በኦሮሚያ ክልል ተደርገው በነበሩ የተቃውሞ ሠልፎች የስምንት ሰዎች ሕይወት ሲጠፋ ከ30 በላይ ሰዎች ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ፣ መረጋጋት ተፈጥሯል፡፡
ረቡዕ ጥቅምት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ከአምቦ ጀምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፍቶ የነበረው የተቃውሞ ሠልፍ መነሻ ምክንያቱ ሰንቀሌ የሚገኘው የአምቦ የማዕድን ውኃ ወደ ትግራይ ክልል ሊሄድ ነው በሚል እንደሆነ መነገሩ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ የአምቦ የማዕድን ውኃ ከፍተኛ ኃላፊ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ፋብሪካው ተዘግቷል ተብሎ የተናፈሰውን ወሬ ሐሰት ነው፡፡ ‹‹አንዳንድ የፋብሪካው ሠራተኞች አሉባልታውን ለሌላ ነገር እያዋሉት ነው፡፡ ፋብሪካው ሥራ አላቆመም፡፡ ፋብሪካውን ወደ ሌላ ቦታ የማዛወር ዕቅድም ሆነ ፍላጎት የለም፤›› ብለዋል፡፡
በወሊሶ፣ በሻሸመኔ፣ በአምቦ፣ በቦኬና በዶዶላ አካባቢዎች በነበሩት የተቃውሞ ሠልፎች ‘ወያኔ ይውረድ፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ይፈቱ፣ ኦሮሚያ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ማግኘት አለባት፣’ ወዘተ የሚሉ መፈክሮች ሲሰሙ እንደነበር ታውቋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል በሻሸመኔ፣ በወሊሶ፣ በአምቦ፣ በዶዶላና በቦኬ (ምዕራብ ሐረርጌ) አካባቢዎች ተቀስቅሶ በነበረው የተቃውሞ ሠልፍ የስምንት ሰዎችን ሕይወት ከመጥፋቱ በላይ፣ ከ30 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ ታውቋል፡፡
በአገሪቱ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲነሳ የኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊና የአገር መከላከያ ሚኒስትሩ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ሰላም ሰፍኗል፡፡ በጥቂት አካባቢዎች የሚቀሩ ትንንሽ ጉዳዮች ቢኖሩም ይኼን በመደበኛው የሕግ አግባብ መፍታት ይቻላል፤›› የሚል ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ተቀባይነት በማግኘቱ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተነሳ ከጥቂት ወራት በኋላ በኦሮሚያ ክልል የተቃውሞ ሠልፎች ተካሂደው የሰው ሕይወት ጠፍቷል፡፡
የኢሬቻ በዓል ሲከበር የክልሎች ሆነ የፌዴራል የፀጥታ አካላት በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ እንዳይመጡና የፀጥታ ችግር እንዳይፈጠር የክልሉ አመራሮች በማድረጋቸው ሲሞካሹ ሰንብተዋል፡፡ በዓሉ ሁለት ሳምንታት ሳያስቆጥር ከሁለት ዓመታት በፊት በክልሉ እንደነበረው የተቃውሞ ሠልፍ መታየቱ፣ አሁንም ያልተፈቱ ችግሮች እንዳሉ ማሳያ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይነገራሉ፡፡
ከተቃውሞ ሠልፉ በኋላ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መግለጫ የሰጡ ሲሆን፣ ክልሉ በተሃድሶ አመራሩ አማካይነት የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ከፍተኛ ሥራ በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በአሁኑ ጊዜም የክልሉ መንግሥት በጀመረው ሥራ የሕዝቡን ጥቅም ከማይፈልጉ ኃይሎች ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ እያደረገ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹አሁን የተጀመረው ትግልና ሥራ የኦሮሞን ሕዝብ ያስደሰተ ቢሆንም፣ የሕዝቡን ሰላም የማይወዱ አፍራሽ ኃይሎች የሕዝቡን ጥቅም ለማስጠበቅ የተጀመሩ ሥራዎችን ለማክሸፍ ከመንቀሳቀስ አልቦዘኑም፤›› ብለዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በሰጡት መግለጫ፣ በአንዳንድ የክልሉ ከተሞች የወጣቶችን ስሜት በመቀስቀስ የተካሄዱ ሠልፎች የክልሉን ሕዝብ ፍላጎት የማይገልጹ ናቸው ብለዋል፡፡ ኅብረተሰቡም ከእንዲህ ዓይነት ሠልፎች ራሱን እንዲጠብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ተጀምሮ የነበረው የተቃውሞ ሠልፍ እስከ ሐሙስ ቢቀጥልም፣ ባለፉት ሁለት ቀናት እንደተረጋጋ ለማወቅ ተችሏል፡፡