ረቡዕ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል በተደረጉ የተቃውሞ ሠልፎች የስምንት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ ታወቀ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት በአምቦ፣ በዶዶላና ሻሸመኔ በተቀሰቀሰው ግጭት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡ ሻሸመኔ ከተማ በነበረው የተቃውሞ ሠልፍ የአምስት ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ፣ በሦስት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ቦኬ ወረዳ በነበረው ተቃውሞም ለሦስት ሰዎች ሕይወት መጥፋትና ለሦስት ሰዎች አካል ጉዳት መንስዔ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ከ30 በላይ ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል፡፡
ተቀውሞው ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይስፋፋና ባለበት እንዲቆም የክልሉ መንግሥት ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት የክልሉ ወጣቶችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስቧል፡፡ የፀጥታ አካላትም በወጣቱ ላይ አላስፈላጊ ዕርምጃ እንዳይወስዱ መልዕክት ማስተላለፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓቢይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ለኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም የቆሙ በማስመሰል ወጣቱን በማነሳሳት ሰላማዊ ሠልፍ የሚጠሩ አፍራሽ ኃይሎች እንዳሉ ገልጸው፣ እነዚህ ኃይሎች ግን የኦሮሞን ሕዝብ ስለማይወክሉ ጥንቃቄ እንዲደረግ ማሳሰባቸው ተገልጿል፡፡ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በአሁኑ ጊዜ በጀመረው ሥራ ሕዝብ እየደገፈው መሆኑን ገልጸው፣ የሕዝብን ጥቅም ከማይፈልጉ ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ እያደረገ መሆኑን ማስታወቃቸው ተሰምቷል፡፡
በአምቦ ከተማ የነበረው ግጭት ዋነኛ መነሻ የአምቦ ውኃ ፋብሪካ ተነቅሎ ወደ ትግራይ ክልል ሊሄድ ነው የሚል እንደሆነ ተሰምቷል፡፡
በሻሸመኔና በአምቦ ከተሞች በነበረው ተቃውሞ መንግሥትን የሚቃወሙ መፈክሮች ሲሰሙ እንደዋሉ የሪፖርተር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በሱሉልታ ከተማ ተቃውሞ እንዲነሳ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ወጣቶች በአካባቢው የፀጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል፡፡