Tuesday, January 31, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በኢትዮጵያ ለሚታየው የፖለቲካ ውጥረት አስፈላጊውን መፍትሔ ለማምጣት እንተባበራለን››

‹‹በኢትዮጵያ ለሚታየው የፖለቲካ ውጥረት አስፈላጊውን መፍትሔ ለማምጣት እንተባበራለን››

ቀን:

የአሜሪካ ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ

በኢትዮጵያ የሚታየውን የፖለቲካ ውጥረት ለመቅረፍ አስፈላጊ የሚሆነውን መፍትሔ ለማምጣት እንደሚረባረቡ፣ በአሜሪካ ሴኔት ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሴናተር ጄምስ ኢንሆፍ አስታወቁ፡፡

ሴናተሩ ማይለን ኢንዚ ከተባሉ ሌላ ሴናተር ጋር በመሆን ሐሙስ ጥቅምት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ተገኝተው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከብሔራዊ ክልሎች ፕሬዚዳንቶች ጋር በወቅታዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውጥረቶችና ግጭቶች ላይ መወያየታቸው ታውቋል፡፡

ሪፖርተር ከአሜሪካ ኤምባሲ ያገኘው መረጃ እንደሚመለከተው፣ ሁለቱ የአሜሪካ ሴናተሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ከክልል ፕሬዚዳንቶች ጋር በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ የፖለቲካ ውጥረቶች ላይ በመወያየት ችግሮች መባባስ እንደሌለባቸው ተግባብተዋል፡፡

በአሜሪካ የሁለትዮሽ የውጭ ግንኙነት ውስጥ ኢትዮጵያ ያላትን ጉልህ ጠቀሜታ ሴናተሮቹ ማስረዳታቸውን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ ሴናተሩ በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተባባሰ የመጣው የፖለቲካ ውጥረት በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ አካባቢያዊ ፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ለመተባበር ያለውን ቁርጠኝነት፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ለክልል ባለሥልጣናቱ በድጋሚ አስረግጠው መናገራቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኢትዮጵያ እየተባባሰ ያለው የፖለቲካ ውጥረት የግድ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር የተነጋገሩት ሴናተሮቹ ለዚህም፣ ‹‹አስፈላጊውን መፍትሔ በማምጣት እንተባበራለን፤›› ማለታቸውን፣ አዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሪፖርተር በሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ ጉብኝት ላይ ያነጋገራቸው አንድ አሜሪካዊ ዲፕሎማት እንዳሉት፣ ሁለቱ ሴናተሮች ኢትዮጵያ የመጡት የአሜሪካን መንግሥት ወክለው አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን ብዙ ጊዜ የሴኔት አባላት የአሜሪካ ከፍተኛ ጥቅም  ባለበት አካባቢ ችግር ሊኖር ይችላል ተብሎ ሲታሰብ በራሳቸው በአካል ተገኝተው ለማየት ይመጣሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ ሥጋት የፈጠረባቸው ሁለቱ ሴናተሮች ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንደመጡም ዲፕሎማቱ ገልጸዋል፡፡

በተለይ ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ ለሚወክሉት ኮሚቴ ሁለተኛ ሰው በመሆናቸው ለሴኔቱ፣ ለኮሚቴውና ለኮንግረሱ ጭምር ባላቸው ተፅዕኖ በኢትዮጵያ ያዩትን ነገር በማስረዳት የአሜሪካ መንግሥት አቋም እንዲይዝ ግፊት እንደሚያደርጉ ዲፕሎማቱ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ የሴናተሮቹ ጉብኝት ከፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ ለምን የክልል ብሔራዊ መንግሥታት ፕሬዚዳንቶችን ሊያካትት እንደቻለ ጥያቄ የቀረበላቸው ዲፕሎማቱ፣ በአሜሪካም ሆነ በተለያዩ አገሮች የውጭ ፖሊሲ ይህ የተለመደ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ካለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ሴናተሮቹ የፌዴራልንም ሆነ የክልል ባለሥልጣናትን አንድ ላይ ማነጋገራቸው ጠቃሚ ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ የአሜሪካን ትልቅ ጥቅም ከማስጠበቅ አኳያ ከሚመለከታቸው ጋር መነጋገራቸው ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉም አክለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ባለችበት የአፍሪካ ቀንድ ለአሜሪካ ሁነኛ አጋር መሆኗ ደግሞ ትልቅ ግምት እንደሚሰጠው ዲፕሎማቱ አስምረውበታል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ለመንግሥት ሚዲያዎች በሰጡት ማብራሪያ፣ ሴናተሮቹ በኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የክልል ፕሬዚዳንቶችም የተገኙት በሴናተሮቹ ጥያቄ መሆኑን ሚዲያዎቹ ዘግበዋል፡፡

ሴናተር ጀምስ ኢንሆፍ በሴኔት አርምድ ሰርቪስ ኮሚቴ ሁለተኛ ሰው መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሴናተሩ የአሜሪካ የጦር ኃይልን ብቁ ለማድረግ የበጀት፣ የቁሳቁስና የሥልጠና ድጋፍ ከየትኛውም ዘርፍ በተለየ ትኩረት እንዲሰጠውና ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት እንዲመከት፣ እንዲሁም በአሜሪካ ላይ የተጋረጡ ዓለም አቀፍ ሥጋቶች እንዲቀለበሱ  ማድረግ ይገባል በሚል አቋማቸው  ይታወቃሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...