ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ድረስ የተዘረጋው የባቡር ሐዲድ ግንባታ ቀደም ሲል በሚታቀድበት ወቅት ወደ ነዳጅ መጫኛና ማራገፊያ ዴፖዎች፣ ወደ ዶራሌና ሆራይዘን ወደቦች፣ እንዲሁም ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ የሚወስድ የሐዲድ ዝርጋታ ባለመካተቱ መንግሥትን ለአላስፈላጊ ወጪ መዳረጉ ተጠቆመ፡፡
ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ድረስ የተዘረጋው የባቡር ሐዲድ በአጠቃላይ 758 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡ ከአዲስ አበባ (ሰበታ) ጂቡቲ ድንበር 658 ኪሎ ሜትር፣ ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ ጂቡቲ 100 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡
የባቡር ሐዲድ ግንባታው በአጠቃላይ አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጎ የተጠናቀቀ ቢሆንም፣ መስመሩ ውጤታማ የሚሆንባቸው አራት ተያያዥ ፕሮጀክቶች ቀደም ብለው ባለመታሰባቸው አገሪቱን ለአላስፈላጊ ወጪ በመዳረግ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡
የመጀመርያው ፕሮጀክት የባቡር ሐዲዱ ሞጆ ደረቅ ወደብ እንዲገባ አለመደረጉ፣ ሁለተኛው የባቡር ሐዲዱ አዋሽ የሚገኘው የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዲፖ ውስጥ እንዲገባ አለመደረጉ፣ ሦስተኛውና አራተኛው ደግሞ መስመሩ ጂቡቲ ከደረሰ በኋላ ወደ ዶራሌ ወደብና ወደ ሆራይዘን ተርሚናል የሚወስደው መስመር አለመታሰቡ ናቸው፡፡
እነዚህ አራት ወሳኝ ፕሮጀክቶች እጅግ ከዘገየ በኋላ አስፈላጊነታቸው በመታመኑ፣ ፕሮጀክቱ የጊዜና የገንዘብ ጉዳት ማድረሱ ተመልክቷል፡፡ በዚህ መሠረት መንግሥት የባቡር ሐዲዱ ሞጆ ደረቅ ወደብ ውስጥ ማለፍ ሲገባው ባለማለፉ ብቻ ተጨማሪ 27 ሚሊዮን ዶላር አውጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወደ ሞጆ ደረቅ ወደብ የሚወስደው የሐዲድ መስመር ግንባታ ተጠናቋል፡፡ በአሁኑ ወቀት ደግሞ ወደ አዋሽ ነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ የሚወስደውን መስመር ለመገንባት የሚያስችል ዲዛይን ሥራ እንዲሁ ተጠናቋል፡፡ ወደ ነዳጅ ማጠራቀሚያው የሚወስደው የሐዲድ መስመር 1.7 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የባቡር ሐዲዱ በነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ ውስጥ እንዲያልፍ አለመደረጉ ጉዳት አምጥቷል፡፡
ነዳጅ ድርጅቱ 36 ሚሊዮን ሊትር የመያዝ አቅም ያለው የነዳጅ ማጠራቀሚያ ዴፖ በቀድሞ አዋሽ መጠባበቂያ ነዳጅ ማከማቻ ቅጥር ግቢ ውስጥ ገንብቷል፡፡ ነገር ግን ሐዲዱ በግቢው ውስጥ ባለማለፉ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አዲስ ፕሮጀክት መቅረፁን አቶ ታደሰ አስረድተዋል፡፡
የእዚህ ፕሮጀክት ወጪ ባይታወቅም ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋናውን መስመር ለገነባው የቻይናው ሲአርኢሲ ኩባንያ ለመስጠት እየተደራደረ መሆኑ ታውቋል፡፡
ሦስተኛው ፕሮጀክት ከጂቡቲ እስከ ዶራሌ ወደብ ያለው 800 ሜትር የባቡር ሐዲድ ጉዳይ ነው፡፡ ይኼ ፕሮጀክት በጂቡቲ በኩል ያለ ቢሆንም፣ ዋነኛ ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ገቢና ወጪ ዕቃዎች እንደመሆኑ ግንባታው ቀደም ብሎ አለመታሰቡ ጉዳት እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
ይኼንን ፕሮጀክት የቻይና ሲሲኢሲሲ እያከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡ አቶ ታደሰ እንደሚገልጹት፣ በመርከብ የሚደገፈው ነዳጅ የሚጠራቀመው ሆራይዘን ተርሚናል ውስጥ ቢሆንም፣ ወደ ተርሚናል የሚወስደው የሐዲድ መስመር አልተገነባም፡፡ በአሁኑ ወቅት 500 ሜትር የሚሆነውን ተጨማሪ መስመር ለመገንባት የሚያስችል ዲዛይን እየተሠራ መሆኑን አቶ ታደሰ ጨምረው ገልጸዋል፡፡ በቅርብ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ የባቡር መስመሩን ከወደብ ጋር ለማገናኘት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
‹‹በጊዜያዊነት የዕቃ መጫኛ ጣቢያ ዶራሌ ወደብ አቅራቢያ እየተዘጋጀ ነው፤›› ሲሉ አቶ ሮባ ገልጸዋል፡፡
ከአዲስ አበባ እስከ ጂቡቲ ወደብ ድረስ ያለው የባቡር መስመር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት የዛሬ ዓመት መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመርቋል፡፡ ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ ጂቡቲ ሆልሆል ባቡር ጣቢያ ያለው መስመር ደግሞ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና የጂቡቲ ፕሬዚዳንት እስማኤል ኦማር ጊሌ በተገኙበት ጥር 2 ቀን 2009 ዓ.ም. ተመርቋል፡፡
በባቡር የሚደረገው ጉዞ ለአንድ ዓመት ያህል በሙከራ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ አቶ ደረጀ እንዳሉት ሙከራው ውጤታማ መሆኑ ሲረጋገጥ መደበኛ ኦፕሬሽኑን እንደሚጀመር ገልጸዋል፡፡ መደበኛ ሥራው የሚጀመርበት ቀን ግን አለመቆረጡን ጨምረው ተናግረዋል፡፡