Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናደኢሕዴን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመፍታት ችግሮች እንደነበሩበት ገለጸ

ደኢሕዴን የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች የመፍታት ችግሮች እንደነበሩበት ገለጸ

ቀን:

የኢሕአዴግ አባል ድርጅት የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣ ባለፈው ዓመት በክልሉ ውስጥ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን  በወቅቱ የመፍታት ችግሮች እንደነበሩበት አስታወቀ፡፡

የደኢሕዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ ዓርብ ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ልማት በሁሉም አካባቢዎች እንዲደርስና መልካም አስተዳደርን በወቅቱ ያለመፍታት ችግሮች ነበሩ፡፡

ደኢሕዴን ‹በአመለካከትና በተግባር ሰፋ ያለ ችግር ውስጥ የገቡና ተሃድሶን ሊሸከሙ ያልቻሉ› ያላቸው 673 በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ላይ ፖለቲካዊና አስተዳዳራዊ ዕርምጃ መውሰዱም ተገልጿል፡፡

‹‹በ2009 ዓ.ም. ሙስናና ብልሹ አሠራር ውስጥ የገቡ አመራሮች ዕርምጃ ተወስዶባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ እነዚህ ችግር የተገኙባቸውን አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁና ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ከማድረግ ባሻገር፣ ከ1,900 በላይ አመራሮች ላይ ደግሞ ማሸጋሸግ መደረጉን፣ አስረድተዋል፡፡ ‹‹በርካታ ወጣቶችንና ተሃድሶውን ተሸክመው ሊሄዱ የሚችሉ አዳዲስ አመራሮችን ደግሞ ወደ መዋቅራችን ጨምረናል፤›› ብለዋል፡፡ ከሳምንታት በፊት የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ተስፋዬ፣ የተሃድሶው ንቅናቄ እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር በትክክለኛ መንገድ እየሄደ እንደሆነ መገምገሙንም አስረድተዋል፡፡

እንደ አቶ ተስፋዬ ገለጻ ደኢሕዴን 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ካለፈው ነሐሴ 20 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች እያከበረ ነው፡፡ በክልል ደረጃ የበዓሉ ማጠቃለያ ጥቅምት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደሚሆን የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፣ ‹‹በሌሎች የአፍሪካና የአውሮፓ እንዲሁም የአሜሪካ አገሮች ክብረ በዓሉ ዓመቱን ሙሉ ይካሄዳል፤›› ብለዋል፡፡

የደኢሕዴን የምሥረታ በዓል ሲከበርም የፓናል ውይይቶች፣ የድጋፍ ሠልፎችና ስፖርታዊ ውድድሮችን እንደሚያካትት ጠቅሰዋል፡፡ እስካሁን ባለው የበዓሉ አከባበርም ከሰባት ሚሊዮን በላይ የድርጅቱ ደጋፊዎችና አባላት እንደተሳተፉ ገልጸዋል፡፡

የዚህ በዓል ዋነኛ ዓላማም ባለፉት 25 ዓመታት የተገኙ ስኬቶች የበለጠ እንዴት እንደሚጠናከሩና አጋጥመው የነበሩ ጉድለቶችና ተግዳሮቶች ደግሞ እንዴት መታረም እንዳለባቸው መላው የድርጅት አመራር፣ አባላቱና ደጋፊዎች ተወያይተው አቋም የሚይዙበትና አቅማቸውን የሚገነቡበት፣ ለቀጣይ ተግባርና ተልዕኮ የበለጠ መነሳሳት የሚፈጥሩበት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከኢሕአፓ ተገንጥለው የወጡ አባላት የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢሕዴን)ን በ1973 ዓ.ም. መመሥረታቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹በ1981 ዓ.ም. የደቡብ ኢትዮጵያ ልጆች በኢሕዴን ውስጥ ገብተው ደርግን ሲፋለሙ ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ከ1981 ዓ.ም. በኋላ ደግሞ ኢሕዴን ውስጥ የነበሩ የደቡብ ልጆች ደቡብን ሊወክል የሚችል ራሱን የቻለ የመጀመርያ አደረጃጀት መፍጠራቸውን፣ ስያሜውንም በ1983 ዓ.ም. የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች ማኅበር ብለው እንደሰየሙት ተወስቷል፡፡

የስምጥ ሸለቆ ታጋዮች ማኅበር የተደራጀው ደግሞ በትግራይ ክልል ታህታይ ቆራሮ ወረዳ ላይ ሹልምባቲ በሚባል ዋሻ ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የመጀመሪያው የደኢሕዴን ጥንስስ የጀመረውም ከዚህ እንደሆነ ጠቁመው፣ ‹‹ያም ስለሆነ ነው በትግራይ ክልል የሕዝብን አብሮነትና አንድነት የሚያጠናክር እንዲሁም የደሕዴንን መነሻ የሚያስታውስ፣ ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን የሚያጠናክር አንድ ማስታወሻ ትምህርት ቤት ተሠርቶ የተመረቀው፤›› ብለዋል፡፡

ከ1983 እስከ 1985 ዓ.ም. ድረስ በደቡብ ክልል 16 የተለያዩ ዞናዊ ድርጅቶች ተፈጥረው፣ በ1985 ዓ.ም. ወደ አንድ ግንባር በማምጣት ደኢሕዴን መመሥረቱን ጠቁመዋል፡፡

ዘንድሮ የሚከበረው 25ኛ ዓመት የደኢሕዴን ምሥረታም እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ለማስታወስና ለመዘከር፣ ብሎም ወደፊት ከዚህ የተሻለ እንዲሠራ ታልሞ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...