Saturday, June 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአህጉራዊ የፋሽን ትስስር

አህጉራዊ የፋሽን ትስስር

ቀን:

በዓለም የገነኑ የፋሽን ዲዛይነሮች ሥራዎቻቸውን ለማሳየት ከሚጠባበቋቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች አንዱ ኒው ዮርክ ፋሽን ዊክ ነው፡፡ በመድረኩ የተለያዩ አገሮች ዲዛይነሮች አዳዲስ የፋሽን ዲዛይን ለለባሾች ያስተዋወቁበታል፡፡ በኒው ዮርክ ፋሽን ዊክ አልባሳትን ማቅረብ በፋሽን ኢንዱስትሪው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው እንደመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን የፋሽን ዲዛይነሮች መሳተፍ መጀመራቸው መልካም ዜና ነው፡፡ ዲዛይነር ማህሌት አፈወርቅ (ማፊ) በኢትዮጵያ ስብስብ ሥራዎች በዓለም አቀፍ መድረኩ እውቅናን ካተረፉ መካከል ትጠቀሳለች፡፡

የምዕራቡ ዓለም የፋሽን ዲዛይነሮች በሚፈጥሯቸው ልብሶችም ይሁን ጌጣጌጦች፣ ቦርሳዎች አልያም የጫማ ምርቶች የአፍሪካን ጥበብ ማካተት ከጀመሩ ስነባብተዋል፡፡ የኢትዮጵያን የሀገር ባህል ልብስ ዲዛይን ከፈጠራ ሥራዎቻቸው ጋር አዋህደው ለዓለም ማቅረባቸው ለአብነት ይጠቀሳል፡፡ የኢትዮጵያን ዲዛይን ከመዋስ ባሻገር ለኢትዮጵያውያን የፋሽን ዲዛይነሮች የሚሰጠው ቦታም እያደገ መጥቷል፡፡

በዘንድሮው የኒው ዮርክ ፋሽን ዊክ ዝግጅት የልብስ ዲዛይን ጥበባቸውን ለዓለም እንዲያሳዩ የተጋበዙት ዮሐንስ ሲስተርስ ዘንድሮ ከተካተቱ ዲዛይነሮች ውስጥ ናቸው፡፡ እህትማማቾቹ ዲዛይነሮች ‹‹ዘ ላየንስ አራይዚንግ›› እና እናት የተሰኙ ሁለት የአልባሳት ስብስቦች በኒው ዮርክ ፋሽን ዊክ አሳይተዋል፡፡ ባህላዊውን የጥበብ አሠራር ከዘመነኛ ፋሽን ጋር በማዋሀድ ያዘጋጇቸው ልብሶች ከብዙዎች በጎ ምላሽ አስችረዋቸዋል፡፡

ዲዛይነሮቹ ሥራዎቻቸውን በአሜሪካ ካሳዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ የተቀበላቸው ሀብ ኦፍ አፍሪካ አዲስ ፋሽን ዊክ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የፋሽን መሰናዶ፣ ከኢትዮጵያና ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ዲዛይነሮችና ሞዴሎች ተሳትፈውበታል፡፡ ሀብ ኦፍ አፍሪካ በዚህ ዓመት ከዮሐንስ ሲስተርስ በተጨማሪ የፋሸን ዲዛይነሮች ዓይናለም አየለ (ዓይኒ ዲዛይን)፣ እጅጋየሁ ኃይለጊዮርጊስ (እጅግ ጥበብ፣) ሔራን አሥራት (ፈትል ዲዛይን)፣ ዮርዳኖስ አበራ (ዮርዲ ዲዛይን)፣ ለምለም ተክለሃይማኖት (ላሊ) እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ዲዛይነሮችንም አካቷል፡፡

አህጉራዊ የፋሽን ትስስር

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ መድረክ ሥራቸውን ማቅረብ የቻሉ ዓባይ ሹልዝ (ዛፍ ኮሌክሽን)፣ ቤተልሔም ጥላሁን (ሶል ሬብልስ)፣ ፍቅርተ አዲስ (የፍቅር ዲዛይን) እና ሌሎችም የሀብ ኦፍ አፍሪካ ተሳታፊዎች፣ ከሌሎች የአህጉሪቱ ዲዛይነሮች ጋር በአንድ መድረክ ሥራቸውን አሳይተዋል፡፡ በፋሽን ኢንዱስትሪው ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል፡፡ ልብስና ጫማ፣ ቦርሳና ጌጣ ጌጦችም ለገበያ አቅርበዋል፡፡

የፋሽን ትርኢት የመርሐ ግብሩ አንድ አካል የነበረ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያውያኑ ዲዛይነሮች ጎን ለጎን ከሴኔጋል የአዳማ ፓሪስ፣ ከኬንያ የአኔሶፊ አቼራ፣ የአኒያንጎ ፒንጋ እና የአርኖልድ ሙሪቲ፣ ከደቡብ አፍሪካ የፓሌሳ ሞኩቡንግ (ማንቲሽ) እንዲሁም ከናይጄሪያ የጋብየል ሶለመን (ራስል ሶለመን) የፋሽን ፈጠራዎች ታይተዋል፡፡ በመስከረም ማብቂያ በኤግዚቢሽን ማዕከል የቀረበውን የፋሽን ትርዒት እንደ አና ጌታነህ ያሉ ዓለም አቀፍ ሞዴሎች እንዲሁም በርካታ ዲዛይነሮችም ታድመውታል፡፡

መሰል አህጉር አቀፍ መድረኮች ብዙም አይደሉም፡፡ አፍሪካውያን ዲዛይነሮች በተናጠል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባለፈ እንደ አህጉር የሚያስተሳስሯቸው መርሐ ግብሮች ውስን መሆናቸው በኢንዱስትሪው ተፅዕኖ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ አፍሪካ ውስጥ የሚሠሩ አልባሳት ከቀደሙት ዓመታት በበለጠ ተቀባይነት እያገኙ መምጣታቸው አይካድም፡፡ በአህጉሪቱ ደረጃ ዲዛይነሮችን የሚያሳትፉ መድረኰች ቢበራከቱ ካለውም የበለጠ ማደግ ይቻላል፡፡

የክሌርቮያንት ማርኬቲንግ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ማህሌት ተክለማርያም፣ የሀብ ኦፍ አፍሪካ መሥራች ናት፡፡ በፋሽን ትርዒቱ ላይ እንደተናገረችው፣ ኒው ዮርክ ፋሽን ዊክን የመሰሉ ግዙፍ የፋሽን መዳረሻዎች የዓለምን ትኩረት እንዳገኙ ሁሉ፣ አዲስ ፋሽን ዊክ በሚል ሀብ ኦፍ አፍሪካም የዲዛይነሮችን ቀልብ ወደሚስብ የፋሽን መሰናዶ ያድጋል፡፡

የፋሽን ትርዒቱ ብቻ ሳይሆን ውይይቱና ዲዛይነሮችን ከሸማቾች ጋር ያገኛኘው ገበያም ሀብ ኦፍ አፍሪካን አለ የተባለ የፋሽን መዳረሻ እንደሚያደርጉ ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡ በሳፋየር አዲስ ሆቴል የዛፍ፣ ማንቲሾ፣ አዳማ ፓሪስና ሌሎችም የአህጉሪቱ ብራንድ የሆኑ ልብሶች፣ ጫማዎችና ቦርሳዎች በተሸጡበት ወቅት ገዢዎች በቀጥታ ዲዛይነሮቹን ማግኘት ችለዋል፡፡ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡት የፋሽን ዲዛይነሮች ተሞክሮ የተለዋወጡበት አጋጣሚም ተፈጥሯል፡፡

ሀብ ኦፍ አፍሪካ የተጀመረው ከስድስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ማህሌት እንደምትናገረውም፣ ዲዛይነሮች እውቅና እንዲያገኙ ለማድረግ የተጠነሰሰ ነው፡፡ በፋሽን ኢንዱስትሪው ለውጥ ለማምጣት ያለመ መርሐ ግብር በመሆኑ፣ ለታዋቂና ለጀማሪ ዲዛይነሮችም የሚሆኑ መሰናዶዎች እንደሚካተቱ ትገልጻለች፡፡ ‹‹ዘንድሮ ወደ 21 ዲዛይነሮች መድረክ ላይ አሳይተዋል፡፡ ሌላ 14 ዲዛይነሮችም ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡ በአፍሪካ ዴቨሎፕመንት ባንክ የተዘጋጀ ወደ 100 ዲዛይነሮች የታደሙት ማስተር ክላስና ወርክሾፕም ነበር፤›› ትላለች፡፡

ሀብ ኦፍ አፍሪካ፣ የአፍሪካውያን ዲዛይነሮች ምርጫ እየሆኑ ከመጡ መድረኮች አንዱ እየሆነ ነው፡፡ እንደ አፍሪካን ሞዛይክ ያሉ አህጉራዊ መድረኮችም ይጠቀሳሉ፡፡ በዲዛይነሮቹ መካከል የልምድ ልውውጥ ከማድረግ በተጨማሪ ለገበያ ትስስርም አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱም ይታመናል፡፡

በሀብ ኦፍ አፍሪካ መሳተፍ ለሚፈልጉ ዲዛይነሮች የወጣውን ማስታወቂያ ተከትለው ማመልከቻ ካስገቡ 50 ዲዛይነሮች መካከል 30ው ተመርጠዋል፡፡ ዲዛይነሮቹ ሥራቸው ታይቶ ምን ያህሉ በጀማሪ ደረጃ ሥራቸውን እንደሚያሳዩና ምን ያህሉ ለፋሽን ትርዒት የሚሆን የአልባሳት ስብስብ ማቅረብ እንደሚችሉ ተመዝኗል፡፡ ማህሌት ዲዛይነሮች የሚገናኙበት መድረክ መፈጠሩ እንደ ባለሙያ ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦች የሚያንሸራሽሩበት ነው ትላለች፡፡ ዲዛይነሮቹ ራሳቸውን ለማስተዋወቅና ሥራዎቻቸውን በመላው ዓለም ለመሸጥ መጠቀም ስላለባቸው መንገዶችም ተወያይተዋል፡፡

የአፍሪካን ዲዛይነሮች ለተቀረው ዓለም በማስተዋወቅ በኩል ሀብ ኦፍ አፍሪካ እንደ ቮግ ኢታልያ ባሉ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ሽፋን ማግኘቱ ትልቅ ሚና እንዳለው ታስረዳለች፡፡ የውሜንስ ዌር ዴይሊ ጋዜጠኛ ለዲዛይነሮቹ ግብረ መልስ መስጠቷ ሌላው ጥቅም ነው፡፡ ‹‹እንደነዚህ ያሉ ዕድሎች ሲመቻቹ በመድረኩ መሳተፍ የሚፈልጉ ዲዛይነሮች ቁጥር ይጨምራል፡፡ ዲዛይነሮቹ ባላፉት ዓመታት መድረኩን ለመታወቅና ገበያ ለማግኘትም እየተጠቀሙበት ነው፤›› ስትል ታስረዳለች፡፡

መድረኮቹ መኖራቸው የተለያዩ አፍሪካ አገሮችን ቱባ ባህል የተመረኮዘ የፋሽን ዲዛይን ለማስተዋወቅ ይረዳል፡፡ እንደ ኒው ዮርክ ፋሽን ዊክ ካሉ መድረኮች ጋር ለመስተካከል ጊዜ ቢወስድም፣ ቀጣይነታቸው እስከተረጋገጠ ድረስ ዘርፉን ይደግፋሉ፡፡

ማህሌት የኢትዮጵያ የፋሽን ዘርፍ እያደገ ለመምጣቱ እንደ ማሳያ ከምትጠቅሳቸው መካከል ባለሙያዎች የሚገናኙበት ማኅበር መመሥረቱን ነው፡፡ ዲዛይን የተደረጉ ልብሶች ለገበያ የሚቀርቡበት ዋጋ መወደዱና ሌሎችም መሰናክሎች ዘርፉን ቢፈትኑትም ለውጦች መኖራቸውን ታምናለች፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ባለሙያዎች ከሌሎች የአፍሪካ ዲዛይነሮች ጋር የሚተሳሰሩበት መድረክ አስፈላጊነቱንም ትናገራለች፡፡ ‹‹አፍሪካ ትኩረት እያገኘች ነው፡፡ ትልልቅ ብራንዶች የአፍሪካን ፕሪንት ይጠቀማሉ፤›› የምትለው ማህሌት፣ አህጉራዊ የገበያ ትስስር ሲጎለብት ዘርፉን የበለጠ እንደሚያድግ ታስረዳለች፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መከፈትና፣ እንደ ኤችኤንድኤም፣ ፒቪኤችና ካልቨን ክላይን ያሉ ብራንዶችም መመረታቸው ለዲዛይነሮች ጥሩ ዕድል እንደሚከፍት ትገልጻለች፡፡ በአህጉር ደረጃ ጠንካራ ትስስር እንዲኖር መንግሥታት ከቀረጥ ነፃ የንግድ ሥርዓትን በመዘርጋትና በሌላም መንገድ ዲዛይነሮቹን መደገፍ እንዳለባቸውም ታክላለች፡፡

ደቡብ አፍሪካዊቷ ዲዛይነር ፓሊሳ ሞኩቡንግ ከአሥር ዓመታት በላይ የደቡብ አፍሪካን ባህላዊ አልባሳትን ከምዕራባውያን ዲዛይን ጋር አዋህዳ ልብሶችን በማቅረብ ትታወቃለች፡፡ በደቡብ አፍሪካ ስመ ጥር ከሆኑ የፋሽን ዲዛይነሮች አንዷ የሆነችው ፓሊሳ፣ ማንቲሾ የተባለውን የልብስ ብራንዷን ይዛ በፋሽን ትርዒቱ ዲዛይኖቿን አሳይታለች፡፡ ከልብሶቹ መካከል ለገበያ ያቀረበቻቸውም ነበሩ፡፡አህጉራዊ የፋሽን ትስስር

‹‹ዲዛይን ያረኳቸውን ልብሶች ብዙ ቦታ አቅርቤያለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳሳያቸው ሰው ደስ ሊለው እንደሚችል ገምቼ ነበር፡፡ ሆኖም ከጠበቅኩት በበለጠ ሰዎች ሥራዬን በጣም እንደወደዱት ሲነግሩኝ ተገርሜያለሁ፤›› ስትል ነበር የፋሽን ትርዒቱን የገለጸችው፡፡ ኢትዮጵያ ስትመጣ የመጀመሪያዋ በመሆኑ በምግቡ፣ በቋንቋው፣ በትራንስፖርቱ፣ በሰዎች የእርስ በርስ ትስስርም መገረሟ አልቀረም፡፡ ባህላዊ ልብስና ጌጣ ጌጥ በብዛት የሚሽጥበት ሽሮ ሜዳ ገበያም ቀልቧን ስቦታል፡፡ ከሁሉም በላይ የተገረመችው ግን በፋሽን ዲዛይነሮቹ ሥራዎች መሆኑን ትገልጻለች፡፡

በቀጣይ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚካሄድ የፋሽን ሳምንት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሳየችውን የልብስ ስብስብ ከሌሎች አልባሳት ጋር አጣምራ ታቀርባለች፡፡ ‹‹ስብስቡ ለሰዎች የሚሰጠውን ስሜት የፈተሽኩበት መድረክ ነው፡፡ የተጠቀምኩትን ቀለምና የጨርቅ ዓይነት ሰዎች እንዴት እንደሚያዩትም ተረድቻለሁ፤›› ትላለች፡፡ ሰዎችን ሊማርኩ ይችላሉ ብላ ያመነችባቸውን ልብሶች ስታቀርብ ምቾትንም ከግምት እንደምታስገባም ታክለላች፡፡

በፋሽን ትርዒት ከምታቀርባቸው ልብሶች አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት የሚሸጡ ሲሆኑ፣ የተቀሩት ሰዎች ገዝተው ዘወትር ባይለብሷቸውም እይታ የሚስቡና የሚያዝናኑ ናቸው፡፡ የፓሊሳን ልብሶች በኤግዚቢሽን ማዕከል ያቀረቡት ከኢትዮጵያና ሌሎችም የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ሞዴሎች ነበሩ፡፡ በስብስቧ 12 ልብሶች አሳይታለች፡፡

ዲዛይነሯ፣ አፍሪካውያን የፋሽን ዲዛይነሮች ከአህጉሪቱ ውጪ ሥራዎቸውን የሚያሳዩባቸው መድረኮች እየበዙ መምጣታቸውን ትገልጻለች፡፡ በተለይም የምዕራቡ ዓለም እውቅ ዲዛይነሮች የአፍሪካን ዲዛይን በልብስ ወይም በሌሎችም ምርቶቻቸው ሲያካትቱም ይታያል፡፡ ‹‹የአፍሪካ ዲዛይን ማራኪ ስለሆነ ላይወዱት አይችሉም፡፡ አፍሪካ የሚመረቱ ጨርቆችን፣ ቀለሞችንና ቅርፆችን ከዲዛይናቸው ጋር የሚያዳቅሉትም ለዚሁ ነው፤›› ትላለች፡፡

አንዳንድ ዲዛይነሮች የአፍሪካን ዲዛይን በዓለም የማስተዋወቅ ጉዳይ ለአህጉሪቱ የፋሽን ዲዛይነሮች ብቻ የተተወ አድርገው መውሰዳቸውን አትቀበለውም፡፡ በየትኛውም አገር የሚሠራ ዲዛይን በሌሎች አገሮች ካለው ጋር መወራረሱ የሉላዊነት ውጤት ነው ትላለች፡፡ በአፍሪካውያን መካከል ጠንካራ ትስስር የሚፈጥሩ እንደ ሀብ ኦፍ አፍሪካ ፋሽን ዊክ ያሉ መድረኰች አናሳ ናቸው የሚለው ሐሳብም አይዋጥላትም፡፡ ‹‹የመድረኮቹን ቁጥር ከመጨመር በፊት ያሉት ምን ያህል ብቁ ናቸው የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፤›› ትላለች፡፡

ፓሊሳ እንደምትናገረው፣ አንድም ይሁን ሁለት አህጉራዊ መድረኮች ቢኖሩ ደረጃቸውን የጠበቁ ማድረግ ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ መድረኮቹ የአህጉሪቱ ምርጥ ዲዛይነሮች ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት እንዲሁም ጀማሪ ዲዛይነሮች የሚማሩበት መሆን አለባቸው፡፡ ‹‹ሁላችንም የምንችለውን እያደረግን ነው፡፡ ሆኖም እንደ አህጉር ያለን ታሪክ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ነባራዊ ሁኔታንም ከግምት ማስገባት ያስፈልጋል፤›› ትላለች፡፡

አሁን ካሉት መድረኮች የአፍሪካ ፋሽን ኢንዱስትሪ ያለበትን ደረጃ የሚመጥኑ ስንቶቹ ናቸው? የሚለው አጠያያቂ ነው፡፡ ምን ያህሉ የዓለምን ትኩረት እየሳቡ ነው? የሚለውን ጥያቄም ማንሳት ይቻላል፡፡ ዲዛይነሮቹ በተናጠል የሚያደርጉት ጥረት የተቀረውን ዓለም ትኩረት እያገኘ ቢሆንም፣ እንደ አህጉር በተዋቀረ መልኩ ያለው እንቅስቃሴ ብዙ እንደሚቀረው ማህሌትና ፓሊሳ ይስማማሉ፡፡ ባለሙያዎቹ ቅድሚያ የሚሰጡት ያሉትን መድረኮች ጠንካራ ለማድረግ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ አህጉራዊ ትስስርና ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንደሚጎለብትም ያምናሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...