Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ከሽልማት ባሻገር ያስቡ ይንቀሳቀሱ!

የአገራችን የውጭ ምንዛሪ ቋት ሞልቶ አያውቅም፡፡ በፍላጎታችን ልክ የውጭ ምንዛሪ ከግምጃ ቤታችን ያገኘንበት ጊዜ የለም፡፡ የቱንም ያህል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ቢኖርም የውጭ ምንዛሪ ፍላጎቱን ሙሉ ለሙሉ ለማሟላት መንገዱ ሩቅ እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህም ቢባል የአገራችን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መሄዱ ግን ያሳስባል፡፡ እጥረቱ ብቻም ሳይሆን ያለችውንም ጥቂት የውጭ ምንዛሪ በአግባቡ ለመጠቀም ብዙ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡

ክፋቱ ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እየጨመረ በሄደበት በዚህ ወቅት የውጭ ምንዛሪ ምንጭ የሆነው የወጪ ንግድ ገቢ ከዓመት ዓመት እያሽቆለቆለ፣ አሸማቃቂ ውጤት እየተመዘገበበት በመምጣቱ፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ አድርጎታል፡፡

ቢሆንልንማ አገሪቱ በየዓመቱ ለገቢ ንግድ ከምታወጣው ይልቅ የወጪ ንግዳችን ገቢ ትርፍ የሚታይበት በሆነ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ ወጪ ንግዱን ለማሳደግ የታቀዱ ዕቅዶች ግማሽ ላይ ቀርተዋል፡፡ ይገኛል ከተባለው ይልቅ እየተገኘ ያለው ግማሽ ያህሉ ብቻ እየሆነ በመምጣቱ የገቢ ንግድ ወጪያችን በአብዛኛው የሚሸፈነው ከሌሎች የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የወጪ ንግዳችን የሚጠበቅበትን ያህል እመርታ አልታይበት ለማለቱ ሌላኛው መገለጫ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች ወደ አገር ቤት የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ መጠን ከገቢ ንግዱ ይልቅ በየጊዜው ብልጫ እያሳየ መምጣቱ ነው፡፡

ዓመታዊው የወጪ ንግድ ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለመሙላት ሲያጣጥር፣ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎች የሚላከው ገንዘብ ግን ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ተሻግሯል፡፡ በአጭሩ በወጪ ንግድ በኩል ከሚመጣውና በዳያስፖራው በኩል ለቤተመዘድ በሚላከው ዶላር መካከል ያለው ልዩነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ መጥቷል፡፡

ይህም የሚያሳየው የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ብዙ ሥራ እንደሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ባንኮች በወጪ ንግድ ገቢ አማካይነት ያገኙት የነበረው ጥቅም እየቀነሰባቸው፣ የውጭ ምንዛሪ ፈላጊዎችም በሚፈልጉት መጠን ስለማያገኙ የንግድና የኢንቨስትመንት ሥራቸው እየተጎዳ ነው፡፡ በመሆኑም ምንዛሪ ለማግኘት ሲሉ ለወራት ወረፋ መጠበቅ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ ከባንኮቹ አንፃር ሲታይ ከዓመታዊ ትርፋቸው ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያለው ይኸው የውጭ ምንዛሪ ግኝት ነው፡፡ የባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግኝት እያነሰ መምጣቱ ዓመታዊ ትርፋቸው ላይ ተፅዕኖ እያሳረፈ እንዲመጣ አድርጎታል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ግኝታቸውን ለማሳደግ የተለያዩ አማራጮችን እንዲፈልጉ አስገድዷቸዋል፡፡

ከሦስትና አራት ዓመታት ወዲህ ባንኮች ደንበኞቻቸውን በተለይም የገንዘብ አስቀማጮችን ቁጥር አበራክተው የተቀማጭ ገንዘባቸውን መጠን ለማሳደግ ሲሉ ገብተውበት እንደነበረው ዓይነት ብርቱ ፉክክር፣ የውጭ ምንዛሪ ለማሰባሰብም እንዲሁ የተለያዩ የመወዳደሪያ ስልቶችን እየተገበሩ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በኢንዱስትሪው ውስጥ የውጭ ምንዛሪያቸውን ለማጎልበት በማለት በዚህን ያህል ደረጃ ፉክክር ሲያደርጉ ያልታዩት ባንኮች፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ምን ያህል እንደባሰባቸው የሚሳብቅ ደረጃ ላይ እንደሚገኙ የሚያሳይ አካሄድ ውስጥ ገብተዋል፡፡ የውጭ ገንዘቦች ዝውውር በባንኮቻቸው በኩል እንዲያልፍ ለማድረግ ተጨማሪ ወጪም እያወጡ ነው፡፡

በባንኮቹ መካከል ውድድሩ ያነጣጠረው ከወጪ ንግድ ገቢ የበለጠ የውጭ ምንዛሪ መገኛ እየሆነ የመጣውን የውጭ ሐዋላ ገንዘብ በመቀበል ላይ ሲሆን፣ በብር መንዝረው ዶላሩን ለራሳቸው ለማስቀረት መሯሯጥ ይዘዋል፡፡ ‹‹በኛ በኩል የተላከዎን የውጭ ምንዛሪ ሲቀበሉ ይህንን እንሸልምዎታለን፤›› የሚሉ የማታወቂያ ጋጋተዎችን ማስጋባት ጀምረዋል፡፡ እንደነገሩ የተጀመረው የሽልማት ነገር አሁን ወደ ሁሉም  ባንኮች እየተዛመተ መጥቷል፡፡

ዶላር በባንካችን ከላካችሁ ቤት፣ መኪና፣ ሞባይል፣ ትራክተር፣ ባጃጅና ላፕቶፕ እንሸልማን በማለት ለደንበኞቻቸው ጥሪ እያደረጉ ነው፡፡  20 ሺሕ ዶላር የተላከለት እስከ 12 ሺሕ ብር የሚደርስ ነፃ የሽርሽር ፕሮግራም ዕድል እንደሚሰጡ ማስታወቂያ የሚያስነግሩ ባንኮች አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተጨማሪ ዶላር ለማግኘት ነው፡፡ እንደ ቢዝነስ ከታየ እንዲህ ያለው ውድድር መልካም ነው፡፡ ደንበኛን ለማግኘት የሚጠቀሙበት መላ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አማራጮችን በመጠቀም የሚፈልጉትን መጠን ለማግኘት መነሳሳታቸውም ቢሆን ጤናማ ነው፡፡ ደንበኞች በምርጫ እንዲገለገሉ የተሻለ ነገር ለማቅረብ ዕድል ይሰጣል፡፡

ብዙ ደንብኞችን ለማፍራት ከተፈለገ ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማፍሰስም ተገቢ ለመሆኑ ባንኮቹ እንሸልማለን ለሚሉት ንብረት እያወጡ ያለውን ወጪ ምሳሌ ማድረግ ይቻላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ገቢን ለማሳደግ ተብሎ የሚደረገው እንቅስቃሴ ምን ያህል አዋጭ እንደሆነ ለማወቅ ግን ከባድ ነው፡፡ ይህንን የሚያውቁት ባንኮቹ ናቸው፡፡

ነገሩን በሌላ አንፃር እንየው ከተባለ ግን ዶላር ለማግኘት እየተደረገ ያለው ውድድር ዶላሩን ከጥቁር ገበያ እንደመግዛት አይቆጠርም ወይ? በማለት ጥያቄ የሚያነሱም አሉ፡፡ ምክንያቱም በየዕለቱ ከምንሰማው የውጭ ምንዛሪ መግዣና መሸጫ ዋጋ አንፃር ሲታይ፣ ባንኮቹ ዶላር ለማግኘት እንሰጣለን የሚሉት ሽልማት የሚያወጣውን ዋጋ በሚያገኙት ዶላር ላይ ደምረን ካየነው ዶላሩን የገዙበት ዋጋ ከዕለታዊ መግዣና መጫረቻ ዋጋ በላይ ሆኖ ስለሚገኝ ነው፡፡ በየዕለቱ የዶላር ሽያጭ ዋጋ ከተተመነለት በላይ የመሆኑ ነገር ምን ያህል ያወጣ ይሆን? የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዶላር በውድ ዋጋ መሸመት መጀመራቸውን ግን ያሳየናል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለው አካሄድ በተቆጣጣሪው ባንክ በኩል እንዴት ይታይ ይሆን?

እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች መልስ የሚያሻቸው ቢሆንም፣ የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችትና ግኝት አቅም ከፍ ለማድረግ ግን ባንኮቹ ሌሎች አማራጮችን ማየት ይኖርባቸዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪው በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ እንዲተላለፍ ለማድረግ አሁን እየተደረጉ ካሉት የሽልማት ፕሮግራሞች የተሻለ ነገር ማምጣት አለባቸው፡፡

መንግሥትም ቢሆን ዜጎች ገንዘባቸውን በባንኮች በኩል እንዲልኩ ለማድረግ የሚያበረታታ እገዛ ማድረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም ዛሬ የወጪ ንግድ ገቢውን እየበለጠ የመጣው የዳያስፖራው ገንዘብ በባንክ ከሚላከው ይልቅ መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች የሚገባው እንደሚበልጥ በማመን ዜጎች የውጭ ገንዘብ ዝውውርን በባንክ በኩል የማድረግ ልማድ እንዲዳብሩ ርብርብ ማድረግ ይጠይቃል፡፡ ገንዘብ በሐዋላ ለመላክ፣ የአስተላላፊ ድርጅቶች የሚያስከፍሉትን ከፍተኛ ገንዘብ ማካካሻ መንገድ ማሰብም ይገባል፡፡ በባንክ በኩል ገንዘብ በመላካቸው ዜጎች ተጠቃሚ መሆን እስካልቻሉ ድረስ የሚልኩበት መንገድ የተጣበበ ስለሚሆን እዚህም ላይ ልዩ ልዩ ማሻሻያዎችን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  

በመሆኑም ዶላር ለማግኘት ሲባል ሽልማት ማዘጋጀት ብቻውን በቂ አይሆንም፡፡ መንግሥትም ሆነ ባንኮች ለዘላቂ መፍትሔ ብዙ መጣር፣ መጣጣር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ላኪዎችም በባንኮች በኩል በመላላክ ለአገር ድጋፍ መስጠት መቻል አለባቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ የውጭ ምንዛሪው ለአገር ጉዳይ የሚውል እንደመሆኑ ሁሉም በመተሳሰብ ሊጠቀምበት ይገባል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት