Monday, July 22, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ጉልበቱን የጨረሰው የግብርናው ዘርፍ

የግብርና ሥራ ከሞላ ጎደል ከሰው ልጅ ዕድሜ ጋር ተቀራራቢነት ያለው መስክ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሰው ልጅ ገና ከጥንታዊ የጋርዮሽ ዘመን አንስቶ በአደንና በዕፀዋት ለቀማ ላይ የተመሠረተ አመጋገብ ነበረው፡፡ በኋላም የሚፈልጋቸውን ዕፀዋትና የሰብል ዝርያዎች በሚኖርበት አካባቢ እየዘራ፣ እያራባና እየተከለ ለመመገብ ጥረት ማድረግ ጀመረ፡፡ እህል የማብቀል ዘዴውንም ከእጅ ወደ ዶማ፣ በኋላም በእንስሳት ጉልበት ታግዞ እስከማረስ ደረሰ፤ ይለናል በሃሮማያ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የተደረገ የጫንያለው ዓለሙ የድኅረ ምረቃ መመረቂያ ጽሑፍ ጥናት መግቢያ፡፡

አገራችን የቅድመ ሰው መገኛ እንደመሆኗ ብቻ ሳይሆን፣ ከአክሱም የሥልጣኔ ዘመን አንስቶ የሥራ ባህል ያለው ሕዝብ ባለቤት እንደመሆኗ፣ ከላይ የተጠቀሰው ታሪካዊ ዳራ አይመለከታትም ማለት አይቻልም፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ ግብርና ሁለትና ሦስት ሺሕ ዓመታትን ተጉዞም ከእንስሳት ጉልበት፣ ከጠባብ መሬት እርሻና ኋላቀር የአስተራረስ፣ የአስተራረም፣ የአስተጫጨድና የአወቃቅ አካሄድ አልወጣም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሰፋፊ መካናይዝድ እርሻና በማሽነሪ የታገዙ የግብርና ኢንቨስትመንት ሙከራዎች ቢኖሩም፣ እንኳንስ ተስፋፍተው ለአርሶ አደሩ ልምድ ሊያሰፉ ይቅርና በውስጣቸው ካለው የኪራይ ሰብሳቢነትና የ‹‹ወጨበሬ›› መረብ ሊወጡ አይችሉም፡፡ የፕሮፓጋንዳውንም ያህል የተሳካ መስክ መሆን አልቻለም፡፡

በዚህም ምክንያት ነው የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የግብርና ሙያ ልምድ እንዳለው፣ አንድ የአገር ተቆርቋሪ ዜጋ፣ ‹‹የግብርናው ዘርፍ አሁን ባለው አካሄድ ጉልበቱን ጨርሷል፤›› ሲል ለመሟገት የሚወደው፡፡ መከራከሪያዎቹን አንድ በአንድ ለማንሳትም ሞክሯል፡፡

እየተሟጠጠ ያለ ምርታማነት

እውነት ነው ከ25 ዓመታት በፊት የኤርትራ ጥቂት ደጋማ ሥፍራዎችን ጨምሮ በአገሪቱ ከ43 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ሰብል አይመረትም ነበር፡፡ ይህ በግርድፉ መረጃ የተያዘ አኃዝ በድርቅ ወቅት ቢያሽቆለቁልም ላለው የአገሪቱ ሕዝብ ከሞላ ጎደል የሚደርስ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ በተጀመረው አዲስ ግብርና ተኮር ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እስካለፈው ዓመት ድረስ 300 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል፡፡ (ያውም የኤርትራ አንዳንድ አውራጃዎች ምርት ሳይካተት) ይህ ዕድገት እንዲመጣ አርሶ አደሩ በጉልበቱ ካከናወነው ጥረት ባሻገር የመንግሥት በጎ ዕርምጃዎች መኖራቸው አይካድም፡፡ ጥቂቶቹን ለመግለጽ፣ የመሬት ባለቤትነት ካርታ መስጠቱ የፈጠረው የባለቤትነት ስሜት፣ የግብርና ባለሙያ ድጋፍ መጠናከር፣ የማዳበሪያና አነስተኛ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት መሻሻል፣ የመሠረተ ልማት ማደግ፣ የገበያ ተኮር ምርታማነት ማዘንበልና የውኃ አጠቃቀም መሻሻልን ማንሳት ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁሉ ማርሾች ግን ጥርሳቸውን እየጨረሱ የመጡ ስለሆነ አዲስ የግብርና አብዮት መቀስቀስ አለበት ባይ ነኝ፡፡

በቀዳሚነት የማዳበሪያ አጠቃቀምን ማንሳት ይቻላል፡፡ ይህ የአፈር ለምነትና ምርታማነትን ለመጨመር የሚረዳ ግብዓት ለረዥም ዓመታት ይቀርብ የነበረው በመንግሥት ከመሆኑ ሌላ በግዳጅ ጭምር አርሶ አደሩ እንዲጠቀም ይደረግ ስለነበር፣ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ነበረበት፡፡ ያም ሆኖ አርሶ አደሩ ባለው ልማዳዊ የእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ ዘዴ (Agronomic Practice) ማሳውን ፆም በማሳደር የአፈር ለምነትን ለመጠበቅ ከመሞከር የተሻለ ፋይዳ አለው፡፡

እንዲያም ሆኖ ግን የአገሪቱ የማዳበሪያ አጠቃቀም ካለን የእርሻ ስፋትና የአርሶ አደር ብዛት አንፃር እጅግ ዝቅተኛ የሚባል ነው፡፡ ከግብርና ሚኒስቴር የወጣ የ15 ዓመታት ማዳበሪያ አጠቃቀም መረጃን ብንጠቅስ በ1994 ዓ.ም. 286 ሺሕ 641 ዳፕ፣ ዩሪያ 170 ሺሕ 901 ወደ አገር ውስጥ ሲገባ፣ በዘገምተኛ ዕድገት ባለፈው ዓመት በድምሩ ከ2.8 ሚሊዮን ኩንታል ያነሰ ማዳበሪያ ነው የገበየው፡፡ እንደዚያም ሆኖ የገባው ሁሉ ተሸጦ ጥቅም ላይ እንደማይውል መረጃው ያስገነዝባል፡፡

እንግዲህ ይህ አኃዝ ከ1 ሚሊዮን 221 ሺሕ 480 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ካሉት ኢትዮጵያ 66.6 በመቶው ለግብርና ልማት ምቹ በሆነበት፣ ሕዝቡም 100 ሚሊዮን በተጠጋበት ሁኔታ ዝቅተኛ ተጠቃሚነት ነው፡፡ ይሁንና በአርሶ አደሩ ውስጥ አሁንም ማዳበሪያን የሚገዛው እንደ ‹‹ግብር›› ግዴታው ስለሆነበት እንጂ፣ ምርቱን ለማሳደግ እንደሆነ የሚረዳው ውስኑ ነው፡፡ በዚህ ላይ የማዳበሪያ መግዣ ዋጋው እየጨመረ በመምጣቱ ከዚህ በኋላ አጠቃቀሙ እየቀነሰ ይሄድ እንደሆነ እንጂ፣ ተጠናክሮ ሊቀጥል አይችልም፡ (በእርግጥ ዘንድሮ ደግሞ አርሶ አደሩ የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ገጥሞናል እያለ ነው)፡፡

መንግሥትም ቢሆን ይህንኑ ተገንዝቦ በውጭ ምንዛሪ በውድ ዋጋ አምጥቶ በድጎማና በብድር ለአርሶ አደሩ ከመስጠት ለመላቀቅ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው በቀዳሚው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሊገነባቸው የሞከራቸው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ሥራ ለማስጀመር መሞከሩ ነበር፡፡ ይሁንና ከአቅም በላይ የተንጠራራው ትልም ይክሸፍም ይሞከርም ሳይረጋገጥ ‹‹ውሻን ያነሳ ውሾ›› ተብሎ ሰባት ዓመታት እያለፉ ነው፡፡

በሌላ በኩል አርሶ አደሩ በራሱ ማሳና በአነስተኛ ወጪ እንዲያዘጋጀው የሚፈለገው ባህላዊ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) የታሰበውን ያህል አልተስፋፋም ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች አጠቃቀሙ እያሽቆለቆለ የመጣ ሲሆን፣ በአንፃሩ በትግራይና በቤንሻንጉል ጉሙዝ የተሻለ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከአፈርና ውኃ፣ ከከብት እዳሪና ተረፈ ምርት የሚዘጋጀውና በቀላል የቤተሰብ ጉልበት ሊሰናዳ የሚችለው ይኼ ግብዓት ለምን ሊስፋፋ አልቻለም፡፡ ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው ጥቅም ምን ያህል ነው? የሚሉ ጥያቄዎች በጥናት መመለስ ይኖርባቸዋል፡፡

ምርታማነት ለማሳደግ የኮትቻ አፈር (የመረሬ ዋልካ፣ ሸክላማ አፈር፣ ጥቁር አፈርና መሰሎቹ) አጠቃቀም ለማሻሻል የሚደረግ ጥረትም አለ፡፡ ይህ እንደ አገር ሰፊ ሽፋን ያለውን አፈር የማጠንፈፍ ዘዴ (በቢቢኤምና አይባር ቢቢኤም የማረሻ ዘዴ መጠቀም) የተገኘ ውጤት ነበር፡፡ በአንድ በኩል ውኃውን አጠንፍፎ በማቆር በዓመት ሁለት ጊዜ ለማምረት የተቻለበት በሌላ በኩል ለዘመናት በኮትቻ አፈር ላይ የማይበቅሉ የተባሉ ሰብሎችን ማምረት ተችሏል፡፡ አሳዛኙ ነገር ግን ይህ ተግባር በታሰበው ልክ እየተስፋፋ አለመሄዱ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን በግምብቹ ወረዳ፣ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን፣ እናርጅ እናውጋ ወረዳና ሁለት እጁ እነሴ ወረዳ የታዩ የምርት ልምዶች በቅርብ ርቀት እንኳን ተጠናክረው አልተጓዙም፡፡ ለምን?! ብሎ መፈተሽ ማርሽ ለመቀየር የሚረዳ ይሆናል፡፡

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የውኃ አጠቃቀምን ማሻሻል ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ጥርጥር የለውም፡፡ በተግባርም የታየው ውኃ ገብ አካባቢዎችና አነስተኛ የመስኖ ጅምሮች አርሶ አደሩ በዓመት ሁለት ጊዜ እንዲያመርት እያገዙት መሆኑን ነው፡፡ ይሁንና ከፍተኛ የአገር ሀብትና ጉልበት የባከነበት ‹‹የውኃ ማቆር›› እንኳን ድህነትን ሊያርቅ ይቅርና ብልጭ ብሎ ድርግም ነው ያለው፡፡ መንግሥት በከፍተኛ ጉጉት የገባበት የመስኖ ሥራም እስካሁን ፍሬው አልተቀመሰም፡፡ በአማራ ክልል የጣና በለስ አንድና ሁለት፣ የርብ መስኖ ፕሮጀክትን ማንሳት ይቻላል፡፡ የስኳር የመስኖ ፕሮጀክቱ እነከሰም ተንዳሆና መሰሎቹ የሙስና መፈንጫ ነው የሆኑት፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

በአጭሩ በተያዘው የቆየ አመለካከት እያነከሱ ምርታማነትን አሁን ከደረስንበት በላይ ለማሳደግ መመኘት ዳገቱ ከባድ ነው፡፡ እንዲያውም ላለመንሸራተት መጣር ካልተቻለ ዕልፍ የማይል ሁኔታ ላይ እንዳለን ማጤን ተገቢ ነው፡፡

የምግብ ዋስትናው ተግዳሮቶች

ከዓመታት በፊት በገጠር ያሉ በድህነት ውስጥ የወደቁ ዜጎችን ለመታደግ ከተነደፉት መርሐ ግብሮች አንዱ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ነው፡፡ በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከሚጠቀሱት ሥራዎች አንዱ የልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ነው፡፡ በ1997 ዓ.ም. የተጀመረው ይህ መርሐ ግብር የቤተሰብ ጥሪት እንዳይሟጠጥ በመከላከል የምግብ ክፍተትን ለመሙላት የሚያስችል መርሐ ግብር ነው፡፡ በምግብ ለሥራ ሥርዓት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለማልማትም የሚረዳ ነው፡፡ የማኅበራዊ ልማትንም ለማሳደግ ይረዳል፡፡

በእርግጥም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድርጅት “The State of Food Insecurity in the World” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2012 ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ እየተገበረ ያለው ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም  ከ2006 እስከ 2010 የተሻለ ውጤት ማስገኘቱን አረጋግጧል፡፡ የቅርብ አምስት ዓመታት ሒደቱ ግን ወደኋላ የመመለስ ዝንባሌ እንዳለው ነው ሙያተኞች የሚገልጹት፡፡ በአንድ በኩል ሲደገፉ የነበሩ ዜጎች የምግብ ዋስትና ‹‹ተረጋገጠ!›› ቢባልም ወደኋላ መመለሱ ሲሆን፣ ሌላኛው ግን ፕሮግራሙ በትግራይና በጥቂት የኦሮሚያ ወረዳዎች ካልሆነ በብዙ ቦታዎች ተንገራግጮ እየቆመ በመሆኑ ነው፡፡ (የከተማ ሴፍቲኔትም እስካሁን ያስገኘው ነገር ስለመኖሩ መረጃ የለም፡፡)

በእርግጥ በዚሁ መርሐ ግብር ከ2010 እስከ 2016 (በአገር ደረጃ በየዓመቱ በአማካይ 530 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለዋል፡፡ በዚያው ልክ በመቶ ሺሕ ሔክታር የሚገመት የተጎዳ መሬት አገግሟል የሚል የመንግሥት መረጃ አለ፡፡ እዚህም ላይ ያለው ፈተና ከተተከለው ችግኝ የፀደቀውና ዛፍ የሆነው ምን ያህሉ ነው? የሚለው ጥያቄ ለመመለስ የሞከርን እንደሆነ ነው፡፡

በሌላ ጫፍ የምግብ ዋስትና መርሐ ግብር ፖሊሲ ጫፍ ተብሎ የተቀመጠው የሠፈራ ፕሮግራም ሲሆን፣ ወንዝ የተሻገረ ሥራ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ደርግ ተጠቅሞበት የነበረውን የመንደር ምሥረታ ፖለቲካ ከማጠልሸቱ ባሻገር ለቀጣይ እንደማይገባበት ተደርጎ መነገሩ ሥራውን አውኮታል፡፡ በሌላ መልኩ የፌዴራል ሥርዓቱ ራሱ ለክልሎች በፈቀደው አጥር ከአንዱ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሄዶ መሥፈር ፈፅሞ የማይቻል ተግባር ሆኗል፡፡

የአገራችን ዜጎች ወደ ዓረብ አገሮች አውሮፓ ሳይቀር በሕጋዊ መንገድ ከሄዱ በነፃነት ሠርተው መብላት ሲችሉ፣ በአገር ውስጥ ግን የክልሎችን ድንበር አልፎ መሥራት ዋስትና ያጣ አሳዛኝ ክስተት ሆኗል፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው የትግራይ፣ የአማራና አንዳንድ የኦሮሚያ ወረዳዎች ነዋሪዎች የተትረፈረፈ ለም መሬት ያለባቸው የጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ መንደሮችን ቢመኙም ሊያገኟቸው አልቻሉም፡፡ ‹‹ድሃና ገበያ አልተገጣጠመም ይሏል›› ይህንኑ ነው፡፡

በእርግጥ ፖሊሲው ላይ የተጻፈውን የሠፈራ ፕሮግራም ለመተግበር ተሞክሮ ከ1995 ዓ.ም. እስከ 2004 ዓ.ም. ባሉት ዘጠኝ ዓመታት 241 ሺሕ 903 አባወራዎች ብቻ ናቸው የሠፈሩት፡፡ ከዚያም ወዲህም ቢሆን እዚህ ግባ የሚባል ሠፋሪ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ቦታ ስለመቀየሩ አልተነገረም፡፡ እንግዲህ ከ20 ሚሊዮን የማያንስ ዜጋ የምግብ ዋስትና ችግር እያለበት፣ ሩብ ሚሊዮን የማይሞላ ሠፋሪ ያውም በአሥራ አምስት ዓመት መንቀሳቀሱ ትርጉም የሚሰጠው አይደለም፡፡ ከዚያም በታሪክ አጋጣሚ በተለያዩ አካባቢዎች ሠፍሮ ድህነትን ያሸነፈውና ኑሮውን መቀየር የጀመረው በትንሽ በትልቁ ሲፈናቀልና ሲሰደድ ማየት የዚህ ዘመን አሳዛኙ ክስተት ሆኗል፡፡ 

በግብርናው መስክ ውስጥ ብዙ አገሮች የተቀየሩባቸው የቤት ውስጥ የዘርፍ ሥራዎች ማለትም የዶሮ ዕርባታ፣ አነስተኛ እንስሳት ዕርባታ (በግ፣ ፍየል)፣ እንዲሁም የንብ ማነብ ባህሉም እምብዛም የተቀየረ አይደለም፡፡ እውነት ለመናገር ከተባለ በእነዚህ መስኮችና በደን ልማት ሥራ ያለፈው የደርግ ሥርዓት የተሻለ አደረጃጀት (በኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በወጣቶች፣ በሴቶች) ለማነቃነቅ እንደሞከረ የሚናገሩ አሉ፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ምናልባት በትግራይ ክልል የሚታየው በጎ የተፈጥሮ ሀብት ልማት በአርአያነት ካልተጠቀሰ በሌላ አካባቢ ተቀሰቀሰ የሚባል የዘርፍ አብዮት የለም፡፡ የእንስሳት ዕርባታውም የዘልማድና የቁጥር ማነስ ልክፍት እንደተበተበው ነው፡፡

የተነሳሁበትን ሐሳብ ለማጠቃለል ስሞክር የግብርናው ዘርፍ በተቀረፀለት ፖሊሲ ልክ ሮጦ ጉልበቱን ጨርሷል፡፡ ደግሜ ማለትን እወዳለሁ፡፡ ለማፍታታት ያህል ባለፉት 25 ዓመታት በተሠሩ ሥራዎች ቢያንስ 100 ሚሊዮን ሕዝብ መቀለብ የሚያስችል ምርት እየተገኘ ነው፡፡ አገሪቱ ባስመዘገበችው የተከታታይ ዓመታት ዕድገትም ቢሆን፣ ግብርናው ተገቢውን አስተዋጽኦ ማድረጉ አይካድም፡፡ ይሁንና ግን አሁን ወደ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር መግቦንም በቂ ጥሬ ዕቃ የሚገኝበት መስክ ሊሆን አልቻለም፡፡ ከነበረው አካሄድ እየወጣን ባለመሆኑም በአንድ ዓመት ድርቅ ብቻ ‹‹የዕርዳታ ያለህ›› ከማለት አልዳንም፡፡ በአንድ ክረምት መዛባት አሥር ሚሊዮን ጉሮሮ ዕርዳታ መጠበቁም የዝግመታዊ ለውጡ ምልክት ነው፡፡

እንደ መፍትሔ ምን ይሁን?! ነው መቋጫው፡፡ ይህ ጽሑፍ የአንድ ግለሰብ ዕይታ ቢሆንም፣ በበኩሌ ኋላቀሩን የግብርና መንገድ ለመቀየር የግሌን ምክረ ሐሳብ ለመሰንዘር እወዳለሁ፡፡

አንደኛው በታዳጊ ክልሎችና ሰፋፊ እርሻ ባለባቸው አካባቢዎች የአገር ውስጥ ባለሀብትና ባለሙያውን እየደገፈ ማሰማራት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምንም ዓይነት የብሔርና የፖለቲካ ኮፍያ ሳይበጅለት፣ ከኪራይ ሰብሳቢነት በፀዳ መንገድና በቅንነት መነሳት ግድ ይላል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አልሚ የውጭ ባለሀብቶችን አበረታትቶ መሳብ ያስፈልጋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ መንግሥት ቢጀምረውም እምብዛም ውጤት ያልታየበት የመስኖ ልማት ተጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ እዚህም ላይ በዓመት ለቀናት ብቻ የሚጥልን ዝናብ ‹‹እንደ ቅቤ›› ይዞ ለመጠበቅ ከመሞከር ውኃ ገብ የሆኑ አካባቢዎችን፣ ወንዞችን፣ ሐይቆችንና ባህሮችን በጥልቅ አጥንቶ ያለምንም ፖለቲካዊ ተፅዕኖ መተግበር ግድ ይላል፡፡ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ለመንገድ መሠረተ ልማት ከፍተኛ በጀት እንደሚመድቡ ሁሉ ለመስኖ ልማትም ሙሉ ትኩረት ሰጥተው በከፍተኛ አቅም መታገል ይገባል፡፡ ይሁንና በሙስና ተተብትበው የሚንገታገቱ የውኃ ሥራዎችና የፌዴራሉን የውኃ ኮንስትራክሽን ባሉበት ቁመና ይዞ መቀጠል የሚቻል አይሆንም፡፡

አሁን ያለውን የገጠር አነስተኛ የማሳ እርሻ አሠራር በአንድ ጀንበር ቀይሮ ሁለት ሦስት ጊዜ በዓመት ይመረትበት ማለት የዋህነት ነው፡፡ አሁን ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ የሚባለው ‹‹ከዓመት ሁለት ጊዜ ተመረተ›› እንደ ፐርሰንት በማይሞላው ውኃ ገብ ማሳ እንደሆነ እንጂ፣ ፍፁም ብዙኃኑን የማይወክል ነው፡፡ ስለሆነም ትውልድ እየበዛ፣ የመሬቱ ምርታማነት እየነጠፈና የእርሻ ቦታ እየጠበበ ዕድገት ማሰብ ስለማይቻል በገጠር አገልግሎት፣ መካከለኛ ኢንዱስትሪና ንግድን ማስፋፋት ያስፈልጋል፡፡ ከተሜነት (Urbanization) ማፋጠንም የግድ ይሆናል፡፡ ካልሆነ ግን የገጠር ልማቱ ሞተር ጉልበቱ ብዙ ርቀት የሚወስድ አይደለም፡፡ 

በጥቅሉ አሁን ያለው የገጠርና ግብርና ልማት ጉዞ በአንድ በኩል ጠንካራ የፖሊስ ማሻሻያና አብዮትን ይፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል እስካሁን የተመዘገበውን ውጤት በማስቀጠል ለውጥ ለማስመዝገብ መሞከር ብቻ የትም እንደማያደርስ አውቆ ሁሉን አቀፍ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርበታል የሚል ሐሳቤን ላነሳ እወዳለሁ፡፡ ለዚህ ደግሞ ፖሊሲ አውጪው መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ የግብርና ተመራማሪዎች፣ ባለሙያዎችና ባለሀብቶች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ዕሙን ነው፡፡  

በልዑል ዘሩ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

              

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles