Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እንረጋጋ እንጂ!

ሰላም! ሰላም! ‹እንቁላል ቀስ በቀስ ሽጉጥ ይሆናል› ማለት ጀመርን አሉ። ዕድገታችን የማያመጣብን ጉድ የማይለዋውጥብን አባባል የለም። አሁን እስኪ አንድ እንቁላል በስንት ተገዝቶ፣ ስንቴ ተቀቅሎ፣ ስንቴ ተጠብሶ ተበልቶ ነው ወደ ሽጉጥነት ያደገው? የሚለው ጥያቄ የእኔም ነው። በጥያቄ ላይ ጥያቄ ስንከምር በትውልድ ላይ ትውልድ ይደረብና ይኼው ነገር ሁሉ ርችት ይሆናል። እውነቴን እኮ ነው። በቀደም ከእንቅልፌ ስነቃ ስልኬ ጢን ብላ ጮኸች። የፈረደበት የሎተሪ ‹ጅንጀና› ነው ብዬ እያዛጋሁ ሳየው ከፖሊስ የተላከ ነው። ስንት ደም መጣጭ ባለበት አገር አሁን እኔ ምን አድርጌ ነው ብዬ ‹ስታክ› አደረግኩ። ከዚያስ አትሉም? ‹በማታ እያሽከረከሩ እንቁላል ከተወረወረብዎ መኪናዎን እንዳያቆሙ፣ ዝናብ መጥረጊያ እንዳይጠቀሙ› ይላል። ይብላኝ መኪና ደረሰኝ አልደረሰኝ እያለ ኮርኪ ሲፍቅ ለሚያመሽ እያልኩ ነፍሴ ተመለሰች። ‹‹እንኳን መኪና ባጃጅም ሲደላ እኮ ነው የሚገዛው፤›› ስለው ለባሻዬ ልጅ፣ ‹‹መጀመርያ መንገድ ሲኖር እኮ ነው፤›› አለኝ።

‹‹ተው እንጂ የምታማው ብታጣ ይኼን መንግሥት በመንገድ ታማለህ?›› አልኩት። መንገድና መሬት ያለነገር ሌላ ሥራ የላቸው ያስብላል እኮ የእኛ አገር ነገር። ‹‹አለ ብለህ ነው? ይኼው ገጭ እጓ ስንል አይደል እንዴ የምንውለው። ተሠርቶ ተሞቷል አቦ…›› ብሎ ተነጫነጨብኝ። ንጭንጩ አጓጉል ሲሆንብኝ ጠረጠርኩ። የባሻዬ ልጅም በሰሞኑ የጫት አቅርቦት እጥረት የተዛባበት ነገር ይኖር ይሆን ብዬ ነዋ። ጉድ እኮ ነው። የሚበላውን እየተወራወርን በማይበላው አንጀታችንን እያሰርን ሆኗል የእኛ ጉዞ። ደግሞ ወሬ ተብሎም ከባለሥልጣናት አንስቶ እስከ ሠፈር አውደልዳዮች ድረስ ችግር ተብሎ ስለቅጠሉ ይተነተንልናል። ቆይ ግን መቼ ነው ቲማቲም፣ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ፍራፍሬ… ዋጋቸው እንደ ኳስ ሲጎን ሲፈርጥ ጉዳዬ ተብሎ የሚወራው? ነው ምርቃናው ነው ያዘጋጋን? ፈዘናል እኮ ጎበዝ!

አንዳንዴ ነገረ ሥራችን ሁሉ ጨዋታ ብቻ ይሆን የለ? ዶላርን አይመለከትም ይኼ። በሩቅ እንደምንሰማው የቢል ጋጋታ ቀልባችንን አስጨንቆ የሚይዝበት ቀን እስኪመጣ ቶሎ ቶሎ መጨዋወቱ ልባም መሆን ይመስለኛል ለማለት ነው። አደራ ደግሞ እንዲህ ስላችሁ ሥራውን ትታችሁ የዶላር ምንዛሪን የሚያስቀንስ ወሬ ወዳድ ስትሰበስቡ እንዳትውሉ። ሆሆ! ዘንድሮ ሰው አላውቅ ያለው ‘ኔትወርክ’ የሚስተካከልበትን ቀን ብቻ ሳይሆን ነገር የሚመጣበትን ቀዳዳ እኮ ነው። እንዲያው እኮ!  ብቻ በልቶ ብቻ ማደር እየከፋብን ስለሄደ (ለነገሩ ጫትም ቢሆን እየበላን አለን) ይኼን ያህል እጅ መስጠት የለብንማ። ታዲያስ! ለአንዳንዱ ሰው እኮ ጨዋታም ምግብ ነው። እና ባሻዬ ፈገግ ብለው ይሰሙኛል። አወራለሁ።

“አሁን እየተወለዱ ላሉ ሕፃናት ልጆች የሚወጡ ስሞች ምን እየተባሉ እንደሆነ ሰምተዋል?” ስላቸው ስላቅ መሆኑን አስቀደሞ ግብቷቸው (እንኳን ይችን የዝንብ ጠንጋራም አንስትም ዓይነት አስተያየት እያዩኝ) “በል እስኪ ንገረኝ?” ይሉኛል። “ወንዶ፣ በለጬ፣ ውኃ የትናየት፣ ስናፍቅሽ መብራቴ፡ ቆቦ ስመኝሽ…” ስላቸው አቋርጠውኝ የሚጠጡት ቡና ትን እስኪላቸው ካንጀታቸው ሳቁ። “ለመሆኑ የቱ ነው ለሴት የቱ ነው ለወንድ የወጣው?” ቢሉኝ፣ “ተባዕትና አንስት ሰዋሰው አልተቀላቀለም እንዴ?  ልማቱም ፆታ፣ መልክ፣ ቀለም ሳይለይ እንደ ጳጉሜን ካፊያ ለሁሉ እየተዳረሰ ነው፤” አልኳቸው። እንዲህ ስንጫወት ቆይተን፣ “የሐበሻ ተንኮሉ ቃላት ማዋደድ ላይ ተገድቦ ቢቀር ምንኛ ሸጋ ነበር?” ብለው ሲመሰጡ ታዘብኩ። ባሻዬ እንዲያ ሲሉ የዴሞክራሲው አየር እንደ ልብ መንፈስ የጀመረ ቀን ከሐሳብ ልዩነትና ከቃላት ምልልስ አልፈን የምንሻገረውን ድልድይ በሐሳባቸው እያፈረሱት ያሉ ይመስላሉ። ደግሞስ ቢዘገይ እንጂ ይቀራል ብላችሁ ነው?

እናላችሁ እንደ ወሬው ሁሉ የከተማውን በሰው፣ በግንባታ ሥራ፣ በበርጫ ቅስቀሳ (ለነገሩ ገና ምኑ ዓይተን) መዋከብና መጨናነቅ ስታዘብ አዕምሮዬ ፈጥኖ የሚያስበው ብዙ ነው። በተለይ በተለይ የሕዝቡንና የግንባታው ብዛት ሌላ ነው። ያለው ለስሚንቶና ለብረት ወጪ ሲጨነቅ የሌለው ያው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ያስቀመጡትን አቅጣጫ ሳይጣረስ በሁነኛ ምርቃና በምናብ ሲገነባ ይውላል። አንድ ዳያስፖራ ወዳጄ፣ “ይህች ከተማ እንዳላደግኩባት ሁሉ እኮ ነው የተለወጠችብኝ። የማውቃቸው ሕንፃዎች የጣቶቼን ቁጥር አልሞሉ ብለውኛል፤” ሲለኝ ነበር። ይኼን ሲለኝ አጠገቤ ተቀምጦ የሚያዳምጥ አዳናቂ ወዳጃችን ጣልቃ ገብቶ፣ “ታዲያ በፊውዳሎች ጊዜና በመደብ ተከፋፍለን በተቧቀስንበት ዘመን ምን ሊሠራ ፈልገህ ኖሯል? ዕድሜ ለኢሕአዴግ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ መጠቀም ለቻለ የባለፀግነት ካባን እየደፋ ከተማችንን አስዋበልን?” እያለ ነገር ያዳምቃል።

በበኩሌ ከሕንፃውና ከተንቦረረቀቀው የከተማችን ግዛት በላይ የሆነው የሕዝብ ቁጥር ውል እያለኝ የማስበውን አላውቀው ብዬ በከፊል ነበር የማዳምጣቸው። በተስፋም በፍርኃትም አጮልቀን ነጋችንን እንደምናይበት መነጽር መጨለምና መብራቱን አነፃፅር የነበረው ታዲያ በ‘ዳያስፖራው’ እና በ‘ሎካሉ’ ወዳጄ የሐሳብ ሙግት ነው። “የቤት ችግር እያንገበገበን የሕዝቡ ወደ መሀል አገር ፍልሰት እያደር እየባሰበት አሁን የሚሠራውስ ሥራ ምን ያህል ያስተነፍሰናል? ተሠራ የሚባለው መንገድ እኮ ገና እንደተከፈተ ይጠበን ጀምሯል፤” ሲል ‘ዳያስፖራው’፣ ‘ሎካሉ’ ቀበል አድርጎ፣ “ሥራ ያጣ መነኩሴ ማለት አንተ ነህ። ደግሞ ሌላ መንገድ ይቆፈራ። የሰፋውን ማስፋት እንደገና ማስፋት። ዕድሜ ለቻይና! በደህና ቀን በቁጥርም በሥራም በልጠውን ደግሞ እነሱ እያሉ። ብናጣም እነሱ አሉ። የሚሰጡት፣ የሚቸሩት፣ የሚሠሩት ሁሉ ነገር ልክ እንደ ጫማቸው ቶሎ የሚያልቅ አገር አጋር አድርገህ በፈጠርህ፣ በዚህ ትብሰለሰላለህ?” ሲለው ሁላችንንም ፈገግ አስባለን። ‘ብድር እንደ ጫማ ሲሮጡ ቢቃለል፣ አበበ በቂላ ባዶ አድርጎልን ነበር’ ማለት እኮ ነው የቀረን እንደ ወዳጃችን አባባል። ወይ ቻይናና እኛ!

ታዲያላችሁ በዚህ ሁሉ መሀል አንድ ቻይና ደንበኛ አጋጠመኝ። እሱን ይዤ ምንም የተጨበጠ መረጃ ሳልይዝ የመኪናው ሻጭ ይገኛል ወደተባልኩበት ሥፍራ ሄድኩ። ሳገኘው ከቻይናው ጋር አስተዋወቅኳቸው። መኪናዋን ሳናያት ስለሞዴሏ ስለ ይዞታዋ ተነጋገርን። በመጨረሻም ወደቆመችበት ሥፍራ ተጉዘን ደርሰን መከፋፈት ስንጀምር 2007 ሞዴል ሲለን የነበረችው አውቶሞቢል 2004 ሞዴል ሆና አረፈችው። “2007 ሞዴል አላልከኝም ነበር?” አለው ቻይናው ኮስተር ብሎ።  የመኪና ነጋዴው፣ “ምን ‘ኦልሞስት’ እኮ እዚያው ነች…” አይል መሰላችሁ።

ኋላ የባሻዬን ልጅ አግኝቼ አላስችለኝ ብሎ ሳቄ እያመለጠኝ በመገረም ስነግረው፣ “ድሮም ሥራን ሳያድጉበትና ሳያውቁት መሥራት ትርፉ ይኼው ነው። ዛሬ ሁሉም ብር አለበት ወደተባለ ሥራና ሙያ ይጎርፋል። የሰው አንጀት ውስጥ ቢላ ከሚረሳው ሐኪም ጀምሮ፣ ነገ አስይዘህ ከባንክ ልትበደርበት የምትችለውን ቀላል የማይባል ንብረት እስከሚሸጥልህ ነጋዴ ድረስ ሰልባጅ ሱሪ ስትገዛ እንደምትደራደረው ሊደራደርህ ይፈልጋል፤” ብሎኛል። እሱ ደግሞ እንዲያው እንዴት እንዴት አድርጎ እንደሚያስብ እኮ ነው የሚደንቃችሁ። እንዳለው ይኼ የመኪና ነጋዴ አንድ ብጣቂ ቲሸርት እንደሚሸጥ ሁሉ ‘ሞዴል’ ዋጋና የገዢ ፍላጎት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድር ነገር ‘ኦልሞስት’ ብሎ ሊያጠጋጋው ሲሞክር አይደንቅም? ቻይናው ራሱ ታዝቦት ምን እንዳለኝ ነገርኳችሁ ግን? የእኔ ነገር። “አንበርብር ቋንቋችሁ በጉራማይሌ ቅጥ ሲያጣ ዝም እያላችሁ፣ ይኼው ዛሬ የምትናገሩትንና የምትሠሩትን ነገር ማስተዋል ከበዳችሁ፤” ነበር ያለኝ። “እግዚኦ!” አሉ ባሻዬ ነገር ሲበዛባቸው!

እንሰነባበት እስኪ። ቻይናው ደንበኛዬ አብሮኝ ብዙ ቢንከራተትም የሚፈልጋትን አውቶሞቢል መርጦ ገዝቶ መለያየታችን አልቀረም። እንደ ቆይታችን ሁሉ ጠቀም ያለ ‘ኮሚሽን’ አሽሮኛል። የያዝኩትን ይዤ ሁሌም ኪሴ ሲሞላ መጀመርያ እንደማደርገው ለሽሮና ለበርበሬ ለአጠቃላይ የወር አስቤዛ ልቆርጥ ማንጠግቦሽ ዘንድ ብቅ አልኩ። በእንዲህ ያለው ቀን እኔና ማንጠግቦሽ እንኳን ሃያ ዓመት አብረን የኖርን ሃያ ደቂቃ የምንተዋወቅ አንመስልም። እንዲያውም አሁን የዋጋ ግሽበቱን እኛ እንደምንለው ለምደነው፣ መንግሥት እንደሚለው ከሆነ ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውሎ በረድ አልን እንጂ በአስቤዛ ወጪ ፍልስጤምና እስራኤል ሆነን ነው ቁጭ የምንለው። ታዲያ አሁንም “እንዴት ዋልሽ?” ብዬ ቤቴ ዘው ስል ለምን በዚያ ሰዓት እንደሄድኩባት ገብቷት አፍንጫዋን በመንፋት የመጀመርያውን ያለመግባባት ሮኬት ተኮሰች።

እንደ ወትሮው የአስቤዛ ገንዘብ ያሳንሰኛል ብላ ነው ብዬ ከጭቅጭቅ ለመዳን ጨመር አርጌ ብሰጣትም ፊቷ አልተፈታመም። “ምን ሆነሻል?” ማለት ኮስተር ብዬ። “ዶላር ጨምሯል የአስቤዛ ወጪም በእጥፍ መጨመር አለበት፤” አለችኛ  ሃያ ዓመት ሙሉ በሁለት ሰው ወርሃዊ የሆድ ወጪ ስትጨቃጨቅ የኖረች ሴትዮ። “እንዴት ዛሬ ትዝ አለሽ? ስንቴ አልጨመረም? እንደ አገር መሆን ነዋ…. ” ስላት መድከሜን በግልጽ እያስፎገርኩ እንደ ባህታዊ ተመስጣ ምንም ሳትናገር እንዳለችው እጥፍ ገንዘብ ወሰደች። ስለራሳችን ብቻ እያሰብን የኖርነው ዕድሜ ስታስታውሰኝ ደግሞ ጭራሽ አንጎሌን በጥብጣው አረፈችው። የመጪው ትውልድ ብሩህ መንገድና ተስፋ ዋናው መሠረቱ የዛሬ የአባቶቻቸው ትጋት መሆኑም ሲታወሰኝ፣ ወገቤ ቢደክምም ትውልድ ተሻጋሪ ሐሳብ ለመውለድ እንዳላረጀሁ ገባኝ። የባሻዬ ልጅ ግን፣ ‹‹ምን ታከተህ ብቻ በለኝ፡፡ ቅድሚያ የሚሰጣቸው የሚያነጋገሩን ነገሮች ስንት እያሉ ያልበላንን ማከክ። በእከክ ላይ እከክ፣ በወጪ ላይ ወጪ፣ በአስቤዛ ላይ አስቤዛ፣ በድንዛዜ ላይ ድንዛዜ አይሰለችም? ኧረ ይሰለቻል! ኧረ ይታክታል!›› ሲለኝ፣ እኔ ደግሞ እንረጋጋ እንጂ ብያለሁ፡፡ ቸር እንሰንብት እስኪ! መልካም ሰንበት!      

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት