Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጨቅላ ሕፃናትን ክትባት በፈለጉት ጤና ተቋማት ማግኘት እስከምን?

የጨቅላ ሕፃናትን ክትባት በፈለጉት ጤና ተቋማት ማግኘት እስከምን?

ቀን:

የመጀመሪያ ልጇን ብራስ የእናቶችና ሕፃናት ሆስፒታል ለወለደችው እናት፣ ለሕፃኗ የመጀመሪያውን መሠረታዊ ክትባት ለማግኘት ምንም ችግር አልገጠማትም፡፡ የሕፃኗን የክትባት መረጃ የያዘውን ቢጫ ካርድም ከሆስፒታሉ ወስዳለች፡፡ ቀጣዩን ክትባት እዛው ብራስ፣ በኋላ ደግሞ ለመታረስ ከነበረችበት ሲኤምሲ አካባቢ በሚገኝ ጤና ጣቢያ አስከትባለች፡፡ በሲኤምሲ ጤና ጣቢያ ክትባቱን ስታስከትብም ከየት መጣሽ፣ መሸኛ አምጪ ወይም የጀመርሽበት ጨርሽ ያላት አልነበረም፡፡

ከሲኤምሲ ወደ መደበኛ መኖሪያዋ ገርጂ ከመጣች ወዲህ ቀጣዩን ክትባት ለልጇ ለማሰጠት ከሄደችበት ድል ፍሬ ጤና ጣቢያ ግን እንደቀደሙት ክትባቶች ነገሮች ቀላል አልነበሩም፡፡ ከፊቷ ከነበሩት ወላጆች ጥቂቶቹ ማብራሪያ ሳይሰጣቸው ከክፍሉ ሳያስከትቡ ይወጡ እንደነበረ ታስታውሳለች፡፡

ከሦስት ሳምንታት በፊት ክስተቱ የገጠማት እናት፣ እንደሌሎቹ እናቶች ሳታስከተብ አልተመለሰችም፡፡ እሷም ሆነች ባለቤቷ ከነርሷ ጋር ሙግት ገጥመው ልጃቸውን ማስከተብ ችለዋል፡፡

ይህች እናት እንደምትለው፣ ማንኛውም ጨቅላ ሕፃን መሠረታዊ ክትባት የማግኘት መብቱ በጤና ፖሊሲው እስከተረጋገጠ ድረስ እናቶች ከየትም ይምጡ ከየት ቢጫውን የሕፃናት ክትባት አስረጂ ካርድ እስከያዙ ድረስ በሚቀርባቸውና በሚያመቻቸው ጤና ተቋም ማስከተብ አለባቸው፡፡

ሕፃናትን ለማስከተብ ቸልተኛ በሆነው ማኅበረሰብ ውስጥ ክትባት ከትቡልኝ ብሎ የሚመጣን ቤተሰብ እዚህ ሂድ እዚያ ሂድ ብሎ መመለስ፣ ክትባት ላይ የሚሠራውን የግንዛቤ ሥራ እንደሚጎዳው በማስታወስም፣ እሷ በሄደችበት ቀን በጤና ጣቢያው ክትባት ክፍል ያየችው አቀባበል ተጠቃሚውን ግራ የሚያጋባ፣ አስከትባለሁ ብሎ የመጣው በፍርሃት እንዲሸማቀቅ የሚያደርግ እንደነበር ትናገራለች፡፡

የራሷን አስመልክታ ‹‹ለምን ልጄ አትከተብም?›› ብላ ላነሳችው ጥያቄ ‹‹የጀመርሽበት ቦታ ጨርሺ›› ከማለት ባለፈ ምክንያቱ እንዳልተነገራት በመግለጽም፣ ጨቅላ ሕፃናት የታቀፉ እናቶች ያለበቂ ማብራሪያና ምክንያት በሥፍራው ማስከተብ እንደማይችሉ እየተነገራቸው መመለሳቸው አግባብ አንዳልሆነ ታክላለች፡፡

የድል ፍሬ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ደግፌ ዳዬ፣ በሚመሩት ጤና ጣቢያ ላይ ከሕፃናት ክትባት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ ከተገልጋዮች ቅሬታ መነሳቱን አስመልክተን ለጠየቅናቸው በሰጡት መልስ ‹‹የክትባት ሥርዓቱን ከማሳለጥ አንፃር ክትባቱን ሥርዓት ለማስያዝ እንጂ ክትባት አልከለከልንም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ሕዝቡ ግንዛቤ አግኝቶ እንዲመጣ እየለፋንና እየመጣልን ነው፡፡ የመጣልንን ወላጅ ልጅህን አንከትብም ብለን አንመልስም፡፡ ክትባት ከጀመሩበት ጤና ተቋም መሸኛ እንዲያመጡ አሊያም የጀመሩበት እንዲጨርሱ እንመክራለን፤›› ብለዋል፡፡

አንድ ሰው በፍላጎቱ ወይም ቀድሞ ከነበረበት ሠፈር በመልቀቁ ምክንያት ወደሚቀርበው ጤና ተቋም ሄዶ ማስከተብ የሚችልበት አግባብ አለ፡፡ ጤና ጣቢያችሁ ለምን ወላጆች ሕፃን ይዘው ከመጡ በኋላ የጀመራችሁበት ሂዱ ይላል ብለን ላነሳነው ጥያቄም፤ ይህ የሚደረግበት ምክንያት አንድ ሕፃን ክትባት ጀምሮ እንዳያቋርጥ ለመከታተል፣ ከጀመረበት ጤና ተቋም ለምሳሌ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ክትባቶች ወስዶ ያለ ምንም መሸኛ ሌላ ጤና ጣቢያ ቢጫውን የሕፃኑን ካርድ ይዞ ቢቀጥል፣ ቀድሞ የጀመረበት ቦታ ላይ ክትባቱን እንዳቋረጠ ተደርጎ ስለሚቆጠርና አጠቃላይ ሪፖርት ተሠርቶ ለአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሲተላለፍ የቁጥር መፋለስን ስለሚያስከተል ነው ብለዋል፡፡

‹‹ክትባት አንከትብም አላልንም›› የሚሉት አቶ ደግፌ፣ የተሳሳተ መረጃ ወደ ማዕከል እንዳይተላለፍ ከማድረግ አንፃር ‹‹መሸኛ ይዛቸሁ ኑ ወይም የጀመራችሁበት ጨርሱ እንላለን›› ብለዋል፡፡ ማንኛውም ወላጅ የሕፃኑን ቢጫ ካርድ ይዞ በመንግሥትም ሆነ በግል ጤና ተቋማት በመሄድ ልጆቹን ማስከተብ እንደሚችልም አክለዋል፡፡

በክትባት ክፍሉ በኩል ለተገልጋዩ በቂ መረጃ እንደማይሰጥ ለቀረበው ቅሬታም፣ ከተገልጋዩም ሆነ ከአገልግሎት ሰጪው በኩል ክፍተት እንዳለ፣ አንዳንዴ ተገልጋዮች ከክፍሉ ቅሬታ ይዘው እሳቸው እንደሚመጡ፣ ሆኖም እሳቸው ቢያስረዷቸውም ተገልጋዮች ለመቀበል ፈቃደኛ እንደማይሆኑና ከነቅሬታቸው እንደሚሄዱ ይናገራሉ፡፡ ‹‹በክትባት ክፍል ያሉ ባለሙያዎች፣ እንደማንኛውም አገልግሎት ሰጪ አካል ሙሉ ለሙሉ ተጠቃሚውን ያስደስታሉ ባልልም መልካም እየሠሩ እንደሚገኙ አምናለሁ፤›› ብለዋል፡፡

በአንድ ጤና ጣቢያ ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም ሆነ በግል ጤና ተቋማት ወላጆች ገጥሞናል ብለው የሚያነሱት ሌላ ችግር ዛሬ ቁጥር ስላልሞላ መድኃኒት አይከፈትም ተብለው ለሌላ ቀን እንዲመለሱ መደረጋቸውን ነው፡፡

አንድ ሕፃን ከተወለደ እስከ 15 ቀናት  ባሉት ጊዜያት የሚሰጠውን ‹‹ቢሲጂ›› የቲቢ መከላከያ ክትባት ለማስከተብ ሲሄዱ ሰው እስኪሞላ ጠብቁ፣ በዚህ ቀን ተመለሱ፣ አሊያም ስልክ ተዉና እንደውልላችኋለን የሚል ምላሸ ተሰጥቷቸው እንደሚያውቅም ወላጆች ነግረውናል፡፡

ይህንን አስመልክቶ ሙያዊ አስተያየት የሰጡት አቶ ደግፌ፣ ‹‹ቢሲጂ›› የተባለው የቲቢ መከላከያ ክትባት አንዱ ጠርሙስ የሚይዘው ለ20 ጨቅላ ሕፃናት የሚሆን ነው፡፡ በመሆኑም ለአንድ ወይም ለሁለት ሕፃን ብሎ መክፈቱ አዋጭ ስላልሆነ የወላጆች አድራሻ ተይዞ አሥር ሕፃናት  እስኪሞሉ በመጠበቅና ለወላጆች በመደወል ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ የምናደርግበት፣ አሊያም ቀነ ቀጠሮ ተይዞ ተከታቢዎች ሰብሰብ ሲሉ የሚከተቡበት አሠራር አለ ብለዋል፡፡

የሕፃናት መሠረታዊ ክትባት ፖሊሲ የጸደቀ ነው፡፡ ሕፃናትም መከተብ አለባቸው፡፡ ሕፃናት ከተወለዱ ጀምሮ እስከ አምስት ዓመታቸው ድረስ የተለያዩ በሽታዎችን የሚከላከሉበትን ክትባቶች እንዲወስዱም ይመከራል፡፡ በኢትዮጵያም ጨቅላ ሕፃናት ከተወለዱ አንስቶ መሠረታዊ የሚባሉትን አሥር ክትባቶች መውሰድ አለባቸው፡፡

በኢትዮጵያ ክትባት ሽፋኑ እየተስፋፋ በመምጣቱም ሕፃናት ከተለያዩ በሽታዎች እየተጠበቁ ይገኛሉ፡፡ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የክትባት አስተባባሪ አቶ በፍቃዱ በቀለ እንደሚሉትም፣ በየጤና ጣቢያውና በየሆስፒታሉ በሚመጡ ሕፃናት ላይም ከፍተኛ የበሽታዎች መቀነስ አዝማሚያ ታይቷል፡፡

ሕፃናት አንድ ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ የሚሰጠውን ነፃ ክትባት መውሰድ አለባቸው፡፡ የግልም ሆኑ የመንግሥት የጤና ተቋማት ደግሞ ይህንን የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ በየትኛውም የጤና ድርጅት የትኛውም ሕፃን የመከተብ መብት ያለው ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ላይም ከጤና ተቋማትና ከባለሙያዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡

አንድ ሕፃን በአንድ ጤና ጣቢያ መከተብ ጀምሮ ሌላ ጤና ጣቢያ መከተብ ቢፈልግ መብቱ የተጠበቀ ሲሆን፣ ቀጣይ ክትባትን እናንተ ዘንድ እየመጣ እንዲጨርስ  የሚል ወረቀት ቀድሞ ከጀመረበት ጤና ተቋም እንዲያመጣም አሠራር ተዘርግቷል፡፡ በዚህ መሠረት የመቀበልና የማስተናገድ ግዴታ አለባቸው፡፡

ቢጫ የክትባት ካርድ እስከተያዘ ድረስ ደብዳቤ ማምጣት ይጠበቅበታል? ብለን ላነሳነው ጥያቄም፣ በድንገት የሄደ ሰው ቢጫውን ካርድ እስከያዘ ድረስ ማስከተብ ይችላል፡፡ ጤና ጣቢያውም ማስረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡ ቀድሞ ክትባት ከጀመሩበት ሥፍራም በስልክ ማረጋገጥ የሚቻልበት አሠራር አለ፡፡

ከግል ሕክምና ተቋማት የሚመጡ ሕፃናት በየትኛውም የመንግሥት ጤና ተቋማት ክትባት ማግኘት መቻላቸውን በተመለከተም፣ ምንም የሚያግድ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ የግል ጤና ተቋማትም አሥሩንም ክትባቶች ከመንግሥት በነፃ  እንደሚያገኙና የአገልግሎት ብቻ አስከፍለው እንደሚከትቡ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ክትባቱን የሚሰጠው በነፃ በመሆኑ የተደራሽነት ችግር የለም የሚሉት አቶ በፍቃዱ፣ እስከ ሁለት ዓመት የሚሰጥ ተጨማሪ ክትባት ለመጀመር ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ያቀዳቸው ነገሮች እንዳሉም ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 ተሠርቶ 2017 ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ የሥነ ሕዝብና ጤና ጥናት እንደሚያሳየው፣ በአገር አቀፍ  ደረጃ ከ12 እስከ 23 ወራት ዕድሜ ውስጥ ካሉ አሥር ሕፃናት አራቱ የቲቢ፣ የኩፍኝ፣ የፖሊዮና የሄፒታይተስ ቢን ጨምሮ መሠረታዊ የሚባሉትን ስምንት ክትባቶች ሳያቋርጡ ወስደዋል፡፡ በከተማ የሚገኙ ሕፃናት ገጠር ከሚገኙት በላቀ ስምንቱን መሠረታዊ ክትባቶች ማለትም በከተማ 65 በመቶ በገጠር 35 በመቶ ወስደዋል፡፡

በአፋር 15 በመቶ ሕፃናት ብቻ መሠረታዊ ክትባት በማግኘት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አዲስ አበባ 89 በመቶ መሠረታዊ የሕፃናት ክትባት በመስጠት ከፍተኛ የሽፋን ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡

ትግራይ 67 በመቶ፣ አማራ 46 በመቶ፣ ኦሮሚያ 25 በመቶ፣ ሶማሌ 22 በመቶ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 57 በመቶ፣ ደቡብ 47 በመቶ፣ ጋምቤላ 41 በመቶ፣ ሐረሪ 42 በመቶ፣ ድሬዳዋ 76 በመቶ ሕፃናት መደበኛውን የበሽታ መከላከያ ክትባቶች ያገኙ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሲታይ ደግሞ ሽፋኑ 39 በመቶ ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አወዛጋቢው የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ጉዳይ

በኢትዮጵያ የሕገ መንግሥት ማሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውዝግብ የሚቀሰቀስበት...

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...