Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበ13 ቢሊዮን ብር ወጪ ከ2000 በላይ የጤና ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል

በ13 ቢሊዮን ብር ወጪ ከ2000 በላይ የጤና ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል

ቀን:

በኢትየጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት በጤና መሠረተ ልማት አቅርቦት ላይ ያተኮሩ 2,483 ፕሮጀክቶች በ13 ቢሊዮን ብር ወጪ ተከናውነው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አሚር አማን (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ሆስፒታሎች፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ላቦራቶሪዎች፣ የጥናትና ምርምር ክፍሎች፣ የደም ባንኮች፣ የመድኃኒት ማከማቻ መጋዘኖች፣ ወዘተ ከተካተቱባቸው ከእነዚሁ የጤና መሠረተ ልማት አቅርቦት ፕሮጀክቶች መካከል 265ቱ የተከናወኑት በክልል መንግሥታት ሲሆን፣ የቀሩት 2218 የሚሆኑት ፕሮጀክቶች የተሠሩት ደግሞ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ነው፡፡

በ13 ቢሊዮን ብር ወጪ ከ2000 በላይ የጤና  ፕሮጀክቶች ተከናውነዋል

 

በክልል መንግሥታት ለተከናወኑት ፕሮጀክቶች 9 ቢሊዮን 275 ሚሊዮን ብር በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለተሠሩት ደግሞ፣ 3 ቢሊዮን 827 ሚሊዮን 380 ሺሕ ብር ወጪ ተደርጎባቸዋል፡፡

በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከተሠሩት ፕሮጀክቶች ውስጥ ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ ያለው የኮተቤ የሥነ አዕምሮ አጠቃላይ ሆስፒታል ይገኝበታል፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ቅጽር ግቢ የተገነባውም ባለ ሦስት ፎቅ ተጨማሪ ሕንፃ የፕሮጀክቱ አካል እንደሆነና እያንዳንዱም ግንባታ 350 አልጋዎች እንዳሏቸው ተገልጿል፡፡

ለአለርትና ለቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታሎች ባለሙያዎች እንዲሁም ለአለርት ዳይሬክተሮች አገልግሎት የሚውሉ 129 መኖሪያ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡

እያንዳንዳቸው ሰባት ፎቆችን የያዙ የአዳማ የሥልጠና ማዕከል፣ የኮተቤ የሥነ አዕምሮ ጠቅላላ ሆስፒታልና የኢትዮጵያ የመድኃኒት ፈንድና አቅርቦት አጀንሲ የአስተዳደር ሕንፃዎች ግንባታ 80 ከመቶ ያህል ተጠናቋል፡፡ ከዚህም ሌላ የመብራትና የውኃ አቅርቦት ለሌላቸው 1,682 ጤና ጣቢያዎች በፀሐይ ኃይል የሚሠራ መብራትና ንፁህ የመጠጥ ውኃ  ገብቶላቸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ለዓድዋ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለአንጋጫና ቦዲቲ፣ በአፋር ክልል ለሉጊያ ሆስፒታሎች ግንባታ ሚኒስቴሩ የ218 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡    

በአገር ደረጃ የተያዘውን የእናቶች ሞት በተለይም የገጠር እናቶች ሞት ለመቀነስ እንዲቻል በገጠር ወረዳዎች ለሚገኙ ጤና ተቋማት 410 የአነስተኛ ቀዶ ሕክምና ማዕከላትን መገንባታቸውንና በዚህም አሥር ሚሊዮን ያህል እናቶች ባሉበት የሕክምና አገልግሎቱን የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡

አንድ ጤና ኬላ ለአምስት ሺሕ፣ አንድ ጤና ጣቢያ ደግሞ በአማካይ ለ25 ሺሕ የኅብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንዲሰጥ የተያዘውን ዕቅድ መቶ ፐርሰንት ማሟላት ተችሏል ይህም ሊሳካ የተቻለው ከ3600 በላይ ጤና ጣቢያዎችና ከ16,000 በላይ ጤና ኬላዎች በመኖራቸው ነውም ብለዋል፡፡

የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜን ዕቅድ እንዳበቃ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታሎች ሽፋን 29 በመቶ ነበር፣ አሁን ግን ክልል መንግሥታት ትኩረት ሰጥተው ባከናወኑት ሥራ ምክንያት 265 ተጨማሪ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታሎችን በመገንባት ሽፋኑን ወደ 59 በመቶ ከፍ ለማድረግ ተችሏል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲከናወኑ ሦስት ፈተናዎች ወይም ችግሮች እንደነበሩ፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው ግንባታዎች ላይ ከዲዛይን ጀምሮ ሲሠሩና ከተሠሩም በኋላ የሚታየው የጥራት ችግር እንደሆነ፣ ሁለተኛው ችግር ሥርጭቱ ላይ ኢፍትሐዊ የሆነ ክፍተት እንዳለ፣ ሦስተኛው ችግር ደግሞ የፕሮጀክቶች መዘግየት እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

እነዚህን ችግሮች በማየት የመፍትሔ አቅጣጫዎች ተቀይሰው እየተተገበሩ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የግንባታውን ብቻ ሳይሆን ከሰው ሀብቱ፣ ከመድኃኒቱና ከአጠቃላይ የጤና አገልግሎቱ ላይ የጥራት ችግር መኖሩ ተደርሶበታል፡፡ በዚም የተነሳ ለዚህ መፍትሔ የሚሆን የጥራት ማስጠበቂያ ፓኬጅና ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል፡፡

ጤና ተቋማት ሲገነቡ የሕዝቡን ፍላጎት፣ አገሪቱ ከደረሰችበትና ወደፊት መድረስ ካሰበችው ዕድገት ጋር ሊጣጣሙ የሚያስችሉ ዲዛይኖች እንደተዘጋጁና በእነዚህም ዲዛይኖች መሠረት የጥራት ችግርን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የግንባታዎችን ጥራት ለማስጠበቅ ከዚህ በኋላ፣ ቀድሞ ከተሠሩት ግንባታዎች መካከል ችግር ያለባቸውን በምን መንገድ ተለይተው ይስተካከሉ? ወደፊት የሚሠሩት ጥራታቸው እንዴት ይጠበቁ? ከግንባታው ጋር የተያያዙ የኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎቶችን ጥራት አጠባበቅ ምን ይመስላል? የሚለው የሚታይም ይሆናል፡፡

ከመሬት ቀጥሎ ለስርቆት፣ ለብክነትና ለሙስና ተጋላጭ የሆነው የኮንስትራክሽን ዘርፍ መሆኑን ጠቁመውም፣ በተለያዩ ክልሎች በጤና ጣቢያዎችና በሆስፒታሎች ግንባታ ላይ በዝርዝር በተጠቀሱት ችግሮች ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑ ኮንትራክተሮች ተዘፍቀው መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም ኮንትራክተሮች መካከል የተፈረደባቸውና ክሳቸው በሒደት ላይ ያሉ እንደሚገኙበት አክለዋል፡፡

ይህም ሊሆን የቻለው የመብራትና ውኃ አገልግሎት መጓተት፣ ግንባታው ከተጀመረ አንስቶ የሰው ኃይል ታስቦበት ተቀጥሮና ሠልጥኖ አለመጠበቁ፣ በሕክምና መሥሪያዎች በኩል ከግዥ ጀምሮ እስከ ተከላ ድረስ የመጓተት ባህሪ መታየቱ፤ አዲስ አበባ ውስጥ ያሉት ጤና ተቋማት ተገንብተው በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረጉ ተነግሯል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...