, February 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊእንደሰማይ የራቁ መድኃኒቶች

እንደሰማይ የራቁ መድኃኒቶች

ቀን:

ከሦስት ዓመት በፊት ከማሕፀን ካንሰር ነፃ መሆኗ ለዓለም በላቸው በተነገራት ወቅት የቤተሰቡ ፈንጠዝያና ደስታ መግለጽ ከሚቻለው በላይ ነበር፡፡ ዜናው በመዳን ትግል ውስጥ የነበረውን የኬሞቴራፒ ሕክምና ስቃይ ማብቂያን ያበሰረ ነበር፡፡ ለመኖር ግብግብ የነበረውን ጉዞዋን የሚያስታውሰው ወንድሟ ክፍሎም ኬሞቴራፒ ‹‹እያንዳንዱ ሕዋሷ እየሞተ ይመስል ነበር፤›› በማለት ይገልጸዋል፡፡

ለዓለም ብቻ ሳትሆን ከካንሰር ለመዳን የሚደረግ ትንቅንቅ ለብዙ በሽተኞች መስዋዕትነት የሚከፍሉበት ጉዞ ነው፡፡ የለዓለም ቤተሰቦችም የማያቋርጥ ሕመሟን፣ ማቅለሽለሹን፣ በየጊዜው የአፏ ላይ መቁሰልን እንዲሁም በድንገት ሆስፒታል መሄድን ተካፋይ ሆነዋል፡፡ ይኼንን ሁሉ ስቃይ አሸንፋ ከካንሰር መዷናን የታዋቂዋ አፍሪካ አሜሪካዊት ጸሐፊ ኦክቴቪያ በትለር ‹‹ከራሷ አመድ ለመነሳት (ለማንሰራራት) ፊኒክስ መጀመሪያ መቃጠል ነበረባት›› የሚለውን አባባል ያስታውሳል፡፡ ይኼ የካንሰር ትግል ግን በዚሁ አላቆመም ለዓለምም ሆነ ቤተሰቦቿ ያስጨነቃቸው ጉዳይ የበሽታው ተመልሶ መምጣት (ሪሚሽን) ነበር፡፡ ይኼ ሁኔታ በብዙ የካንሰር በሽተኞች የሚከሰት ሲሆን፣ ከዳኑም በኋላ ተመልሰው ሊታመሙ ይችላሉ፡፡ ከበሽታው መመለስ በተጨማሪ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ በኬሞቴራፒው ወቅት የሚጠቀሙት መድኃኒት ዝቃጩ ሰውነት ላይ የሚቆይና ይኼም የጤና እንከንን ሊያስከትል እንደሚችል መረዳታቸው አስጨናቂ ሁኔታ ፈጠረባቸው፡፡ ክፍሎም ይህ ይመጣል ብሎ አላሰበም ነበር፡፡ ለዓለም በጠና ታማ ቤተ ዛታ ሆስፒታል ገባች፡፡ የቤተሰቦቿ ደስታ ወደ ሐዘን ተቀየረ፡፡ በፍጥነት የጤናዋ ሁኔታ መቀየር ጀመረ፡፡ ኩላሊቷ ከጥቅም ውጭ እንደሆነ ተነገራት የሌሎቹም የሰውነቷ ክፍሎች መድከም ጀመሩ፡፡ ምግብ መብላት አቆመች በአማራጩም ግሉኮስ ብቻ እንድትወስድ ተነገራት፡፡ ሰውነቷ እንዲጠነክርና በሽታውን የመቋቋም አቅሟ እንዲጨምርም ፖይንት ፋይቭ የተባለ ግሉኮስ ታዘዘላት፡፡ በወቅቱ አጠገቧ የነበረው ክፍሎም በሆስፒታሉ ውስጥ የተባለው ግሉኮስ አለመኖሩን ሲረዳ ቢደነግጥም በሌሎች የጤና ማዕከላት ይኖራል የሚል ተስፋ ነበረው፡፡ ነገር ግን ተስፋ አስቆራጭ በሆነ ሁኔታ የአዲስ አበባን የጤና ማዕከላትን ቢያስስም፤ ሊያውቁ ይችላሉ የሚላቸውን የጤና ባለሙያዎች ቢያማክርም የተባለው ግሉኮስ ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡ በመጀመሪያው ቀን ትንሽ ግሉኮስ ስለነበራት ሁኔታው አሳሳቢ አልነበረም በሁለተኛው ቀን ምንም ዓይነት ግሉኮስ ስላልነበር ምንም ዓይነት ምግብ በሌለበት ሰውነቷ መድከም ጀመረ፡፡ ‹‹ምንም ማድረግ አለመቻላችንን መረዳታችን በጣም የሚያሳዝን ነበር፡፡›› በማለት ሁኔታውን ያስታውሰዋል፡፡

በሦስተኛው ቀን ተዓምራዊ በሚመስል ሁኔታ ግሉኮሱ ቢገኝም የለዓለምም ሕይወት አለፈ፡፡ የሕይወቷ በእንደዚህ ሁኔታ ማለፍ ቤተሰቡ በጤና አገልግሎት ሥርዓቱ ላይ እንዲበሳጭና እንዲያዝን አድርጓል፡፡ ይህ ስሜት ሌሎች መድኃኒት ማግኘት ያልቻሉ ሕመምተኞችና ቤተሰቦችም የሚጋሩት ነው፡፡ በተለይም በሕይወትና በሞት መካከል ሆነው ለሚያጣጥሩ የመድኃኒት መታጣት ሊፈጥርባቸው የሚችለውን ስሜት መገመትም ይከብዳል፡፡ በውጣ ውረድ የሕክምና ማዕከላት ሄደው ለሚታከሙ ሰዎችም መድኃኒት አለማግኘት መታከማቸውን ትርጉም አልባ ያደርገዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የችግሩን ወሰነ ሰፊነት ለመረዳት ሪፖርተር ያነጋገራቸው እንደገለጹት የመድኃኒት ከፍተኛ እጥረት፣ የአቅርቦት መቆራረጥ እንዲሁም ጥራታቸውና ጤንነታቸውን ያልጠበቁ፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች እንዳጋጠማቸው ነው፡፡ መቆራረጥና ዕጥረት የሚያጋጥማቸው መድኃኒቶች በዓይነትም በዋጋም የሚለያዩ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መድኃኒቶች አንዳንዶቹ ኦ.አር.ኤስ (ኦራል ራሀይድሬሽን ቴራፒ)፣ ኢንሱሊን፣ የአስም መድኃኒት ሴሬታይድ፣ ከዘጠኝ ወራት በፊት ለሚወለዱ ሕፃናት የሚሆነው ሠርፋክታንት እንዲሁም የፓርኪንሰንን አንዳንድ ሕመሞች ለመቀነስ የሚረዳው አርቴን ትራይሄክሲፈንዲል ይገኙበታል፡፡

ባለው የመድኃኒት ማጠርና የአቅርቦት መቆራረጥ ምክንያት በመሠላቸት አቋራጭ የሆነ የመድኃኒት ማግኛ ዘዴንም የሚጠቀሙ ጥቂት አይደሉም፡፡ ብዙዎች ውጭ አገር የሚኖሩ ዘመዶቻቸውን፣ የአየር መንገድ አስተናጋጆችን መድኃኒት አምጡልኝ ማለት የተለመደ ሆኗል፡፡ ለአንዳንዶች መድኃኒት ማግኘት ማለት ከባድና ፈታኝ ሆኖም አግኝተውታል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዷ ዮዲት አስመላሽ ናት፡፡ በብዙዎች ለደም ዓይነት ዘንድ ነጌቲቭ የሚለውን የደም ዓይነት ቅጥያ መስማት አስደንጋጭ ነው፡፡ በወቅቱም ዮዲት የደም ዓይነቷ ኦ ነጌቲቭ መሆኑን አንዳንድ ጓደኞቿ ሰምተው ልጅ መውለድ አትችልም በሚል የሐዘኔታ ዓይን ተመልክተዋታል፡፡

በ28ተኛ ሳምንት እርግዝና ወቅት ያለችው ዮዲት ነጌቲቭ የሚለው የደም ዓይነት  ምን እንደሚያመላክት በጥልቅ ተረድታለች፡፡ በተለምዶ ሾተላይ ተብሎ የሚታወቀው ነጌቲቭ የደም ዓይነት ሳይንሳዊ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቀይ የደም ህዋስ ውስጥ ሪሄሰስ ፋክተር የሚባል የፕሮቲን ዓይነት አለመኖር ነው፡፡ ይኼ ሁኔታ የጤና መወሳሰብ ሊያጋጥም የሚችለው አርኤች ነጌቲቭ ደም ያላት እርጉዝ ሴት በእርግዝና ወቅት ልጁ አር ኤች ፖዘቲቭ የሚሆንና የደም ንክኪ የሚፈጠር ከሆነ ነው፡፡ ፅንሱን እንደ ልውጥ አካል በመቁጠር እናቲቱ አንቲ ቦዲ ታመርታለች፡፡ ይህ ሁኔታ አር ኤች ሴንሲታይዜሽን ይባላል፡፡ ይኼም ሁኔታ የፅንሱን የቀይ ደም ሴል ጉዳት ላይ ይጥለዋል፡፡ ሕፃኑ በሕይወት ድንገት ሊወለድ ከቻለም የአዕምሮ ጉዳት፣ የሰውነት ማበጥ፣ የመስማትና የመናገር ችግር፣ የደም ማነስ፣ ማንቀጥቀጥና የመሳሰሉ ችግሮች ሊገጥመው እንደሚችሉ በጉዳዩ ላይ የተሠሩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያም ይሁን በአፍሪካ የአር ኤች ነጌቲቭ የደም ዓይነት ያላቸው ሰዎች ቁጥር አነስተኛ ቢሆንም ከሰሀራ በታች ባሉ አገሮች ለፅንስ ሞት አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንዳንድ ባህሎች ከእርግማንና ከሰይጣን መንፈስ ጋር የሚገናኘው ይህ ነገር ብዙ እናቶችን በእርግዝና ወቅት ብዙ ልጆች በሚሞቱባቸው ወቅት ‹‹ልጆቻቸውን የበሉ›› የሚል መጥፎ ስምም አሰጥቷቸዋል፡፡ ለሳይንሳዊ ምርምሮችና መድኃኒቶች ምሥጋና ይግባቸውና ነጌቲቭ ደም ያላቸው እናቶች ጤነኛ ልጆች እንዲወልዱ አስችሏል፡፡ ዮዲትም ለኔጌቲቭ ደም የሚሆነውን መድኃኒት አንታይ ዲ ኢሚውኖግሎቢን በስፋት ይገኛል በሚል እሳቤ ብዙም አላስጨነቃትም፡፡

መድኃኒቱን ለማግኘት ያደረገችው ውጣ ውረድ ግን እውነታው ምን ያህል ተቃራኒ እንደሆነ አሳይቷታል፡፡ ምንም እንኳን ምርመራ ባደረገችበት የሆስፒታል ውጤቷ የሚያሳየው ሰውነቷ ምንም ዓይነት አንታይ ቦዲ እንዳላመረተ ቢሆንም የልጁን ደኅንነት ለመጨመርና እርግጠኛ ለመሆን አንታይ ዲ ኢሙውኖግሎቢሊን መውሰድን መረጠች፡፡ ፍለጋዋን ከተመረመረችበት ሆስፒታል በመጀመር መድኃኒቱ ይገኝባቸዋል ብላ ወደምታስባቸውና ይገኛል ወደተባለችበት መድኃኒት ቤቶች አቀናች፡፡ ራስ ደስታ ሆስፒታል፣ ዘመነ ዮሐንስ፣ ዓለም ጤና፣ ከነማ፣ ግሸን ፋርማሲዎች የመሳሰሉት ከሃያ በላይ ፋርማሲዎች ብትሄድም መድኃኒቱ ሊገኝ አልቻለም፡፡ ተስፋ ባለመቁረጥም መድኃኒቱ ሊኖርበት የሚችልበትን ሁኔታ ያውቃሉ ብላ የምታስባቸውን ሰዎች ብታጠያይቅም ፍለጋው ተስፋ አስቆራጭ እየሆነ መጣ፡፡ በሁለት ቀን ፍለጋም ግንፍሌ አካባቢ በሚገኝ ፋርማሲ በእጥፍ ዋጋ 2,800 ብር የሚሸጥ አገኘች፡፡ ዮዲት በፍለጋዋ ወቅት በሙያው ላይ አሉ የሚባሉ የማሕፀን ስፔሻሊስቶችና የጤና ባለሙያዎች መድኃኒቱ ይገኝበታል ወደሚባለው ወደተለያዩ አቅጣጫዎች መርተዋት መድኃኒቱን በአንደኛው የመንግሥት ሆስፒታል በነፃ ለማግኘት ችላለች፡፡ ብዙ ሴቶች ግን የእሷን ያህል ከጤና ባለሙያዎች ጋር ግንኙነት የላቸውም፡፡ ተስፋ ቆርጠው የሚተውትም ብዙ ናቸው፡፡

ከመድኃኒት አቅርቦት መቆራረጥና ማጠር ጋር ተያይዘው የሚመጡ ማማረሮች ብዙ ከመሆናቸው አንፃር ችግሩ የት ጋ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ መድኃኒቶች ለሕዝብ የሚሠራጩበት መንገድንም በጥልቀት ማየት እንደሚገባም ያሳያል፡፡ በተለይም ከእጥረትና ከመቆራረጥ በተጨማሪ በመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖች ውስጥ ተቀላቅለው የተገኙ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች በገፍ መኖርም አስደንጋጭ ዜና ነው፡፡

በባለፈው ዓመት የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ መድኃኒት ግዥና ሥርጭትን በተመለከተ አስደንጋጭ ሪፖርት ለፓርላማ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ ሪፖርት እንደሚያሳየው ሕግና ሥርዓትን ያልተከተለ ጨረታ፣ ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች ጥርቅምና የሕክምና መሣሪያዎች ጊዜያቸው ካላለፈባቸው ጋር እንዲበሰብሱ በመተው የሚሉ ናቸው፡፡ በዚህም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ እንዲባክን ሆኗል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አዲስ አበባ በሚገኙ የተለያዩ የኤጀንሲው መጋዘኖች በ28/09/20066 ከማኔጅመንት አስወጋጅ ኮሚቴ በቀረበ ሪፖርት ለማንና መቼ እንደተገዙ መረጃዎች ያልቀረበ ሁለት መቶ ሐምሳ ስድስት ሚሊዮን ሰባት መቶ አንድ ሺሕ አርባ ስድስት ብር የሚያወጣ መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች እንዲሁም ከአዳማ ቅርንጫፍ በ26/05/07  ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ እንደተገለጸው የጥራት ችግር አለባቸው የተባሉ ሰላሳ አራት ሚሊዮን ስምንት መቶ ስልሳ ሦስት ሺሕ ስምንት መቶ አርባ ስምንት ብር የሚያወጡ የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ተገኝተዋል፡፡ በአጠቃላይም በድምሩ አምስት መቶ ስልሳ ዘጠኝ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሰላሳ ሦስት ሺሕ ዘጠኝ መቶ አሥራ ዘጠኝ ብር የሚያወጡ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችና የሕክምና መገልገያ መሣሪያ መኖሩ ኦዲተሩ በሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

የኦዲተሩ ሪፖርት ከ2005 እስከ 2007 ያሉትን ሦስት ዓመታትና እንዲሁም የ2008ን የሩብ ዓመት ላይ ጥናት ያካሄደ ሲሆን በዚህም ጥናት የተለያዩ ጤና ማዕከላት ከፍተኛ የሥራ አመራር አባላት ቃለ መጠይቆች እንዲሁም የኤጀንሲውን የተለያዩ መጋዘኖች በማየትና በመመርመር የተጠናቀረ ሪፖርት ነው፡፡ በተለያዩ ከተሞችም ጊዜያቸው ያለፉባቸውና ያልተወገዱ መድኃኒቶች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ በ2005 እስከ 2007 ዓ.ም. ከቅርንጫፎች በቀረበ የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሠረት በባህር ዳር 71,372,697 ብር፣ ድሬዳዋ 17,387,474.24 ብር፣ ጂማ 38,528,315.04 ብር፣ መቐለ 13,979,155.44 ብር፣ ነቀምት 11,280,979.12 ብር ሐዋሳ 26,576,756.01 ብር፣ ጎንደር 7,988,702.96 ብር፣ ነገሌ ቦረና 4,318,389.17 ብር፣ አዳማ 50,752,837.67 ብር፣ ደሴ 20,021,973.13 ብር እንዲሁም አዲስ አበባ ቅርንጫፍ 16,091,745.39 ብር የሚያወጡ አገልግሎታቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶች ተገኝተዋል፡፡

መድኃኒቶቹና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎቹ በመጀመሪያ ለማንና ለምን እንደተገዙ፣ እንዲሁም በወቅቱ ለተጠቃሚዎቹ ያልተሰራጩበትን ምክንያት በተመለከተ ተጠይቀው ለግዥ ሲቀርብ ታሳቢ የተደረጉት ሁኔታዎች በመድኃኒቱ አጠቃቀም ትግበራ ወቅት መለያየት፣ መድኃኒቶቹ ተገዝተው በመሠራጨት ላይ እያሉ በዓለም ጤና ድርጅት ለሕክምና እንዳይውሉ በመደረጉና በሌላ መድኃኒት በመተካታቸው የሚሉ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጤና ተቋማት የሚገኘው የመድኃኒት ፍጆታ መረጃ የተሟላ አለመሆንና ለመደበኛ መድኃኒቶቹ ግዥ በጤና ተቋማት በቂ በጀት አለመያዝ በተላላፊ በሽታዎች ተኝተው ይታከማሉ ተብሎ የተገመተው ሕሙማን መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ የሚሉ ናቸው፡፡ ኤጀንሲው እነዚህ መድኃኒቶች በወቅቱ አልተወገዱም ለሚለው በቂ ምክንያት ካለመስጠታቸውም በላይ አንዳንድ መድኃኒቶች በዓለም ጤና ድርጅት ለሕክምና እንዳይውሉ መደረጋቸውን ለሚሉት ምክንያቶች ምንም ዓይነት መረጃ ማቅረብ አልቻሉም፡፡ ሪፖርቱ ጨምሮ እንደሚያስረዳውም ጥራታቸው ያልተጠበቁና የተበላሹ መድኃኒቶችም እንደተገኙ ነው ምንም እንኳን ኤጀንሲው የተበላሹት መድኃኒቶችን መመለስ ኃላፊነቱ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን (ኤፍኤም ሀካ) መሆኑን ቢገልጹም ባለሥልጣኑ ለኦዲተር ጄኔራሉ የጻፈው ደብዳቤ እንደሚያስረዳው ባለሥልጣኑ ትዕዛዝ መስጠት ብቻ ነው፡፡

መድኃኒቶቹን የመመለስ፣ በምትኩ ሌሎች መድኃኒቶችን መቀበል እንዲሁም ብሩ የሚመለስበትንና የማይመለስበትን መንገድ መከታተል የኤጀንሲው ኃላፊነት ነው፡፡ የኤፍምሀካ ደብዳቤ ጨምሮ እንደሚያስረዳው ኤጀንሲው በወቅቱ መረከብ ያልቻላቸው መድኃኒቶች ለሰባት ስድስት ቀናት በፀሐይና በዝናብ መፈራረቅ ምክንያት እንደተበላሹ ነው፡፡ አገሪቷ ውስጥ ካሉ መድኃኒት አምራቾችም ጋር በተደረገ ቃለ መጠይቅ ኤጀንሲው የገዛቸውን መድኃኒቶች በወቅቱ አለመውሰዱን ነው፡፡ ምንም እንኳን ኤጀንሲው በመጋዘኖች እጥረት ነው የሚል ምክንያት ቢያቀርብም ሪፖርቱ የአሠራር እንዝህላልነት እንዳለበትም አሳይቷል፡፡

የመድኃኒት ፈንድ የሕዝብ ግንኙነት ወ/ሮ አድና በሬ የኦዲተሩ ሪፖርት ላይ አስተያየት ባይሰጡም የመድኃኒት አቅርቦት መቆራረጥ እጥረት እንዲሁም ሕገወጥ አሠራርና ሽያጭ አዲስ እንዳልሆኑ ይናገራሉ፡፡ ፈንዱ በአዋጅ 553/1999 የተቋቋመ መሥሪያ ቤት ሲሆን፣ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍል የሚገኙ 17 ቅርንጫፎችም አሉት፡፡ ዋናው የተቋቋመበት ዓላማም በመድኃኒት ፈንድ በመጠቀም በአገሪቱ ዋና ዋና የጤና ችግሮች ላይ ያተኮሩ ጥራታቸው የተረጋገጠ መሠረታዊ መድኃኒቶችን በበቂ መጠን፣ በተመጣጣኝ ዋጋና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመንግሥታዊ የጤና አገልግሎት ተቋማት ማቅረብ የሚያስችል ቀልጣፋና ብቃት ያለው የግዥና የሥርጭት ሥርዓት ለመዘርጋት እንዲሁም ዘመናዊ የክምችትና አስተዳደር ለማስፈን የሚያስችል አሠራር በመዘርጋት ተመጣጣኝና ተገቢ የመድኃኒት ክምችና ያልተቋረጠ አቅርቦት እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ ምንም እንኳን መድኃኒት መቆራረጥና እጥረት እንዳለ ወ/ሮ አድና ቢቀበሉም ለዚህ ምክንያቶቹ ዘርፈ ብዙ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡ ፈንዱ በዋነኝነት ከተለያዩ መንግሥታዊ የጤና ማዕከላት ከሚመጡ ትዕዛዞች በተጨማሪ ኤችአይቪ፣ ወባ፣ እንዲሁም ለቤተሰብ ዕቅድ የሚውሉ የፕሮግራም መድኃኒቶችን በጀት በመያዝ ይገዛል፡፡ ከእነኝህ ከሁለቱ በተጨማሪ በዕርዳታ የሚመጡ መድኃኒቶችን በየዓይነቱ ያከፋፍላል፡፡ ምንም እንኳን ወ/ሮ አድና የፕሮግራም መድኃኒቶች በዕቅድ መሠረት ስለሚገዙ እጥረት የለም ቢሉም የኦዲተሩ ሪፖርት እንደሚያሳየው ከፕሮግራም መድኃኒቶች ግዢ ጋር በተገናኘ የአሠራር ግድፈቶች ታይቶባቸዋል ይላል፡፡

የተለያዩ ቴክኒካል ኮሚቴዎችን ማዋቀርና የሦስት ዓመት ዕቅድ ማቀድ ቢያስፈልግም ከኤችአይቪና ከወባ በስተቀር ሌሎቹ በዘፈቀደ እንደሚሠሩ ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡ ይህ የአሠራር ክፍተት በፕሮግራም መድኃኒቶች ብቻ ሳይሆን አስቸኳይ የመድኃኒት ግዥንም ይመለከታል፡፡ ከዕቅድ ውጭ ለሚገዙ አስቸኳይ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ግዢዎች የሚፈፀሙበት መስፈርትን ተግባራዊ ሊያደርጉ ቢገባም መስፈርት ሳይኖር አሥራ ስድስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ስልሳ ሦስት ሺሕ ሦስት መቶ ሰላሳ ሦስት ብር የሚያወጡ የአስቸኳይ መድኃኒቶች የሕክምና መገልገያ መሣሪያዎች ግዥ ተፈጽሞ ተገኝቷል፡፡

ሪፖርቱ ጨምሮ እንደሚያስረዳው ግዢዎቹ አስቸኳይ ስለመሆናቸው ከቀረቡት ማስረጃዎች ውስጥ የአስቸኳዩ አሳሳቢነት ተገልጾ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጠያቂነት የተከሰተውን ድርቅ ተከትሎ በውኃ እጥረት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች መከሰት የጀመረውን የአተት ወረርሽኝ ወደሌላ አካባቢ እንዳይዛመት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከተከናወነው ግዢ በስተቀር ሌሎቹ አስቸኳይ ግዢ መሆናቸውን ኤጀንሲው መረጃ ማቅረብም ሆነ ማረጋገጥ አልቻለም፡፡

የአንዳንዶቹ መድኃኒቶች ግዢ እንደሚያሳየው በተገዙ በሁለት ወር ልዩነት አስቸኳይ ግዢ ተብለው መቅረባቸው በመጀመሪያም በበቂ ሁኔታ አለመገዛታቸው አስቸኳይነታቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በብዙ መድኃኒቶች ግዢ ላይ ዝርዝር መረጃና በጀት በግልጽ አለመቀመጥ በአስቸኳይ መድኃኒት ግዢ ላይ የታዩ ክፍተቶች ናቸው፡፡

የተለያዩ መንግሥታዊ የጤና ማዕከላት በየዓመቱ የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒቶችና መሣሪያዎች ዝርዝር ለፈንዱ የሚሰጡ ሲሆን እነዚህም መድኃኒቶች ኤፍኤም ሀካ በሚገኘው የአገራዊ መድኃኒት ዝርዝር ውስጥ መገኘት መቻል አለባቸው፡፡ እነዚህ መድኃኒቶች በዚህ ዝርዝር ውስጥ ካልተገኙ ይህ የእጥረቱ መንስዔ ሊሆን እንደሚችል ወ/ሮ አድና ይናገራሉ፡፡ ኤፍኤምሀካ ከምዝገባ፣ ቁጥጥርና ፈዋሽነቱን ከማረጋገጥ በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ አስፈላጊ የሚባሉ መድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ መሠረት መድኃኒቶች መግባታቸውን ያረጋግጣል፡፡ ከሕመም ማስታገሻ ጀምሮ የተለያዩ በሺዎች የሚቆጠሩ የመድኃኒት ዓይነቶች በዝርዝሩ ውስጥ የተካተቱ ሲሆን የኤፍኤምሀካ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን አብርሃ የመድኃኒቶቹ ዝርዝር ትንሽ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ከተለያዩ የጤና ማዕከላትና አስመጪዎች ዝርዝሮቹን የመጨመር ጥያቄ እየመጣ ቢሆንም ሒደቱ አዝጋሚ እንደሆነ ጨምረው አቶ ሳምሶን ያስረዳሉ፡፡ አሁን ያለው የመድኃኒት ዝርዝር ለመድኃኒት እጥረት አንዱ መንስኤ ሊሆን እንደሚችል የሚያስረዱት አቶ ሳምሶን ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች 1,500 የሚሆኑ የተለያዩ ዓይነት መድኃኒቶችን ለመጨመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከተለያዩ ወረርሽኝና ድንገተኛ መድኃኒቶች በስተቀር በዝርዝሩ ካሉት መድኃኒቶች ውጪ መግዛት አንችልም፡፡ ይህ ማለት ዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተቱ መድኃኒቶች እጥረት ያጋጥማል ይላሉ፤›› አቶ ሳምሶን፡፡

ኤጀንሲው ከዝርዝሩ በተጨማሪ በሕጉ መሠረት ጄኔሪክ የሚባሉ መድኃኒቶች ይገዛሉ፡፡ ጄኔሪክ መድሃኒት የሚባሉት ብራንድ ከሚባሉት መድኃኒቶች በፈዋሽነታቸውም በደኅንነታቸው፣ በንጥረ ነገር ይዘታቸውም አንድ ዓይነት ሲሆኑ ብራንድ መድኃኒቶች ከወጡ ከዓመታት በኋላ እነሱን በማመሳሰል የሚወጡ የመድኃኒት ዓይነቶች ናቸው፡፡

ወ/ሮ አድና እንደሚሉት አንዳንድ ጊዜ ዶክተሮች የአገሪቷ የመድኃኒት ዝርዝር ውስጥ ያልተካተቱ መድኃኒቶችና ብራንድ መድኃኒቶች ሊታዘዙ የሚችሉበት አጋጣሚ በመኖሩ ይህ ሁኔት እጥረት ሊፈጥር ይችላል ይላሉ፡፡ አንዳንድ የመድኃኒት ገዥና ተጠቃሚዎች ልምድ የሚያሳየው ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው፡፡ ዮዲትንም የሚከታተሏት ዶክተር እንደነገሯት አንታይ ዲ ኢሙኖግሉቢን በአንድ ዓይነት የብራንድ ስም ስለማይገኝ በተለያየ የጄኔሪክ ስሙ እንድትፈልገው ነበር፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የተለያዩ የመድኃኒት ተጠቃሚዎች እንደገለጹት ፋርማሲዎች የተለያዩ የመድኃኒት አማራጮችን እንደሚያቀርቡላቸው ነው፡፡ ከዚህ በተለየ ወ/ሮ አድና እንደሚገልጹት የተለያዩ የጤና ማዕከላት ትክክል ያልሆነ ትንበያ፣ ከበጀት ማጠር ጋር ተያይዞ በአንዳንድ መድኃኒቶች ማጠር በአንዳንዶችም መብዛት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የኦዲተሩ ሪፖርት የሚያሳየው ከዚህ ተቃራኒው ነው፡፡ በኤጀንሲው መቋቋሚያ አዋጅ አንቀጽ 15/2 የመንግሥት ጤና ተቋማት በወቅቱና በጠየቁት መጠን መድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች እንዲደርሳቸው ባለመደረጉ ወይም በራሳቸው መፍትሔ እንዲፈልጉ ኤጀንሲው ድጋፍ ባለማድረጉ በሦስቱ ዓመታት በአዲስ አበባ የሚገኙ ሆስፒታሎች በአጠቃላይ አንድ መቶ አምስት ሚሊዮን አራት መቶ አራት ሺሕ ሁለት መቶ ዘጠና ዘጠኝ ብር እንዲያወጡ ተገድደዋል፡፡ ኤጀንሲውም መሸፈን የቻለው 30 በመቶ ጥያቄያቸውን መሆኑን ሪፖርቱ ጨምሮ ያስረዳል፡፡

ኤጀንሲው በዘረጋው 8772 የነፃ የስልክ መስመር እጥረቶች ሪፖርት የሚደረጉ ሲሆን፣ በጥቂት ወራት ውስጥም ሰላሳ አምስት ዓይነት መድኃኒቶች ሪፖርት እንደተደረጉም ወ/ሮ አድና ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የሆነው በእርጉዝ ሴቶች የሚወሰደው ፎሊክ አሲድ የቦሌ ክፍለ ከተማ ጤና ጽሕፈት ቤት ለዘጠኝ ጤና ጣቢያዎች ለወራት ሳያከፋፍል በመቅረቱ እንደሆነ ወ/ሮ አድና ተናግረዋል፡፡ ይህ የመድኃኒት ዘርፉና ሥርጭት ብዙ ችግሮች ያሉበት ሲሆን በተለያየ መንገድም በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ መድኃኒቶች እንደሚገቡና የሕክምና ባለሙያዎችም በስርቆት እያወጡ እንደሚሸጡ አንዳንድ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...