Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢትዮጵያን ለመጉዳት በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የተጠነሰሱ ሁለት ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦች መምከናቸው ተገለጸ

ኢትዮጵያን ለመጉዳት በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የተጠነሰሱ ሁለት ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦች መምከናቸው ተገለጸ

ቀን:

  • ለዳያስፖራ አባላት መኖሪያ የአዲስ አበባ አስተዳደር መሬት በፍጥነት እንዲያቀርብ ተጠየቀ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ ስድስተኛ ወራቸውን እያገባደዱ የሚገኙት ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ የአፈጻጸጸም ሪፖርታቸውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ የተወሰኑ የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ኢትዮጵያን ለመጉዳት ያቀረቧቸው ሁለት የውሳኔ ሐሳቦችን የያዙ ሰነዶች ላይ ውይይት ሳይካሄድ ማምከን መቻሉን ገለጹ፡፡

ዶ/ር ወርቅነህ ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ሪፖርታቸውን ሲያቀርቡ እንደተናገሩት፣ ስለኢትዮጵያ በጎ አመለካከት በሌላቸው የአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጠንሳሽነት ኢትዮጵያን የሚጎዱ ሁለት ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦች ተዘጋጅተው ነበር፡፡

ከሰነዶቹ አንዱ በአሜሪካ ሴኔት የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 432 እና በኮንግረሱ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ቁጥር 861 ናቸው፡፡ እነዚህ የውሳኔ ሐሳቦችን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆኑ ሴናተሮች ጋር ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ውይይት በማድረጋቸው፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወዳጅ ከሆኑ የኮንግረስ አባላት ጋር በመገናኘትና የቀረቡትን የውሳኔ ሐሳቦች ለማጨናገፍ የሚያስችል ሰነድ በማዘጋጀት ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረትም ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦችን ያዘጋጁ የኮንግረስ አባላት ስለኢትዮጵያ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳላቸው ለማስረዳት በተደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴ፣ ረቂቅ የውሳኔ ሰነዶቹ ውይይት እንዳይደረግባቸውና ነገሩ ባለበት ደረጃ እንዲቆም መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ በአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት አያያዝን በመኮነን ለሦስት ጊዜያት ሊወጡ የነበሩ የውሳኔ ሰነዶች ላይ ሰፊ ርብርብ ተደርጎ እንዳይወጡ ማድረግ እንደተቻለ ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡  

ይሁን እንጂ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2017 የኮንግረስ አባል በሆኑት ክሪስ ስሚዝ የተባሉ ግለሰብ የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚያበላሽና ጉዳት የሚያደርስ ረቂቅ የውሳኔ ሰነድ መቅረቡን ጠቁመዋል፡፡

እንደ አዲስ የቀረበው ሰነድ “Supporting Respect of Human Right  Encouraging Inclusive Governance in Ethiopia” በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን፣ የተሳሳተ ግንዛቤን መነሻ አድርጎ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የቀረበና አግባብነት የሌለው መሆኑን የማስረዳት ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ሁለቱ ሰነዶች ‹‹Supporting Respect of Human Right Encouraging Inclusive Government in Ethiopia›› የሚል ተመሳሳይ ርዕስ ያላቸው፣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ተከስቶ ከነበረው ግጭትና ተቃውሞ በኋላ እ.ኤ.አ. በሴፕቴምበር 2016 የቀረቡ መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሰነዶቹ የኢትዮጵያ መንግሥት ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል በግጭቱ ወቅት መጠቁሙን፣ ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ተማሪዎችን ያላግባብ ማሰሩን፣ እንዲሁም ዜጎች ነፃነታቸውን እንዳይጠይቁ መገደቡን ያወግዛሉ፡፡ በመሆኑም የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የሚሰጠውን ድጋፍ በድጋሚ እንዲያጤን ይጠይቃሉ፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኮሚኒቲ አደረጃጀቶች ጋር በመሆንም ሰነዱ እንዳይፀድቅ መራጭ በሆኑባቸው አካባቢዎች እንዲቃወሙ እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ ነው፤›› ሲሉ ሚኒስትሩ ዶ/ር ወርቅነህ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በአገራቸው የቤት ልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰፊ ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለእነዚህ የዳያስፖራ አባላት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራም ለመጀመር የሚያስችል የቤቶች ዲዛይንና መነሻ ዋጋ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አዘጋጅቶ ቢያቀርብም፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለግንባታ የሚሆን መሬት መስጠት አለመቻሉን ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የአደረጃጀት፣ የክትትልና የድጋፍ ሥራዎች ተጠናክረው ባለመከናወናቸው ፕሮግራሙን ማስጀመር አልተቻለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ የመኖሪያ ቤት ኅብረት ሥራ ማኅበራትን የሚያደራጅ፣ የሚመዘግብ፣ የቤቶቹን ግንባታ የሚከታተልና ሲጠናቀቁ የሚያስረክብ አደረጃጀት፣ እንዲሁም ቦታ የማዘጋጀት ሥርዓት በፍጥነት ሊዘረጋ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ላቀረበችው የሰላም ሐሳብ ላለፉት 12 ዓመታት በላይ በጎ ምላሽ ባለመስጠቱ፣ ኢትዮጵያንና አካባቢውን ከማተራመስ ተግባር መታቀብ አለመቻሉን ዶ/ር ወርቅነህ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን ግንኙነት በጥናት ላይ ተመሥርቶ ለማሳደግና በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በጥናት ላይ በተመሠረተ ትንተና ለመምራት እንዲቻል፣ በኤርትራ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ጥናት ተደርጎ ለመንግሥት መቅረቡን አስረድተዋል፡፡  

ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ልትከተል ያረቀቀችው ‹‹አዲስና ጥልቅ›› የተባለው ፖሊሲ ምን እንደሆነ ‹‹ፍንጭ ይስጡን›› በማለት አንድ የምክር ቤት አባል ሚኒስትሩን ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዶ/ር ወርቅነህ ለጥያቄው ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹ሰነዱን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርበናል፡፡ ሚኒስትሮቹ ተወያይተውበት ሲያፀድቁት ወደ ፓርላማው የሚመጣና የሚፀድቅ ነው፤›› በማለት አልፈውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ለፓርላማው ባቀረቡት ሪፖርት፣ መንግሥታቸው በኤርትራ ላይ አዲስ ፖሊሲ ተግባራዊ እንደሚያደርግና ይህም ዘላቂ መፍትሔ ለኢትዮጵያ እንደሚያመጣ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...