የኢንኦኮ የቶኪዮ ኦሎምፒክ አስተባባሪ ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ጆን ኮኤትስ፣ የኦሺያና ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ጠቅላላ ጉባኤ መጋቢት 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲካሄድ ጉዳዩን ይፋ አድርገውታል፡፡
ኢንሳይድ ዘጌምስ በድረ ገጹ እንደዘገበው፣ ኢንኦኮ በቶኪዮ 2020 ጨዋታዎች አምስት ስፖርቶች ቤዝቦል እና ሶፍትቦል፣ ካራቴ፣ ስኬትቦርዲግ፣ ስፖርት ክላይምቢንግ፣ ሰርፊንግ እንዲካተቱ ዓምና ማድረጉ ይታወሳል፡፡
የኢንተርናሽናል ዒላማ ተኩስ ስፖርት ፌዴሬሽን፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ውድድሮችን የጾታን እኩልነት ባማከለ መልኩ እንዲሆን ኢንኮን ባሳሰበው መሠረት ለውጦችን ለማድረግ አስቧል፡፡
በወንዶች ብቻ ሲካሄዱ የነበሩትን ሦስት የወንዶች የዒላማ ተኩስ ውድድሮች በድብልቅ ቡድኖች መካከል በሚካሄዱ ተተክተዋል፡፡ ኢንተርናሽናል ጁዶ ፌዴሬሽንም ባለፈው ታኅሣሥ ለኢንሳይድ ዘ ጌምስ እንደገለጸው፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የነጠላ ድብልቅ የቡድን ጁዶ ውድድር የሚካተት ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል በላከው መግለጫ እንዳመለከተው፣ ይህ ለውጥ ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኖች አሁን ባላቸው ፕሮግራም ላይ ተጨማሪ ማሻሻያዎችና ለውጦች እንዲያደርጉ ያግዛቸዋል፡፡ ቶኪዮ በጉዳዩ ዙሪያ የፋይናንስ ጫና ያመጣል አያመጣም የሚለውን በማጥናት ላይ መሆኗም ታውቋል፡፡
እንዲለወጡ አልያም እንደ አዲስ እንዲካተቱ ከተፈለጉት የስፖርት ዓይነቶችና ውድድሮች መካከል የወንዶች ጨዋታ ብቻ የነበሩት የሴቶችም ጭምር እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹ ሁለቱንም ጾታዎች በማቀላቀል ድብልቅ ውድድሮችን ለማድረግ ታልሟል፡፡
የውድድሮቹ ቅጥ (ፎርማት) የተዘጋጀው በሁለቱም ጾታ በስድስት የክብደት ደረጃዎች ነው፡፡ በወንዶች ከ73 ኪ.ግ. በታች፣ ከ90 ኪ.ግ. በታችና ከ90 ኪ.ግ. በላይ ሲሆን፣ የሴቶች ከ57 ኪ.ግ. በታች፣ ከ70 ኪ.ግ. በታችና ከ70 ኪ.ግ. በላይ ውድድርን ይዟል፡፡ ሌሎች ስፖርቶች ቀስት፣ ጠረጴዛ ቴኒስና ትራይትሎንን ጨምሮ የድብልቅ ጾታ ቡድን ውድድሮችን ጨምሮ የድብልቅ ጾታ የቡድን ውድድሮችን ለማካተት ሲታቀድ፣ በሴቶች የቦክስ ጨዋታ ሁለት የክብደት ዘርፎችም (ካታጎሪዎች) ታሳቢ ሆነዋል፡፡
በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚኖሩት ውድድሮች 310 ሊደርሱ፣ አሊያም ሊጨምሩ እንደሚችሉ የኢንኦኮ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮኤትስ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ አስተባባሪ ኮሚሽን የቀረቡትን ማመልከቻዎች ከኢንኦኮ ፕሮግራም ኮሚሽን ጋር ሚያዝያ 27 ቀን 2009 ዓ.ም. ካጤነ በኋላ ግብረ መልሶችን ይመረምራል፡፡ የፕሮግራም ኮሚሽኑ በበኩሉ ለኢንኦኮ ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ በሐምሌ ወር የውሳኔ ሐሳቡን እንደሚያቀርብ፣ በቀጣይም ለውጦችንና አዳዲስ የተካተቱ ውድድሮች ይፋ እንደሚደረጉ ታውቋል፡፡