Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊለእምቦጭ አረም የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ

ለእምቦጭ አረም የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

ከአራት ዓመታት በላይ ላይ የተንሰራፋውና በአሁኑ ወቅት በሺሕ የሚቆጠር ሔክታር ስፋት የጣና ሐይቅን ክፍል የሸፈነው የእንቦጭ አረምን ለመከላከል፣ የፌዴራል መንግሥት እገዛ እስካሁን ድረስ አነስተኛ እንደሆነ ተገለጸ፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በክልል ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃም አረሙን ለማስወገድ ከባድ እንደሆነ ቢታወቅም የፌዴራሉ መንግሥት ድጋፍ ግን አነስተኛ ነው፡፡

‹‹የህዳሴ ግድቡ ከ375 ዓመታት በላይ እንዲቆይ ተደርጎ እየተገነባ ነው፡፡ የዓባይ ወንዝ ዋነኛ ምንጭ ጣና ሐይቅ እንደሆነ ቢታወቅም፣ የፌዴራሉ መንግሥት ከዚህ አንፃር የሰጠው ትከረት አነስተኛ መሆኑ ያሳዝናል፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት የሐሮማያ ሐይቅ በደለል ተሞልቶ እንደ ደረቀ የሚታወቅ ሲሆን፣ ጣና ሐይቅም ተመሳሳይ ችግሮች እንደተጋረጡበት በተደጋጋሚ ጊዜ በባለሙያዎች ሲነገር ተሰምቷል፡፡

የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ለሪፖርተር በስልክ እንደገለጹት፣ የክልሉ መንግሥት አቅሙን አሟጦ በመጠቀም አረሙን ለማስወገድ ሲንቀሳቀስ ቢታይም ከአረሙ ፈጥኖ የመራባትና አስቸጋሪ ባህሪ የተነሳ በቀላሉ ማስወገድ አልተቻለም፡፡ ጣና ሐይቅ ለባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ወይም ለክልሉ ሕዝብ ንብረት ብቻ እንዳልሆነ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎች፣ የፌዴራል መንግሥት ከሁሉም ሥራዎች ቅድሚያ በመስጠት ሊያስወግደውና የአገሪቱን ሕዝብ በአራቱም አቅጣጫ ሊያንቀሳቅሰው ይገባ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በዓለም ረጅሙ ወንዝ ዓባይ ከሰከላ ተነስቶ ጣና ሐይቅን በማቋረጥ በለስን፣ ዴዴሳን፣ ዳቡሰን፣ ድንድርንና በርካታ ጅረቶችን አቅፎ የሚፈሰው ወንዝ አንድነትንና መተባበርን የሚሰብክ እንደሆነ ቢያሳይም፣ በዚህ ረገድ የፌዴራል መንግሥት መላው የአገሪቱን ሕዝቦች በማስተባበርና ችግሩን በመቅረፍ ረገድ ውስንነቶች እንዳሉበት ጠቁመዋል፡፡

ወጣት ዘሪሁን በቀለ ተወልዶ ያደገው በባህር ዳር ከተማ መሆኑን ይናገራል፡፡ በጣና ሐይቅ ላይ ዋኝቶ ከማደጉም በላይ በአሁኑ ወቅት ከጣና ሐይቅ ዓሣ በማስገር ነው የሚተዳደረው፡፡ የእንቦጭ አረም በጣና ላይ ከተከሰተ ወዲህ የሐይቁ የውኃ መጠን እየቀነሰ መጥቷል ይላል፡፡ ይህን ችግር ለመፍታት ከክልሉ ሕዝብና መንግሥት ውጪ ሌላ የፌዴራል አካል በተግባር ሲንቀሳቀስ እንዳላየ ይናገራል፡፡

የእንቦጭን አረም ለመከላከል ከወራት በፊት በጎንደርና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲዎች  ማሽን ከመሥራት ጀምሮ ከውጭ አገር ጢንዚዛዎችን በማምጣትና በማባዛት ለመከላከል ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቶ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ሊሠራ የታቀደው አረሙን ለማጨድ የሚያግዝ ማሽን፣ እስካሁን ድረስ ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት እንዳልቻለ ታውቋል፡፡

ከውጭ ተገዝተው የመጡ ጢንዚዛዎችም እየተራቡ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልጽ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ ወደ ሐይቁ ተለቀው አረሙን እንዲበሉት አለመደረጉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን አረም ለመከላከል ከኦሮሚያ ክልል  የተውጣጡ ከ200 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ሐሙስ ጥቅምት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ባህር ዳር ተንቀሳቅሰዋል፡፡

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ እንደገለጹት፣ ‹‹ከዛሬ 121 ዓመታት በፊት መላው ኢትዮጵያውያን ወራሪውን የጣሊያን ጦር አሳፍሮ ለመመለስ ከየአቅጣጫው በአንድ መንፈስ ወደ ዓደዋ እንደተመሙት ሁሉ፣ ዛሬም የኦሮሚያ ወጣቶች የሰላሌን ሜዳ ገስግሰው፣ የዓባይን በረሃ አቋርጠው በደጀን በኩል ብቅ ሊሉ ነው፡፡ ጣናን ሊታደጉ፤›› ብለዋል፡፡ አረሙን ሊያስወግዱ የሚችሉ ጀልባዎች በክልሉ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችና ተመራማሪዎች እየተሠሩ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጣና ሐይቅ በመሄድ ችግሩ ያለበትን ሁኔታ ከማየት በተጨማሪ አረሙን ለመንቀል በተደረገው ዘመቻ መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጣና የአንድ ክልል ሀብት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት በመሆኑ፣ ገደብ የለሽ ርብርብ እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረባቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የዚህ ጥሪ አካል ተደርጎ የተወሰደውና አገራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ወደ ሥፍራው የተጓዙት የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች፣ ከተለያዩ አካላት ምሥጋና ቀርቦላቸዋል፡፡ በብዙ መቶ የሚቆጠር ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው ባህር ዳር የሄዱት የኦሮሚያ ወጣቶችም በክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ደማቅ አቀባበል እንደተደረገላቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጣና ሐይቅ በአሁኑ ወቅት የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ድጋፍ የሚሻ እንደሆነ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቢሰማም፣ እስካሁን ድረስ ይህ እየሆነ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው፡፡

ማክሰኞ መስከረም 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የህዳሴ ግድቡ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በ2010 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤቱ በኩል ሊሠሩ ስለታቀዱ ሥራዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በኢትዮጵያ ሆቴል ባደረገው ውይይት ላይም፣ ተሰብሳቢዎች በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን የእንቦጭ አረም ለመከላከል የፌዴራል መንግሥት የሰጠው ትኩረት አነስተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ግድቡ ረዥም ዕድሜ ሊያገለግል የሚችለው ጣናና መሰል ሐይቆችን፣ እንዲሁም ወንዞችን መጠበቅ ሲቻል ብቻ እንደሆነም አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...