Sunday, April 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ሦስት ሆቴሎችን እየገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በአምስት ዓመት ሆቴሎችን ብዛት 20 ለማድረስ አቅዷል

ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በአርባ ምንጭ፣ አዲስ አበባና በአዳማ ሦስት ዘመናዊ ሆቴሎችን በመገንባት ላይ ነው፡፡

ከስምንት ዓመት በፊት ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል የኢንቨስትመንት ኩባንያው የሐዋሳ ኃይሌ ሪዞርትን በመገንባት ወደ ሆቴልና ቱሪዝም መስክ የተቀላቀለ ሲሆን፣ በዝዋይና በሻሸመኔ ሁለት ሪዞርት ሆቴሎችን ከፍቷል፡፡ በሱሉልታ ከተማ ያያ ቪሌጅን ገንብቶ አገልግሎት ላይ ማዋሉ ይታወሳል፡፡

ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል በአሁኑ ወቅት በቱሪስት መስህብነት በምትታወቀው አርባ ምንጭ ከተማ በ250 ሚሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ ሪዞርት ግንባታ ለማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የሪዞርቱ ግንባታ የሚካሄደው የጫሞና የዓባያ ሐይቆች በሚገናኙበት በተለምዶ ‹የእግዜር ድልድይ› ተብሎ በሚጠራው አካባቢ 41,313 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ነው፡፡ ይዞታውን ኩባንያው ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር በሊዝ እንደተረከበው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኃይሌ ሪዞርት አርባ ምንጭ የተለያዩ ደረጃዎች ያሏቸው 108 የእንግዶች ማረፊያ ክፍሎች፣ የመዋኛ ገንዳ፣ ስፓና ጂምናዚየም፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ አነስተኛ የጎልፍ መጫወቻ ሜዳና የፈረስ ግልቢያ ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራ አሟልቶ የያዘ ነው፡፡ ኃይሌ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ሪዞርቱ የሚገነባበት ሥፍራ የሰዎችን ቀልብ የሚማርክ ድንቅ የተፈጥሮ ውብት ያለው ነው፡፡ የሆቴሉ ግንባታ መስከረም 2009 ዓ.ም. ተጀምሮ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የግንባታው 85 በመቶ ሥራው መጠናቀቁን የገለጸው ኃይሌ፣ በአሁኑ ወቅት የማጠናቀቂያ ሥራዎች በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ የሪዞርቱ ግንባታ በመጪው ታኅሳስ ወር ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

‹‹እዚህ የደረስነው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ሥራውን በጣም አጣድፈነዋል፡፡ ሁሌም ስለቻይና ኩባንያዎች የሥራ ፍጥነት እናወራለን፡፡ ይኼን ያደረግነው እኛም ኢትዮጵያውያን በፍጥነት መሥራት እንደምንችል ለማሳየት ነው፤›› ብሏል ኃይሌ፡፡

የኃይሌ ሪዞርት አርባ ምንጭን ዲዛይን ያደረገው ጌሬታ ኮንሰልት የተባለ አገር በቀል አማካሪ ድርጅት ሲሆን፣ የግንባታ ሥራውን ቁጥጥር የሚያካሄደው ይኼው ኩባንያ ነው፡፡ የግንባታ ሥራውን የሚያካሄደው ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ኩባንያ ነው፡፡

የአርባ ምንጭ ከተማ በስምጥ ሸለቆ ሐይቆች፣ በአዞ እርባታና በቅርብ ርቀት በሚገኘው ነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ ትታወቃለች፡፡ ኃይሌ የሐዋሳን ሪዞርት ሲገነባ ‹‹ሰዎች ገንዘብህን ሜዳ ላይ ለምን ትጥላለህ?›› ብለውት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ‹‹ዛሬ ሐዋሳን ብትመለከት ኤርፖርት ተገንብቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በየዕለቱ ይበራል፡፡ ግዙፍ የሆነ የኢንዱስትሪ ፓርክ ተገንብቷል፡፡ አርባ ምንጭ ትልቅ ከተማ ነው፡፡ ነገር ግን ከሁለት ሦስት ዓመት በኋላ እንዴት እንደምትለወጥ መገመት ይቻላል፤›› ብሏል፡፡

ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል በሆቴል መስክ ብቻ ለ700 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የገለጸው ኃይሌ፣ ለአገሪቱ የቱሪዝም ዕድገት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

ኩባንያው በአዲስ አበባና መገናኛ አቅራቢያ ኮረብታማ ሆቴል ይባል በነበረው ሥፍራ በ10,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ አዲስ ሆቴል ግንባታ ጀምሯል፡፡ ሆቴሉ ባለ ስምንት ፎቅ ሕንፃ የሚኖረው ሲሆን፣ 120 የእንግዶች ማሪፊያ ክፍሎች፣ ስፓ፣ ጂምናዚየምና መዋኛ ይኖረዋል፡፡

ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል ከአንድ ወር በፊት በአዳማ የሰባተኛውን ሆቴል ግንባታ ጀምሯል፡፡ የአዳማው ሪዞርት 110 የመኝታ ክፍሎች፣ ስፓ፣ ጂምናዚየም፣ የስብሰባ አራዳሽና የመዋኛ ገንዳ ይኖረዋል፡፡ ሪዞርቱ የሚገነባው በአዳማ ከተማ ከአዲስ አበባ መግቢያ የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት አቅራቢያ ነው፡፡

ኃይሌ የሆቴሎቹን ብዛት በመጪው አምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ 20 ለማድረስ ማቀዱን ገልጿል፡፡ ህልሙን ዕውን ለማድረግ በርካታ ፈተናዎች እንደገጠሙት ጠቁሟል፡፡ ከዚህም ውስጥ ትልቁ ማነቆ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንደሆነ ይናገራል፡፡

‹‹የሆቴል ግንባታ ዕቃዎች ሁሉም ማለት ይቻላል ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ ለመሣሪያዎች መግዣ የሚሆን ዶላር ለማግኘት እንቸገራለን፡፡ ከአገር ውስጥ ለመግዛት እኛ የምንፈልገው ጥራት ደረጃ የሚያሟሉ ዕቃዎች ማግኘት ፈታኝ ነው፡፡ አንዳንድ ዕቃዎች ስናገኝ ደግሞ ዋጋቸው የማይቀመስ ይሆንብናል፤›› ያለው ኃይሌ፣ ኩባንያው ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ በመጀመሩ ችግሩን እንደሚቀርፍ ያለውን ዕምነት ገልጿል፡፡

የሆቴል ሥራ ከባድ መሆኑን ሲገልጽ፣ ‹‹የምትሰጠው አገልግሎት ነው፡፡ የደንበኞችን ፍላጎት ሁልጊዜም ማርካት ከባድ ነው፡፡ ሥራው በየቀኑ ያንተን ክትትል ይጠይቃል፡፡ ዞር ካልክ ሥራው ይበላሻል፡፡ እንደ ሌላው ዓለም ተሞክሮ ለንደንና ኒውዮርክ ሆነህ መምራት እኛ አገር አይሠራም፤›› ብሏል፡፡

በየቢሮ ያለው የተንዛዛ ቢሮክራሲ ሌላው ትልቁ ፈተና እንደሆነ ገልጿል፡፡ ‹‹አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ብዙ ቀናት ተመላልሰህ ደጅ ጠንተህ ነው፡፡ ከላይ ያለው ቢወስንልህ ከታች ያለው ይይዝብሃል፡፡ ቅንነት ያስፈልጋል፤›› ያለው ኃይሌ፣ የንግድ ሥራ ፍጥነት የሚጠይቅ በመሆኑ በየመሥሪያ ቤቱ ባለው ረዥም ቢሮክራሲ የሚባክነው ጊዜ ኢንቨስትመንት ላይ ትልቅ ሳንካ እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግሯል፡፡

‹‹መንግሥት የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ይሰጣል፡፡ ነገር ግን የታክስ ዕፎይታ ጊዜ መስጠት በቂ አይደለም፡፡ ባለሀብቶችን ተብትቦ የያዘውን ቢሮክራሲ እንዴት ላሳጥረው ብሎ መንግሥት በእዚህ ላይ መሥራት አለበት፡፡ ኢንቨስትመንት የሚያድገው ባለሀብቱ የተቀላጠፈ አሠራር ሲመቻችለት ነው፤›› ብሏል፡፡

ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሸናል የኢንቨስትመንት ሥራውን የጀመረው በሪል ስቴት ዘርፍ ነው፡፡ በትምህርት፣ በግብርና፣ እንዲሁም ወርቅ ፍለጋ ዘርፍም ተሰማርቷል፡፡

በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የቡና እርሻ ልማት በማካሄድ ላይ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ለመጀመርያ ጊዜ ኦርጋኒክ ቡና ኤክስፖርት በማድረግ ከሙከራ ምርቱ 250,000 ዶላር ያህል አስገብቷል፡፡ በ2010 ዓ.ም. የቡና ኤክስፖርቱን ገቢውን በአምስት እጥፍ ለማሳደግ አቅዷል፡፡

ኩባንያው በደን ሀብቱ በሚታወቀው ሸካ ዞን ኦርጋኒክ የሆነ የጫካ ማር በማምረት ለአገር ውስጥና ውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

በትምህርቱ ዘርፍ ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል በባህር ዳርና በትውልድ ከተማው አሰላ ትምህርት ቤቶች በመክፈት በአሁኑ ወቅት 3,500 ተማሪዎች በማስተማር ላይ ነው፡፡

ማራቶን ሞተርስ የተባለው ኩባንያው የሀይውንዳይ ኩባንያ ብቸኛ ወኪል በመሆን የሀይውንዳይ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች በማስመጣት ለገበያ ያቀርባል፡፡ በቀጣዩ የሀይውንዳይ መኪኖች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ለመገንባት በመሥራት ላይ እንደሆነ ኃይሌ ገልጿል፡፡

ኃይሌና ዓለም ኢንተርናሽናል የኢንቨስትመንት ቡድን እስካሁን ለ2,100 ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን የገለጸው ኃይሌ፣ በቀጣይ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በመቅረፅ ላይ እንሆነ ተናግሯል፡፡

‹‹ለዚህ ሁሉ ያነሳሳኝ ቅናት ነው፡፡ በየሰው አገር ስሄድ ባየሁት ነገር በመቆጨት አገሬ ላይ የበኩሌን ለማድረግ ካለኝ ምኞት ነው የምሠራው፡፡ ገንዘብ ለእኔ ሁለተኛ ነገር ነው፡፡ ለገንዘብ የሚገርመኝ ሰው አይደለሁም፡፡ በአንድ ሰከንድ ምክንያት አንድ ሚሊዮን ዶላር ያጣሁ ሰው ነኝ፡፡ በሌላ አጋጣሚ በሁለት ሰከንድ ምክንያት የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሽልማት አሸንፊያለሁ፤›› ያለው ኃይሌ፣ አገር ለመለወጥ ተባብሮ በቅንነት መሥራት ወሳኝ እንደሆነ ገልጿል፡፡

‹‹ኃይሌ ያለው አንድ አገር ነው፡፡ አሜሪካ ሄጄ ብኖር ስደተኛ ነኝ፡፡ በአገሬ ላይ ሠርቼ ኢንቨስት አድርጌ ለእህትና ለወንድሞቼ የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሌ ያስደስተኛል፡፡ መቶ ሰው አሜሪካ ሊሄድ ይችላል፡፡ 100 ሚሊዮን ሕዝብ ግን ሊሄድ ስለማይችል ትኩረታችን አገራችን ላይ ብናደርግ መልካም ነው፤›› ብሏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች