Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሁለት ኢትዮጵያዊ ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆኑ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ታንዛኒያ 2,100 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በነደፈችው ፕሮጀክት የኢትዮጵያ ሁለት አገር በቀል ኩባንያዎች ተሳታፊ ሆኑ፡፡ በተካሄደው የአዋጭነት ጥናት ሦስት ቢሊዮን ዶላር ያወጣል በተባለው ፕሮጀክት ተሳታፊ የሚሆኑት አገር በቀል ድርጅቶች፣ መንግሥታዊው የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽንና በኤፈርት ሥር የሚገኘው ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት ባካሄደችው መጠነ ሰፊ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ግንባታዎች ያገኘችውን ልምድ ለመካፈል፣ የታንዛኒያ ፕሬዚዳንት ጆን ማግፋሊ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጥያቄ አቅርበው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬዚዳንቱን ጥያቄ በመቀበል የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ጉዳዩን እንዲያስተባብር ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡

በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ኮርፖሬሽን በፕሮጀክቱ ላይ በቀጥታ ተሳታፊ ሆኗል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ለጨረታ የሚሆን ዲዛይን ከማዘጋጀት ጀምሮ፣ ፕሮጀክቱ ለኮንትራክተር ሲሰጥ ተቆጣጣሪ ሆኖ ለመሥራት የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ነገደ አባተ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከታንዛኒያ ከመጡና ከኢትዮጵያውያን በድምሩ 13 ባለሙያዎች ያካተተ ቡድን ተቋቁሟል፡፡

‹‹የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ለአንድ ኮንትራክተር ተጠቃሎ የሚሰጥ ሲሆን፣ ሥራውን ኮርፖሬሽኑ ይቆጣጠራል ብለን እንጠብቃለን፡፡ ለጨረታ የሚሆነውን መሠረታዊ ዲዛይን በማጠናቀቅ ላይ ነን፡፡ በዚህ ሳምንት አጠናቀን እናስረክባለን፤›› ሲሉ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ታንዛኒያ ቀደም ብሎ የነበረውን የኢነርጂና የማዕድን ሚኒስቴር በድጋሚ እያዋቀረች ነው፡፡ በአዲሱ መዋቅር ኢነርጂ ለብቻው ማዕድንም ለብቻው ራሳቸውን ችለው ይዋቀራሉ፡፡

ሥራ አስፈጻሚው እንደገለጹት፣ እየተካሄደ ባለው የመዋቅር ለውጥ ምክንያት ኮርፖሬሽኑ ኮንትራት ባለመፈራረሙ ለሥራው የሚከፈለውን የገንዘብ መጠን አሁን መግለጽ አይቻልም፡፡ ሌላው አገር በቀል ድርጅት የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ኢንዶውመንት ፈንድ (ኤፈርት) ሥር የሚገኘው ሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው፡፡ ሱር ኮንስትራክሽን የታንዛኒያ መንግሥት ለኃይል ማመንጫ ግንባታው ያወጣውን የጨረታ ሰነድ በመግዛት በጨረታው ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡

የሱር ኮንስትራክሽን ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ የማነ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጨረታው የወጣው ኢንጂነሪንግ ፕሮኪዩርመንት ኮንትራት (ተርን ኪ) ነው፡፡ ‹‹እኛ ከሌላ ኮንትራክተር ጋር በመሆን ግንባታውን ለማካሄድ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ለዚህ ሥራ በተለይ በተከዜ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታና በጢስ ዓባይ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታ ተሳታፊ ሆነን ያገኘነው ልምድ ይጠቅመናል፤›› ሲሉ አቶ ታደሰ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ታንዛኒያ አሁን የምታመነጨውን 1,500 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት 10,000 ሜጋ ዋት የማድረስ ዕቅድ ነድፋለች፡፡ ይህ ፕሮጀክት የዚህ ግዙፍ ዕቅድ አካል ሲሆን፣ ግንባታው የሚካሄደው ወደ ህንድ ውቅያኖስ በሚፈሰው ሩፊጂ ወንዝ ላይ ነው፡፡

ይህንን ፕሮጀክት ለማሸነፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ50 በላይ የሚሆኑ ኩባንያዎች የጨረታ ሰነድ በመግዛት ጨረታው የሚከፈትበትን እ.ኤ.አ. ኖቬምበር 27 ቀን 2017 በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ፕሮጀክት በሦስት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ የሚፈልገው የታንዛኒያ መንግሥት፣ በዚህ ጨረታ የሚሳተፉ ኩባንያዎች በዓመት 500 ሚሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅሱ መሆን እንዳለባቸው ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡

ይህንን ፕሮጀክት የአካባቢ ተቆርቋሪዎች የግድቡ ግንባታ በታችኛው ተፋሰስ የሚገኙ የዱር እንስሳትንና መኖሪያቸውን አደጋ ላይ ይጥላል በማለት እየተቃወሙ ነው፡፡

መንግሥት አገር በቀል ኩባንያዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ፈለግ ተከትለው በሌሎች አገሮች እንዲሠሩ ይፈልጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች