Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየብሔር ብሔረሰቦችን ተዋጽኦ በፌዴራል ተቋማት ለማረጋገጥ ትኩረት የሰጠ የሠራተኞች አዋጅ ቀረበ

የብሔር ብሔረሰቦችን ተዋጽኦ በፌዴራል ተቋማት ለማረጋገጥ ትኩረት የሰጠ የሠራተኞች አዋጅ ቀረበ

ቀን:

  • በመንግሥት ውሳኔ ሠራተኞች ከክልል ተዘዋውረው እንዲደለደሉ ይደረጋል
  • ተቀጣሪዎች ለሕገ መንግሥቱ ታማኝነታቸውን በቃለ መሃላ እንዲያረጋግጡ ይጠየቃሉ

የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦችን ተዋጽኦ በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ለማረጋገጥ ዓብይ ትኩረት የሰጠ የፌዴራል የመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡

ረቂቅ አዋጁ በሥራ ላይ የሚገኘውን የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 515/99 የሚተካ ነው፡፡ የረቂቅ አዋጁ መግቢያ የአዋጁን አስፈላጊነት ሲገልጽ አዋጁ የተረቀቀው፣ ‹‹የምልመላና መረጣ ሥርዓትን በመሠረታዊነት በመለወጥና በአገር አቀፍ ደረጃ የሙያና የሥራ ብቃት ማረጋገጫ ሥርዓት በመዘርጋት፣ እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኛው በዚህ ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፍ በማድረግ ብዝኃነቱን ያረጋገጠና አገሪቱ እያስመዘገበች ያለችውን ዕድገት ለማስቀጠል የሚያስችል ፐብሊክ ሰርቪስ ለመገንባት በማስፈለጉ፤›› መሆኑን ይገልጻል፡፡

በዚሁ መሠረት የረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ፣ ‹‹በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚፈጸም የሠራተኛ ሥምሪት የብሔር ብሔረሰቦችን ሚዛናዊ ተዋጽኦ ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ መሆን አለበት፤›› በማለት ያስቀምጣል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ ሁለት ላይ ደግሞ፣ ‹‹በመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ አነስተኛ ብሔራዊ ተዋጽኦ ያላቸው ብሔር ብሔረሰቦች በቅጥር፣ በደረጃ ዕድገት፣ በዝውውር፣ በድልድል፣ በትምህርትና ሥልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ የድጋፍ ዕርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው፤›› ይላል፡፡

ይህንን ዕውን ለማድረግ የተቀመጠው መሣሪያ በድልድል ወይም በዝውውር ሠራተኞችን ከክልል መሥሪያ ቤቶች ወደ ፌዴራል ተቋማት ማምጣት መሆኑን የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያና የረቂቁ የተለያዩ አንቀጾች ያመለክታሉ፡፡

ከሌላ መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ የመንግሥት መሥሪያ ቤት የሠራተኛ ድልድል ወይም ምደባ የማድረግ ኃላፊነት የሚኒስቴሩ ሆኖ፣ መሥሪያ ቤቱ ሲዘጋ ወይም ትርፍ የሰው ኃይል ሲኖረው ከሚደረገው ዝውውር በተጨማሪ በመንግሥት (በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት) ሲታዘዝም ዝውውሩ ሊከናወን እንደሚችል በረቂቁ ተስተካክሏል፡፡

ይህም ማለት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ ከአንድ መሥሪያ ቤት ወደ ሌላ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በድንገት ወይም ያለ ተቋሙ ፍላጎት የሚደለደሉበት አሠራር ይፈጠራል ማለት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ አንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ለሥራው አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘውና ላኪና ተቀባይ መሥሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም ሠራተኛው ሲስማሙ አንድን የመንግሥት ሠራተኛ እኩል በሆነ ደረጃና ደመወዝ ሚኒስቴሩን በማሳወቅ አዛውሮ ማሠራት እንደሚቻልም በረቂቅ አንቀጽ 28(1) ላይ ተቀምጧል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ደግሞ፣ ‹‹የሚመለከተው የመንግሥት ሠራተኛ፣ የክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤትና የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሲስማሙ እንዲሁም ከክልሉ ወደ ፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት እኩል በሆነ ደረጃና ደመወዝ አዛውሮ ማሠራት ይቻላል፤›› ይላል፡፡

በሌላ በኩል ልዩ ሙያና ዕውቀት ያላቸውን ሠራተኞች የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በጋራ መጠቀም የሚችሉበት አሠራርም በረቂቅ አዋጁ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

በረቂቁ አንቀጽ 23 ላይ እንደተቀመጠው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአንድ የመንግሥት ሠራተኛ ልዩ ዕውቀትና ሙያዊ አቅም ለሥራቸው እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት በጋራ ሊቀጥሩት ይችላሉ ይላል፡፡ የቅጥሩ ሁኔታ፣ ቅጥሩ የሚቆይበት ጊዜ፣ የደመወዝ አከፋፈልና ሌሎች የሥራ ሁኔታዎች በመመርያ እንደሚወሰኑ ይገልጻል፡፡

የመንግሥት ሠራተኛ ሆኖ ለመቀጠር ከ18 ዓመት ዕድሜ በላይ መሆን የሚጠይቅ ሲሆን ወንጀል የሠሩ ቅጣቱ ከተፈጸመ፣ በይርጋ ከታገደ፣ ወይም በይቅርታ ከተሰረዘ በኋላ ቢያንስ አምስት ዓመት ካላለፈው በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መቀጠር እንደማይችሉ ይደነግጋል፡፡

በተመሳሳይ የሙስና፣ የእምነት ማጉደል፣ የስርቆት፣ የማጭበርበር፣ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሞ ሥልጣን ባለው ፍርድ ቤት የተፈረደበት በመንግሥት መሥሪያ ቤት መቀጠር እንደማይችል በረቂቁ ሰፍሯል፡፡

የብቃት መመዘኛዎችንና ሌሎች መሥፈርቶችን በማሟላት ለቅጥር የተመረጠ ሰው ቃለ መሃላ ለመፈጸም ፈቃደኛ መሆን እንደሚያስፈልገው በረቂቅ ሕግ የተቀመጠ ሲሆን፣ የቃለ መሃላው ይዘትም በአንቀጽ 17 ላይ ሰፍሯል፡፡

‹‹እኔ         ሠራተኝነቴ ከሁሉም በላይ አድርጌ በእውነት፣ በታማኝነትና በሥነ ምግባር ሕዝቡን ለማገልገልና የመንግሥትን ፖሊሲዎች ለመፈጸም፣ በማንኛውም ጊዜ ሕገ መንግሥቱንና የአገሪቱን ሕጎች ለማክበርና በሥራዬ ምክንያት ያወቅኩትንና በሕግ ወይም በሚመለከተው አካል ውሳኔ በሚስጥርነት የተመደቡትን ለሌላ ለማንኛውም ወገን ላለመግለጽ ቃል እገባለሁ፤›› የሚለው የቃለ መሃላው ሙሉ ይዘት ነው፡፡

ረቂቅ አዋጁ በመላ አገሪቱ ወጥና በአንድ ዓይነት የሥራ ዓይነቶች ተመሳሳይ ክፍያ እንደሚኖር ይገልጻል፡፡ ሴት ሠራተኞች በወሊድ ወቅት ያገኙት የነበረው የሦስት ወራት የወሊድ ዕረፍት ወደ አራት ወር ከፍ እንዲል በረቂቁ ተካቷል፡፡ በተጨማሪም ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሴት የመንግሥት ሠራተኞች ሕፃናት የሚንከባከቡበት የሕፃናት ማቆያ ማቋቋም እንደሚኖርበትና ዝርዝር አፈጻጸም በመመርያ እንደሚወጣ በረቂቁ አንቀጽ 48(6) ላይ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...