- ዕጣ የደረሳቸው ግንባታው ለዘገየበት ወለድ እንዲከፍሉ ተደርጓል
በሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም. መጀመርያ ሳምንት በዕጣ ከተላለፉ የ40/60 የጋራ መኖርያ ቤቶች፣ በዕጣ ከደረሳቸው የተወሰኑት የሕንፃው ግንባታ ሙሉ በሙሉ እንደተጠናቀቀ ተደርጎ ሙሉ ክፍያ እንዲፈጽሙ የተደረጉት ትክክል አለመሆኑን፣ ሕንፃው ብዙ መጠናቀቅ የሚገባቸው ነገሮች እንደቀሩት ተናገሩ፡፡ ንግድ ባንክ እንዲያስረክቡት ሲጠይቁት ‹‹አልተጠናቀቀም›› መባላቸውንም ገልጸዋል፡፡
የዕጣው ዕድለኞች ለሪፖርተር እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕጣውን ካወጣ ከአንድ ወር በኋላ ዕጣ ለደረሳቸው ተመዝጋቢዎች ስልክ በመደወል ክፍያ እንዲያጠናቅቁና ቤታቸውን እንዲረከቡ ነግሯቸዋል፡፡ ምንም እንኳን የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ መጨመርን ምክንያት በማድረግ፣ ሲመዘገቡ ትከፍላላችሁ ከተባሉትና ውል ከፈጸሙበት ዋጋ ከእጥፍ በላይ ዋጋ እንደተጨመረባቸው ቢያውቁም፣ ለመክፈል አለማንገራገራቸውን ዕድለኞቹ ተናግረዋል፡፡
በተሰጣቸው የመክፈያ አጭር ቀናት ውስጥ ለባለሦስት መኝታ ቤት 963,000 ብር ሙሉ ክፍያ ከፈጸሙ በኋላ ለማስረከብ እንደሚጠሩ የተነገራቸው ቢሆንም፣ ዝም እንደተባሉ አክለዋል፡፡ ጊዜው ሲረዝምባቸው ራሳቸው ተመልሰው በመሄድ እንዲያስረክቧቸው ሲጠይቋቸው፣ ዕጣ የወጣላቸው የተወሰኑ ዕድለኞች የደረሳቸው የሕንፃ ብሎክ አሳንሰር ያልገባለት መሆኑንና እንዲጠብቁ እንደተነገራቸው ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ ቤተልሔም በቀለ ባለሦስት መኝታ ቤት ዕጣ ከደረሳቸው መካከል አንዷ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ባለዕጣዎች እንደሚናገሩት እሳቸውም የደረሳቸው ብሎክ ብዙ ግንባታ ይቀረዋል፡፡ የንፅህና ዕቃዎቹ ያልተሟሉና የተሰባበሩ፣ የውስጥ በሮች ያልተገጠሙለት፣ ግድግዳዎቹ የተሰነጣጠቁ፣ የውኃ ማስተላለፊያ መስመሮች ያልተገናኙ፣ ለምን እንደ ተተው ያልተገለጹ ቀዳዳዎችና ሌሎችም ጉድለቶች እንዳሉበት አስረድተዋል፡፡
ዋጋው ከመናሩ በተጨማሪ ግንባታው በሁለት ዓመት ውስጥ ተጠናቆ ለተመዝጋቢዎች እንደሚተላለፍ የተገለጸ ቢሆንም፣ በተባለው ቀን ባለመድረሱ 123,000 ብር ወለድ እንዲከፍሉ መደረጋቸውን ወ/ሮ ቤተልሔም ይናገራሉ፡፡ ‹‹ወለድ መክፈል ያለበት መቶ በመቶ ቅድሚያ የፈጸመውና በተባለበት ጊዜ ያልተረከበው ነው? ወይስ ግንባታውን ያዘገየው?›› በማለት የሚጠይቁት ደግሞ አቶ ሳሙኤል ፍሰሐና ወ/ሪት ፀሐይ ሃድጉ ሲሆኑ፣ ይህንን ለመንግሥትና ለሕዝብ እንደሚተውት ጠቁመው፣ ባልተጠናቀቀ ግንባታ ተጨማሪ ሙሉ ክፍያና ወለድ እንዲከፍሉ መደረጋቸው አሳዛኝ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከቤት ኪራይ ስቃይ ለመላቀቅ ያላቸውን ገንዘብ አሟጠው የከፈሉ በመሆናቸው፣ የሚመለከተው አካል በአፋጣኝ የሚጠናቀቅበትን መንገድ ፈጥሮ እንዲያስረክባቸው ጠይቀዋል፡፡ ገንዘቡን ለመቀበል በሙሉ ፈገግታ የተቀበላቸው ንግድ ባንክ፣ በከፈሉት ልክ የፀዳ ቤት ማስረከብ ሲገባው ባለማድረጉ ቅሬታቸውን ሊያቀርቡ ሲሄዱ የሚያናግራቸው መጥፋቱን ተናግረዋል፡፡
ግንባታውን ያካሄደው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቤቶቹን ሲያስተላልፍ፣ አንዳንድ ጉድለቶች ቢገኙ ለማስተካከል መፈራረሙንና ነዋሪዎች በሚያቀርቡት ማንኛውም ቅሬታ ላይ አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጥ የገለጸ ቢሆንም፣ ወደ ተግባር ሲገባ ግን ምንም ዓይነት ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኃላፊ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ በልሁ ታከለ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ባንኩ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ ሲረከብ የተጓደሉ ሥራዎችን እንደሚያስተካክል ቃል ገብቷል፡፡ የሚጠበቀውም እንዲያስተካክል ነበር፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ ደብዳቤ የተጻፈለት ቢሆንም ምላሽ አለመስጠቱን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ የተጓደሉ ነገሮች መኖራቸው እርግጥ ቢሆንም፣ ቀለም መቀባትና የውስጥ በሮችን መግጠም ኢንተርፕራይዙን አይመለከተውም፤›› ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ዕድለኛው በምርጫው የሚያደርጋቸው በመሆኑ እንደሆነና በውሉም ውስጥ አለመካተታቸውን አስረድተዋል፡፡ ኢንተርፕራይዙ በገባው ቃል መሠረት የማይፈጽም ከሆነ በቀጣይ የሚታይ መሆኑን አክለዋል፡፡
ግንባታውን ለማጠናቀቅ ቃል መግባቱንና መፈራረሙ የተገለጸው የአዲስ አበባ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን የሥራ ሒደት መሪ አቶ ዮሐንስ ዓባይነህ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ባንኩ ከተረከባቸው ሕንፃዎች መካከል ጥቃቅን ሥራዎች የቀራቸውና ኢንተርፕራይዙ እንደሚያስተካክል ቃል የገባው ለሁለት ሕንፃዎች ብቻ ነው፡፡ እነሱንም እየሠራና እያስተካከለ ነው፡፡ ሊፍት ያልተገጠመለት ሕንፃ ግን የለም፡፡ ይህ ሁሉ ችግር የመጣው ከተቋራጩ ነው ብለዋል፡፡ ሕንፃዎቹን ለባንኩ ገና ስላላስረከቡ፣ ለማስረከብ እየሠሩ ስለሆነ በቅርብ ቀን አጠናቀው እንደሚያስረክቡ አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡ ባንኩ ስለጻፈው ደብዳቤ ግን የሚያውቁት እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡